የደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን አግተው ለታጣቂዎች ሰጥተዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ተከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, The Federal High Court of Ethiopia
ከወራት በፊት ባልታወቁ ሰዎች ታግተው የደረሱበት ካልተወቁ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እገታ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ አስራ ሰባት ሰዎች ላይ የሽብር ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው።
በብሔራዊው ቴሌቪዥን እንደተዘገበው ዛሬ አርብ ሐምሌ 10/2012 ዓ.ም በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሦስት ክስ የተመሰረተባቸው ሰዎች 17 ሲሆኑ የክስ መዝገቡም እነከሊፋ አብዱራህማን በሚል እንደሚጠራም ተገልጿል።
ክስ የተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎቹ እስካሁን ያሉበት ያልታወቁና አብዛኞቹ ሴት ተማሪዎችን አግተዋል በሚል ዐቃቤ የእገታና የጠለፋ ሽብር ወንጀልን ጠቅሶ ነው ክስ የመሰረተባቸው።
ሌላኛው በተጠርጣሪዎቹ ላይ የቀረበው ክስ ደግሞ ከተከሳሾቹ አንዱ ተማሪዎቹ በጫካ ውስጥ እየተጓዙ ስለመሸባቸው ታጋቾች መሆናቸውን እያወቀ ቤቱ በማሳደሩና ሁኔታውን ለየትኛውም የመንግሥት አካል ባለማሳወቁ የሽብር ወንጀልን ባለማሳወቅ ክስ ቀርቦበታል።
ለፍርድ ቤቱ በቀረበው ክስ ላይ ተማሪዎቹ ወደ አማራ ክልል በአንድ መኪና በመጓዝ ላይ ሳሉ በቄለም ወለጋ ዞን ደምቢ ዶሎ ከተማ ሰዬ እና አንሰሎ ወረዳዎች በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ ከመኪናው በማስወረድ እየደበደቡ ጫካ ውስጥ ለሚገኙ የኦነግ ሸኔ አመራሮች አሳልፈው መስጠታቸው ተገልጿል።
በዛሬው ችሎት ሰባት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ሲገለጽ፣ ሁለቱ በኮሮናቫይረስ በመጠርጠራቸው ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን የቀሩት ተከሳሾች እንዲቀርቡ ችሎቱ አዟል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ክስ ያሰማው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በችሎቱ የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ከጠበቃቸው ጋር ተመካክረው እንዲቀርቡና ክሳቸው እንዲሰማ ለሐምሌ 30/20 12 ዓ.ም ቀጠሮ መስጠቱ ተገልጿል።













