ስለታገቱት ተማሪዎች መንግሥት ዝምታውን የሰበረበት መግለጫ

የታገቱ ተማሪዎች ጉዳይ የሚያጣራ ቡደን መቋቋሙን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዛሬ በተሰጠ መግለጫ ተነግሯል።
መግለጫውን የሰጡት የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፣ የሳይንስ እና ከፍትኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጀኔራል ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ናቸው።
በመግለጫው ምን ተባለ
የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክቴሪያት አቶ ንጉሱ ጥላሁን በአገሪቱ በሚገኙ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንደተከሰተው ሁሉ በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲም ተመሳሳይ የጸጥታ ችግር እንደተከሰተ አስታውሰዋል።
በዚህም ለደህንነታቸው የሰጉ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲውን ለቀው ሲወጡ እንደነበረ በማስታወስ፤ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ጥለው እንዳይሄዱ ፌደራል ፖሊስ ከአካባቢው ማህብረሰብ ጋር የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
የፌደራል ፖሊስ በአከባቢው ያለውን የጸጥታ መደፍረስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲውን ጥለው ከወጡ ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል ሲያስጠነቅቅ እና መረጃ ሲሰጥ ነበረ ብለዋል።
"ተማሪዎች ግን በማይጠበቅ መንገድ በጋምቤላ በኩል ጉዟቸውን ቀጠሉ።" ብለዋል አቶ ንጉሱ።
ቸአንፊሎ ወረዳ ሱዲ በምትባል ቦታ ላይ ተማሪዎች፣ ሌሎች ወጣቶች እና አንድ የአካባቢው አመራር ጭምር ህዳር 25፣ 2012 ላይ መያዛቸው መረጋገጡን አቶ ንጉሡ ተናግረዋል።
"ሰዎች መያዛቸው ሲሰማ መከላከያ ሠራዊት አሰሳ አካሂዶ 21 ተማሪዎችና ሌሎች ተጨማሪ ሰዎችን ማስለቀቁን ጠቅሰው፤ 21ዱ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲው እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል። "በቀን ጥር 2 ይህኑን መረጃ ለሕዝብ ማቅረባችን ይታወሳል፤ በእጃችን ላይ ያለን መረጃ ጥር 2 ላይ የሰጠነው መረጃ ትክክለኛነትን ያረጋግጣል" ብለዋል፤ አቶ ንጉሡ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ የአካባቢው የ2ኛ ደረጃ ተማሪና ሌሎች አምስት ሰዎች እየተጓዙ እያሉ 6 ሰዎች መያዛቸውን አቶ ንጉሡ ተናግረዋል። ከአምስቱ ተያዙ ከተባሉ ወጣቾች መሀል የአንዱ ወላጅ አባት ታጋቾቹ ተማሪዎች እንደሆኑ የገለጹ ቢሆንም እኛ ግን እያጣራነው ነው ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል አቶ ንጉሡ።
አቶ ንጉሡ ጨምረወ እንዳብራሩት "አንድ መጥራት ያለበት ጉዳይ መገናኛ ብዙሃንም ሆኑ በማህብራዊ ሚዲያ ላይ የሚነገረው የታገቱት ተማሪዎች ቁጥር 17 ስለመሆናቸው ነው። ይህ ቁጥር ሲጣራ ግን ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ የሚያሳያው 12 ብቻ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ናቸው። 5 ግን የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ስለመሆናቸው መረጃ የለም" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት 800 የሚሆኑ ተማሪዎች የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ጊቢ ለቀው መውጣታቸውን አስታውቀዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጀኔራል ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው
