ጥላቻን፣ ጥቃትንና ጠብ አጫሪነትን የያዙ የፌስቡክ መልዕክቶች እንዴት ይታያሉ?

ፌስቡክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሆነ ተብሎም ይሁን በስህተት ሌሎችን ሊጎዱ የሚችሉ መልእክቶች ይተላለፋሉ።

በኢትዮጵያም በተለይ ፌስቡክን በመጠቀም የሚተላለፉ መልዕክቶች ጥላቻንና ንጹሃንን በተለያየ መልኩ ለጉዳት እየዳረጉ ነው ሲሉ መንግሥትን ጨምሮ አንዳንዶች ወቀሳ ይሰነዝራሉ።

የማኅበራዊ ሚዲያ አውታሩ ፌስቡክም መሰል መልዕክቶች በሌሎች ላይ የሚያሳድሩትን ጫና ለመቅረፍ በማሰብ ማንኛውም የፌስቡክ ተጠቃሚ በገፁ ላይ ሰፍረው የሚመለከታቸው ነገሮች መልዕክቶች (Facebook posts) በሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ ብለው ካመኑ ጉዳዩን ለፌስቡክ ሪፖርት የሚያደርጉበት ቀላል አማራጭ አለው።

በዚህም ፌስቡክ በድረገጹ ላይ የተላለፉት መልዕክት ይዘቶች የማኅብራዊ ሚዲያውን ሕግጋት ያልተከተሉ ከሆነ ከገጹ ላይ ያስወግዳል።

ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ የፌስቡክ መልዕክቶች የትኞቹ ናቸው?

የሚከተሉት አይነት ይዘት ያላቸው መልዕክቶች በተጠቃሚዎች ላይ ቀጥተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ፌስቡክ ሪፖርት ሊደረጉልኝ ይገባል ይላል። መልዕክቶቹ በጽሁፍ፣ በፎቶ ወይም በቪዲዮ መልክ ሊቀርቡ ይችላሉ። እነሱም

የጥላቻ ንግግሮች

ፌስቡክ የጥላቻ ንግግርን ሰዎችን በብራቸው፣ በቆዳ ቀለማቸው፣ በይማኖታቸው፣ በጾታቸው እና በአካል ጉዳተኝነታቸው በመለየት ከሰዋዊ ክብራቸው ዝቅ የሚያደርግ እና የሚያዋርድ ጥቃት ሲል ይገልጸዋል። በዚህም ምክንያት ፌስቡክ የጥላቻ ንግግሮችን ከገጹ ላይ ያስወግዳል።

ሐሰተኛ ዜናዎች

ሐሰተኛ ዜና ሆነ ተብሎ የፖለቲካ ወይም የገንዘብ ፍላጎትን ለማሟላት ሲባል የሚሰራጭ የውሸት መረጃ ማለት ነው። በርካቶች የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት ሐሰተኛ መረጃዎችን እውነት በማስመሰል ያሰራጫሉ።

በኢትዮጵያና በተለያዩ አገራት ውስጥ ፌስቡክን በመጠቀም የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎችን ለተለያዩ ጥፋቶችና ጉዳቶች መንስዔ መሆናቸው ከዚህ በፊት መዘገቡ ይታወሳል። ፌስቡክም ከተጠቃሚዎቹ በሚደርሱት ሪፖርቶች መሠረት አስፈላጊውን ማጣራት ካካሄደ በኋላ ሐሰተኛ መረጃዎቹን ከገጹ ላይ ያነሳል።

ልቅ የሆኑ ምስሎች እና ቪዲዮዎች

ፌስቡክ ልቅ የሆኑ የግብረ ሥጋ ግነኙነትን እና እርቃንን የሚያሳዩ ምስሎችን እንዲሁም ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ያግዳል። ለዚህም እንደምክንያት የሚቀርበው እንደዚህ አይነት የአደባባይ መልዕክቶች ከማኅበረሰቡ እሴት ጋር አብሮ አይሄድም የሚለው አንዱ። በተጨማሪም ቪዲዮዎቹ እና ምስሎቹ የተገኙት ተገቢው ፍቃደኝነት በተሰጠበት ሁኔታ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ስለማይገኝላቸው ነው።

