ሻሸመኔ፡ ቤት ንብረት የወደመባቸው ሰዎች በምን ሁኔታ ላይ ናቸው?

ሻሸመኔ

ሰኔ 23 ምሽት የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ከተሰማ በኋላ የተለያዩ ውድመቶችና ጥቃቶች ከደረሱባቸው አካባቢዎች መካከል ሻሸመኔ አንዷ ናት።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰቦች የሥራ ቦታ፣ ፋብሪካ፣ ህንጻ፣ መኖሪያ ቤቶች መውደማቸውንና በርካቶችም የነበራቸውን ሁሉ በጥፋቱ አጥተው ባዶ እጃቸውን ቀርተዋል።

"ስለወደመው ከማውራት ስለተረፈው ማውራቱ ይቀላል" የሚሉት ተጎጂዎች በአንድ ድምጽ 'መንግሥት ቶሎ ቢደርስልን' ሲሉ ይደመጣል።

የአርቲስቱ ግድያ ከተሰማ በኋላ በኦሮሚያ ክልል፤ 523 መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፤ 499 መኖሪያ ቤቶች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የክልሉ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በክልሉ በተፈጸመው ውድመት ቤት ንብረታቸውን አጥተው የመንግሥት እርዳታን የሚሹ ሰዎች ቁጥር ከ10 ሺህ በላይ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።

ተጎጂዎች ምን ይላሉ?

ሻሸመኔ ቀበሌ አስር ውስጥ ከባለቤታቸውና ከሦስት ልጆቻቸው ጋር የሚኖሩት ግለሰብ በወቅቱ ጥቃት ከደረሰባቸው መካከል አንዱ ናቸው።

ግለሰቡ ለቢቢሲ እንዳሉት በነበረው አለመረጋጋት ቤት ንብረታቸው ሙሉ በሙሉ ወድሟል።

ግለሰቡ ተወልደው ያደጉት ሻሻመኔ መሆኑን ተናግረው "ወላጆቼም የተወለዱት፤ አያቶቼም የኖሩት እዚህ ነው" ሲሉ ከሻሸመኔ ውጪ የሚያውቁት ቦታ እንደሌለ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

"የቤቴ ጣርያው፣ በሩ፣ መስኮቱ ተነቃቅሎ ተሰባብሯል" የሚሉት ግለሰቡ ንብረታቸው ሙልጭ ተደርጎ መዘረፉንም ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ቤት ንብረታቸው ሲወድም በስፍራው የነበሩ ቢሆንም ለመከላከልም ሆነ ንብረታቸውን ለማትረፍ የሚያስችል ሁኔታ እንዳልነበር የሚናገሩት ግለሰቡ፤ በጓሮ በኩል በሚገኝ ሌላ መውጫ ሾልከው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ከቤታቸው አቅራቢያ ወደሚገኘው ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን መሸሻቸውን ያስታውሳሉ።

እኚህ የሦስት ልጆች አባት የሆኑት ግለሰብ ከአካባቢያቸው ካሉ ነዋሪዎች ተለይተው ጥቃት እንደደረሰባቸው እንደሚያምኑም ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በአካባቢያቸው ቤቶች ሲቃጠሉ የአንዱን ቤት ከሌላኛው ለመለየት ጥቃት ፈጻሚዎቹ የብሔርና የሐይማኖት ሽፋን መጠቀማቸውንም ይገልፃሉ።

ግለሰቡ በአሁኑ ሰዓት ልጆቻቸውን ወደ ሐዋሳ አሽሽተው እርሳቸው ደግሞ በሻሸመኔ ከተማ በሚገኝ ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ በመግለጽ ከእርሳቸው ጋር 80 ያህል ንብረታቸው የወደመባቸው ሰዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ግለሰቡ እንደሚናገሩት የአካባቢው አስተዳደር ያረፉበት ድረስ በመምጣት ድጋፍ ያደረገላቸው ቢሆንም ወጥ አለመሆኑን አስረድተው መጠኑም ቢሆን ለሁሉም የሚበቃ አለመሆኑን ገልፀዋል።

በተለያየ ጊዜ ከከተማው አስተዳደር ጋር ስብሰባ ማድረጋቸውን፣ ከቀበሌ እና ከፌደራል መጣን ያሉ ሰዎች እንዳናገሯቸው፣ የወደመ ንብረታቸውንም መመዝገባቸውን በመግለጽ አስተማማኝ የሆነ ድጋፍ እና መደረግ ያለበትን ግን አለመስማታቸውን ተናግረዋል።

