ሂላሪ ክሊንተን ስለኤፕስቲን ወንጀሎች 'ምንም እንደማያውቁ' ለኮንግረስ አባላት ተናገሩ

የቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን

የፎቶው ባለመብት, REUTERS/Shannon Stapleton TPX IMAGES OF THE DAY

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ሂላሪ ክሊንተን ስለጄፍሪ ኤፕስቲን ወንጀሎች "ምንም እንደማያቁ" ለኮንግረስ አባላት ተናገሩ።

ክሊንተን አክለውም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሟቹ የወሲብ ወንጀለኛ ጋር ስላላቸው ግንኙነት ቃለ መሃላ ገብተው እንዲጠየቁ ጥሪ አቅርበዋል።

የቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደተናገሩት ከሆነ ኤፕስቲንን በተመለከ ምርመራ ለሚያከናውነው የኮንግረስ ኮሚቴ ለሰዓታት በዝግ ከመሰከሩ በኋላ "እውነታው ወጥቶ ማየት እፈልጋለሁ" ብለዋል።

ባለቤታቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ዛሬ ኮሚቴው ፊት ቀርበው ይመሰክራሉ ተብሏል።

ጥንዶቹ የፓናሉን መጥሪያ ፖለቲካዊ ነው በማለት ሲቃወሙ ቢቆዩም ኮንግረሱን በመድፈር ከመጠየቅ በሚል ለመመስከር ተስማምተዋል። ክሊንተን እና ትራምፕ ከኤፕስቲን ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

ሐሙስ ዕለት ለስድስት ሰዓታት ከቁጥጥር ኮሚቴው አባላት ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ምስክርነቱ ለሕዝብ ይፋ ባለመደረጉ "በጣም አዝኛለሁ" ብለዋል። "በዚህም እዚህ መጥቼ ለእርስዎ መግለጽ አይጠበቅብኝም ነበር" ብለዋል።

የኮሚቴው ሊቀመንር ጄምስ ኮመር ስለ ምርመራው ባህሪ እና መመርመር ስለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች በመስማታቸው አመስግነዋቸዋል።

"ይህንን አደንቃለሁ። እውነቱ እንዲወጣ እፈልጋለሁ፣ ይህንን ረዥም እና ተደጋጋሚ የሆነ የክስ ሂደት ለማቆም የሚረዳ መንገድ ነበር" ሲሉ ስለኮመር ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ክሊንተን የኮሚቴውን የሪፐብሊካን አባላት ስለኤፕስቲን ወይም ስለተፈረደባት ተባባሪው ስለግሌይን ማክስዌል ሌላ ሰው ባለመጠየቃቸው ትችት መሰንዘራቸውን ገልጸዋል።

ቢል ክሊንተን ስለኤፕስቲን ወንጀሎች ምንም ዕውቀት እንደሌላቸው እና ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ከእሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዳቋረጡ ተናግረዋል።

ከፕሬዚዳንትነት ከለቀቁ በኋላ ከበጎ አድራጎት ሥራቸው ጋር በተያያዘ ግንኙነት የተፈጠረ መሆኑን እና በ2019 በኒውዮርክ እስር ቤት ሕይወቱ ካለፈው የፋይናንስ ባለሙያ ጋር መገናኘታቸው እንደሚቆጫቸው ገልጸዋል።

ሂላሪ ክሊንተን የመክፈቻ ንግግራቸውን ቅጂ በኤክስ ላይ ሐሙስ ዕለት በቻፓኳ፣ ኒውዮርክ ከሚደረገው ችሎት በፊት አውጥተዋል።

ክሊንተን ስለኤፕስቲን እና ማክስዌል "የወንጀል ተግባር ምንም አላውቅም ነበር" ብለዋል።

አክለውም "ሚስተር ኤፕስቲን አግኝቼው አላውቅም። በአውሮፕላኑ አልበረርኩም፤ ደሴቱን፣ ቤቶቹን ወይም ቢሮዎቹን አልጎበኘሁም። ከዚህ በላይ የምጨምረው ነገር የለኝም።"