ሽብር የሚነዙ መልዕክቶች

የሸብር ጥቃትን ወይም ሽብርተኛን የሚያወድሱ፣ የሽብር ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ወይም ለሽብር ቡድን አባልነት ጥሪ የሚያደርጉ፣ በሽብር ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው ላይ የሚያፌዙ የፌስቡክ መልዕክቶች በፍጥነት እንዲጠፉ ይደረጋሉ። ተጠቃሚዎች ይህን አይነት ይዘት ያላቸውን መልዕክቶችን ሪፖርት እንዲያደርጉ ፌስቡክ ይጠይቃል።

ኃይል ጥቃትን የሚያንጸባርቁ መልዕክቶች

ፌስቡክ የኃይል ጥቃትን የሚያሞግሱ እና ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች የሚያዋርዱ መልዕክቶችን ያስወግዳል ወይም ተጠቃሚዎቹ ምስሎቹን ከመመልከታቸው በፊት ምስሉ/ቪዲዮው ስሜት የሚተብሽ ይዘት እንዳለው በመግለጽ ያስጠነቅቃል።

ከዚህ በተጨማሪም ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በፌስቡክ ፈጽሞ ተቀባይነት የላቸውም።

ከላይ የተጠቀሱትን አይነት ይዘት ያላቸውን የፌስቡክ መልዕክቶች እንዴት ሪፖርት ማድረግ ይቻላል?

ቀላል ነው።

ፌስቡክ

የፎቶው ባለመብት, Facebook

ለምሳሌ በምስሉ ላይ የሚታየው መልዕክት ይዘት በፌስቡክ ተጠቃሚዎች ላይ ጉዳት ያደርሳል ብለን እናስብ።

ይህን መልዕክት ለፌስቡክ ሪፖርት ለማድረግ ከመልዕክቱ በስተቀኝ አናት የሚገኙትን ••• (ሦስት ነጥቦችን) መጫን። ሦስቱን ነጥቦች ስንጫን የተለያዩ አማራጮችን ይሰጠናል። ከዚያም እርዳታ ያግኙ ወይም ፖስቱን ሪፖርት ያድርጉ (Find Support or report post) የሚለውን አማራጭ ይጫኑ።

ከዚያም እርዳታ ያግኙ ወይም ፖስቱን ሪፖርት ያድርጉ (Find Support or report post) የሚለውን ሲጫኑ ከታች የሚታየውን አይነት ሌላ አማራጭ ይሰጥዎታል።

Facebook

የፎቶው ባለመብት, Facebook

ለምሳሌ የተመለከቱት የፌስቡክ ፖስት ወይም መልዕክት የጥላቻ ንግግር ይዘት ካለው፤ 'Hate Speech' የሚለውን ይጫኑ። ከዚያም ጉዳዩን ሪፖርት በማድረግዎ ከፌስቡክ ምላሽ ያገኛሉ።

የፌስቡክ ፖስትን ሪፖርት ካደረኩ በኋላ ምን ይከሰታል?

እርሶ ወይም ሌሎች አንድን የፌስቡክን ፖስት ሪፖርት ስላደረጉ ብቻ ፌስቡክ ከገጹ ላይ ያስወግደዋል ማለት አይደለም። ፌስቡክ የራሱ የሆነ 'ኮሚኒቲ ስታንዳር' ወይም የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም መመሪያ አለው። ሪፖርት የሚደረጉለትን ይዘቶችንም የሚመረምረው እና ከውሳኔ የሚደርሰው 'ኮሚኒቲ ስታንዳርዱን' መሠረት በማድረግ ነው።

እርስዎ ሪፖርት ያደረጉት ይዘት የትኛውም አይነት እርምጃ ይወሰድበት፤ እርሶ ይዘቱን ለፌስቡክ ሪፖርት ማድረጎ በሚስጥር የሚጠበቅ ነው የሚሆነው።

የጥላቻን፣ ጥቃትና ግጭት ቀስቃሽ እንዲሁም የኅብረተሰብን እሴቶች የሚቃረኑ በማንኛውም መልኩ የቀረቡ መልዕክቶችን የፌስቡክን ሥርዓት ተጠቅሞ ሪፖርት በማድረግ ሊደርሱ የሚችሉ አሉታዊ ውጤቶችን መቀነስ ይቻላል።