እኚህ በቤተክርስቲትያን ውስጥ ተጠልለው የሚገኙት ግለሰብ በአሁኑ ወቅት "ከዚህ በኋላ የት ነው የምንሄደው? እንዴት ነው የምንኖረው? ሕይወታችንን እንዴት ነው የምንቀጥለው?" የሚሉ ጥያቄዎች መልስ እንደሚያሳስቧቸው ይገልጻሉ።

ሌላኛው ቢቢሲ ያነጋገራቸው ቤት ንብረታቸው የወደመባቸው ግለሰብ አደጋው በደረሰባቸው ወቅት ቤታቸው ውስጥ የእርሳቸውን ልጆች ጨምሮ በእንግድነት የመጡ ሁለት ልጆች እንደነበሩ ይናገራሉ።

ሻሸመኔ ውስጥ በንግድ ሥራ ተሰማርተው እየኖሩ እንደነበር የሚገልፁት ግለሰቡ፤ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት መሆናቸውንና አንድ የማደጎ ልጅ አብሯቸው እንደሚኖር ተናግረዋል።

በወቅቱ የባለቤታቸው ወንድም ሁለት ልጆች በእንግድነት መጥተው አብረዋቸው እንደነበሩ የሚገልፁት እኚህ ግለሰብ፤ ሰፈራቸው ውስጥ ጥቃት አድራሾቹ መጥተው ስማቸውን እየጠሩ በራቸውን ሲደበድቡ ግቢ ውስጥ ለእቃ ማስቀመጫነት ወደ ተሰራች አነስተኛ ክፍል ሰባት ሆነው ገብተው መደበቃቸውን ያስታውሳሉ።

የስኳር ህመምተኛ መሆናቸውን የሚናገሩት እኚህ ግለሰብ በዚያ ችግር ውስጥ ሁሉ ልጃቸው መድኃኒታቸውንና ስልካቸውን ኪሳቸው ውስጥ መክተታቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በሚኖሩበት ሰፈር ውስጥ የእርሳቸው መኖሪያ ተመርጦ ጥቃት እንደደረሰበት የሚገልፁት እኚህ ግለሰብ በወቅቱ የግቢያቸውን በር ጥሰው የገቡ ጥቃት አድራሾች መኪናቸውን በመሰባበር እና ገፍተው ከግቢ በማውጣት በእሳት መለኮሳቸውን ተናግረዋል።

መኖሪያ ቤታቸውም ቢሆን መሰባበሩንና መዘረፉን የሚናገሩት ግለሰቡ "ዋናውን ቤት ሰባብረው ከጨረሱ በኋላ ተደብቀን ወደነበርንበት ክፍል መጥተው በሩን መደብደብ ጀመሩ" ሲሉ ያስታውሳሉ።

በወቅቱ እዚያው ባሉበት ክፍል ሆነው አደጋውን ከመቀበል፣ ወጥተው ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን እንዳይነኩባቸው መማፀን ጀመሩ።

ከጥቃት አድራሾቹ መካከል አንድ ወንድና አንድ ሴት ወደፊት መጥተው እነርሱን ማንም እንዳይነካቸው እንደተናገሩና ከግቢያቸው ወጥተው እንዲሄዱ እንደፈቀዱላቸው ያስታውሳሉ።

ከቤታቸው ወጥተው እየሄዱ በነበረበት ጊዜ የማያውቁት ሰው ደውሎ የልጆቻቸውና የእርሳቸው ህይወት እንዲተርፍ ከፈለጉ ገንዘብ እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን የሚናገሩት እኚህ ግለሰብ፤ በተለያየ ወቅት ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ጋር እየተደወለ ጥቆማ እንዳያደርጉ ማስፈራሪያ እንደሚደርስም ተናግረዋል።

ጥቃቱ በደረሰበት ወቅት ልጆቻቸው ያለጫማ፣ እርሳቸውና ባለቤታቸው ደግሞ በለሊት ልብስ መውጣታቸውን የሚናገሩት ግለሰቡ በቀጥታ በአካባቢው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ማምራታቸውን ያስታውሳሉ።

በወቅቱ የተጠለሉበት ፖሊስ ጣቢያም ተኩስ እንደነበር የሚገልፁት ግለሰቡ ከመምሸቱ በፊት መሃል ከተማ ወደሚገኙ የቅርብ ወዳጆቻቸው ጋር ሄደው መጠለል መምረጣቸውን ይናገራሉ።