በተጨማሪም ኮሚቴው ስማቸው በተደጋጋሚ በኤፕስቲን ሰነዶች ውስጥ የተጠቀሰውን ፕሬዝዳንት ትራምፕን በቀጥታ እንዲጠይቅ ጠይቀዋል።

የክሊንተን ስሞች በፋይሎቹ ውስጥ በተደጋጋሚ ተነስተዋል። ከሟቹ የወሲብ ወንጀለኛ ጋር በተያያዙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰነዶች ውስጥ የአንድ ሰው ስም ተገኘ ማለት ከየትኛውም ጥፋት ጋር ይያያዛል ማለት አይደለም።

የሂላሪ ክሊንተን ምስክርነት ከአሜሪካ የሕግ አውጪዎች ጋር በዝግ ያደረጉት ምስክርነት ፎቶ ሾልኮ በመውጣቱ ምክንያት ለአጭር ጊዜ እንዲቋረጥ ተደርጓል።

በኮሚቴው ውስጥ ያሉት ዴሞክራቶች በኮሎራዶ የኮንግረስ አባል ሎረን ቦበርት የተነሳው ፎቶ "ሙሉ በሙሉ ከሕጎቹ ጋር የሚቃረን" መሆኑን ተናግረዋል።

ቦበርት የክሊንተንን ፎቶ ለወግ አጥባቂ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደላኩ ተናግረዋል። ምስክርነቱ ከመጀመሩ በፊት ያነሱት ፎቶ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ክሊንተን በበኩላቸው የቦበርት ድርጊት ሕግ አውጪዎች ሌሎች ደንቦችን እንዳይጥሱ ሂደቱን እንዲቆም ማስደረጋቸውን አስታውቀዋል።

በኮሚቴው ውስጥ ያሉት ዴሞክራቶች የቀድሞዋን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን በመከላከል ውጭ ለተሰበሰቡ መገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።

ሕግ አውጪዎቹ ክሊንተን የተጠየቁትን ጥያቄዎች ሳይገልጹ፣ ሂደቱ ምንም አዲስ ነገር ያልተገኘበት ጊዜ ማባከኛ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በርካታ የመገናኛ ብዙኃን አባላት ስላለው ድባብ ጥያቄዎችን ቢሰነዝሩም፣ የኮንግረስ አባሉ ሮበርት ጋርሲያ በዝርዝር ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ሕዝቡ ሙሉውን እና ያልተስተካከለውን የሂላሪ ክሊንተን ምስክርነት ቅጂ በ24 ሰዓታት ውስጥ ማግኘት እንዲችል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ትራምፕ ለኮሚቴው እንዲመሰክሩ ከመጠየቅ ባለፈ "በፍጥነት መከናወን አለበት" ብለዋል።

ዲሞክራቷ የአሪዞና የኮንግረስ አባል ያሳምን አንሳሪ በበኩላቸው የሐሙሱን ችሎት በጣም "ምንም ቁምነገር የሌለው" ሲሉ ጠርተው ሪፐብሊካኖች "እውነቱን ለማወቅ እና ሰዎችን ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ የሂላሪ ክሊንተንን ፎቶዎች ማግኘት የበለጠ አሳስቧቸዋል" ሲሉ ከስሰዋቸዋል።

ባለፈው ሳምንት በርሊን ጀርመን ውስጥ ከቢቢሲ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ሂላሪ ክሊንተን ስለኤፕስቲን ጉዳይ ስለሚሰጡት ምስክርነት "የምደብቀው ነገር የለም" ሲሉ ተናግረዋል።

"እነዚህ ፋይሎች ሙሉ በሙሉ እንዲለቀቁ ደጋግመን ጥሪ አቅርበናል።"

ኤፕስቲንን አግኝተው እንደማያውቁ ቢገልጹም ግን ማክስዌልን "በጥቂት አጋጣሚዎች" አግኝተዋታል። ማክስዌል በ2010 በኒውዮርክ በተከናወነ የሴት ልጃቸው ቼልሲ ክሊንተን ሠርግ ላይ ተገኝታለች።