የፌደራል ፖሊሰ ኮሚሽነር ጀነራል በበኩላቸው "በስፍራው አላንቀሳቅስ አላላውስ ብለው ሕዝብ የሚያስቸግሩ አካላት አሉ" ሲሉ ተናግረዋል።
"በደምቢ ዶሎ አካባቢ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል ተደምስሷል። ተደምስሶ ግን አልቀረም። የተረፈው አሁን እራሱን አደራጅቶ በሽፍታ መልክ እየተንቀሳቀስ ነው። መንግሥት ዝም አላለም። እርምጃ እየወሰደ ነው።"ብለዋል።
እገታው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችንና የአካባቢው ነዋሪዎችን እንዲሁም ነጋዴዎችን ይጨምራል ሲሉ ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተረጋጋ ሁኔታ እንዲማሩ ዝግጅት እየተደረገ ነውም ብለዋል።
ልጆቹ የት ነው ያሉት ተብሎ ለሚነሳው ጥያቄ "በእጃችን በቂ መረጃ አለ። እነዚህ መረጃዎች ተገቢ ክትትል እየተደረገባቸው ነው የሚገኙት። መረጃዎች ልጆቹ ላይ ከቀላል እስከ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል እየተባለ በሚወራው ጉዳይ እስካሁን በፖሊስ የተረጋገጠ አይደለም። በጉዳዩ ላይ ምረመራ እየተካሄደ ስለሆነ ዝርዝር መረጃ መስጠት አልፈለግንም። ሦስት ቡደን አደራጅትን ምርመራዎችን እያካሄድ ነው" ብለዋል።
የሳይንስ እና ከፍትኛ ትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ
ዶ/ር ሳሙኤል "ከተማሪዎቹ እገታ ጋር በተያያዘ የሰማነው ቁጥር 17 ነው። ይህን ቁጥር በመጀመሪያ የሰጠችው አስምራ ሹምዬ የምትባል ተማሪ ነች። በዚህ ጉዳይ መረጃ መስጠት ያለብኝ ስለመሰለኝ ነው ይህን ማብራሪያ የምሰጠው ብለዋል"
ተማሪ አስምራ ለአካባቢው ኮማንድ ፖስት ሰጠች ያሉትን መረጃ ዶ/ር ሳሙኤል እንደሚከተለው አስቀምጠዋል።
"በአካባቢው ላለ የኮማንድ ፖስት በ26-03-2012 የሰጠችው መረጃ፤ 'ህዳር 25 ላይ ከደምቢ ዶሎ ወጥተን በጋምቤላ አድርገን ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ሱዲ በሚባል ቦታ ላይ ወጣቶች ወሰዱን፤ እኔ አምልጬ አንድ ሽማግሌ አሳፍረው ወሰዱኝ' በማለት በንጋታው (ህዳር 26 ) ለኮማንድ ፖስት ተናግራለች" ብለዋል።
"የታገቱት ተማሪዎች ከእርሷ ጋር 7 ሰው መታገቱን ተናግራ ነበር። እዚህ ከመጣች በኋላ 17 ብላላች። እገታው ከተካሄደ ከአራት ቀናት በኋላ የአገር መከላከያ 21 የሚደርሱ ሰዎችን አግኝቶ 19ኙ ተማሪዎች ናቸው ተብሎ ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመልሰዋል" ያሉት የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ዲኤታው ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ነገር ግን መንግሥት ተለቀዋል ያላቸው ተማሪዎች በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ እንደሚገኙ ጥቆማ ሰጥተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው አጭር መዘርዝር ጠፍተዋል ብለው ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ያቀረቡ ወላጆች ቁጥር 11 መሆኑን ጠቅሶ በተለያየ መልኩ ጠፍተዋል ተብለው ከተገለጹት ተማሪዎች ውስጥ 9ኙ ወላጆቻቸው ሪፖርት አላደረጉም ወይም የወላጆቻቸው አድራሻ ማግኘት አልተቻለም ይላል።
በመንግሥት በኩል መረጃው ከደረሰ ጀምሮ ተማሪዎችናን ዜጎችን የማፈላለግ ሥራ በመሠራት ላይ እንደሆነ የሚጠቅሰው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፌት ቤት መግለጫ ጠቃሚ መረጃና ማስረጃዎች ተገኝተዋል፤ ጠንካራ የምርመራ ሥራ እየተሠራ ነው ሲል ያትታል።