ግጭቱን የተመለከቱ ልጆቻቸውና ዘመዶቻቸውን ስሜት ሲናገሩም መረበሻቸውን፣ መተኛት አለመቻላቸውን፣ በተደጋጋሚ ይባንኑ እንደነበር ያስረዳሉ።

"ከወደመው ንብረት በላይ ታዳጊዎቹ ልጆች አእምሮ ውስጥ የተፈጠረው ነገር አስደንጋጭ ነው" የሚሉት እኚህ ግለሰብ "በፈጣሪ እርዳታ ተርፈናል" በማለት በአንድ ጊዜ ባዶ እጃቸውን መቅረታቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት እርሳቸውና ቤተሰቦቻቸው በተጠለሉበት ስፍራ የአካባቢው ነዋሪ እየመጣ እንደሚያጽናናቸው በመናገር፤ በ49 ዓመታቸው መሬት መተኛታቸው፣ ያለ ቅያሪ ልብስ፣ ሙሉ ቤተሰባቸው ደግሞ ያለ ተገን መቅረታቸውን ማሰብ ከባድ ጭንቀት እንደሆነባቸው ይገልፃሉ።

አሁን ያሉበት ደረጃ ለመድረስ እድሜያቸውን በሙሉ መልፋታቸውን የሚናገሩት እኚህ ግለሰብ ንብረታቸውን ወደ ነበረበት ለመመለስ አስቸጋሪ መሆኑንም ያስረዳሉ።

ጥቃቱ በደረሰበት ወቅት ከተማዋ ውስጥ የፀጥታ አካላት ቢኖሩም ተደራሽ ባለመሆናቸው ችግሩ መድረሱን ተናግረው መንግሥት እንዲያቋቁማቸው ጠይቀዋል።

'ጉዳቱ የደረሰው በሁሉም ላይ ነው'

በሰው እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰው በምዕራብ አርሲ ሦስት ወረዳዎች ውስጥ መሆኑን የተናገሩት የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልጫ፤ በተለይ በሻሸመኔ እና ባቱ ከተሞች እንዲሁም በባሌ ዞን ሮቤ እና አጋርፋ ከተሞች የደረሰው ገዳት ከሌሎች አካባቢዎች አንጻር ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አቶ ጌታቸው ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ ህይወታቸውን ያጡት፣ ቤት ንብረታቸው የወደመባቸው ሰዎች የአንድ ብሔር ወይም ሐይማኖት ተከታይ ብቻ አይደሉም ብለዋል።

"በአንደ ብሔር እና ሐይማኖት ላይ ብቻ ያነጣጠረ አልነበረም። ሁሉም ብሔር እና የሐይማኖት ተከታዮች ጉዳት ደርሶባቸዋል" ሲሉ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።

መልሶ ማቋቋም

ቤት ንብረታቸው ተቃጥሎባቸው ባዶ እጃቸውን ቀርተው የእምነት ተቋማትን ጨምሮ በተለያዩ ስፍራዎች ተጠልለው የሚገኙ ዜጎች ቁጥር በርካታ መሆኑን አቶ ጌታቸው ገልጸው፤ በተፈጸመው ውድመት ንብረታቸው ወድሞባቸው የመንግሥት እርዳታን የሚሹ ሰዎች ቁጥር ከ10 ሺህ በላይ እንደሚሆን አመልክተዋል።

ንብረታቸው የወደመባቸው ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። "የምግብ እና የአልባሳት ድጋፍ በያሉበት እንዲደርሳቸው እየተደረገ ነው" ሲሉ አቶ ጌታቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ቁጥር

ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በተፈጠረው አለመረጋጋት በኦሮሚያ ክልል በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰዎች ቁጥር ሰባት ሺህ በላይ መሆኑን አቶ ጌታቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የክልሉ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ ጨምረውም በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሰዎች ጋር በተያያዘ ፖሊስ አና አቃቢ ሕግ ከ5 ሺህ በላይ በሚሆኑ መዝገቦች ተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ መመስረታቸውንም አመልክተዋል።

አቶ ጌታቸው "መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ጠንክሮ እየሰራ ነው" ካሉ በኋላ፤ "በጸጥታ ኃይሎች የተያዙ ሰዎችም በቁጥጥር ከዋሉበት በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የማቅረብ ሥራ እየተሰራ" መሆኑን ጠቁመዋል።