"የኤፕስቲንን ሰነዶች ለመመርመር ስል ሥራዬን አቆምኩ"

ገለልተኛዋ አሜሪካዊት ጋዜጠኛ ኤሊ ሌነርድ በአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ይፋ የተደረጉ ሰነዶችን ለመተንተን ጥረት እያደረጉ ካሉት አንዷ ናት

የፎቶው ባለመብት, Ellie Leonard

የምስሉ መግለጫ, ገለልተኛዋ አሜሪካዊት ጋዜጠኛ ኤሊ ሌነርድ በአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ይፋ የተደረጉ ሰነዶችን ለመተንተን ጥረት እያደረጉ ካሉት አንዷ ናት
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

አዲስ የተለቀቁት የወሲብ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስቲን ሰነዶች አሁንም ድረስ በዓለም ዙሪያ በርካቶችን እያነጋገሩ ነው።

የተለቀቁት ሰነዶች ብዛት ለመገናኛ ብዙኃንም ለሕዝቡም ፈታኝ ቢሆንም ዝርዝር ይዘቱን ለመረዳት የሚደረገው ጥረት እንደቀጠለ ነው።

ገለልተኛዋ አሜሪካዊት ጋዜጠኛ ኤሊ ሌነርድ በአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ይፋ የተደረጉ ሰነዶችን ለመተንተን ጥረት እያደረጉ ካሉት መካከል አንዷ ናት።

"3.5 ሚሊዮን ገጾች አንብቤ እንደማልጨርስ ማመን አለብኝ" ትላለች።

ስለ ጄፍሪ ኤፕስቲን ያወቀችው ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ይፋ ከወጣ በኋላ ነው።

ለማኅበራዊ ፍትሕ መቆም የሚያስደስታት ኤሊ፤ ትራምፕ የሚያራምዱትን የምጣኔ ሃብት እና የስደተኞች ፖሊሲዎችን ትቃወማለች።

አዲስ ይፋ የተደረጉት የኤፕስቲን ፋይሎች 3 ሚሊዮን ገጾች፣ 180 ሺህ ምሥሎች እና 2,000 ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ይዘዋል።

ቢል ጌትስ፣ ኢሎን መስክ እና ሪቻርድ ብራንሰንን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ግለሰቦች በሰነዶቹ ውስጥ ስማቸው ተጠቅሷል።

በሰነዶቹ ውስጥ ስማቸው የተገኙ ሰዎች በአጠቃላይ ጥፋተኛ ናቸው ማለት አይደለም።

ከዚህ ቀደም ይፋ በተደረጉ ሰነዶች ውስጥ ስማቸው የተገኘ ግለሰቦች ከኤፕስቲን ጋር የተያያዘ ወንጀል አለመፈጸማቸውን አስታውቀዋል።

ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ፍትሕ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ፍትሕ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ

ኤሊ እንደ አውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 2025 ላይ ከሥራ የለቀቀችው ጊዜዋን የኤፕስቲንን ሰነዶች በመፈተሽ ላይ ለማዋል ነው።

በልጇ ትምህርት ቤት ውስጥ የነበራትን ሥራ ካቋረጠች በኋላ ግን የኤፕስቲንን ሰነዶች ለመተንተን ድጋፍ ማግኘት እንዳለባት አወቀች።

በአውሮፓውያኑ ኅዳር 2025 ላይ የአሜሪካ ኮንግረስ ሁለቱም ምክር ቤቶች የኤፕስቲን ሰነዶች ለሕዝብ ይፋ እንዲደረጉ ውሳኔ አሳልፈዋል።

ውሳኔው 'Epstein Files Transparency Act' የሚባል ሲሆን፤ የአገሪቱ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ሰነዶቹን ይፋ እንዲያደርግ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል።

ሰነዶቹ ይፋ ሲደረጉ ሰዎች ፈልገው ሊያገኙት እና በኮምፒውተር/ስልክ ሊጭኑ በሚችሉበት መንገድ እንዲሆንም ታዟል።

ኤሊ ሰነዶቹን ለመተንተን እንዲያግዟት ጥሪ ያቀረበችላቸው ሰዎች "ከመላው ዓለም ምላሽ እንደሰጧት" ትናገራለች።

ከሦስት ሺህ በላይ የዜጋ ጋዜጠኞች (citizen journalists) ከደቡብ ኮርያ፣ ከኖርዌይ እና ከሌሎችም አገራት ቡድኑን ተቀላቅለዋል።

ሰብስታክ በተባለው የበይረ መረብ ገጽ ላይ ከተሰባሰቡት በጎ ፈቃደኞች መካከል የሥነ ልቦና ባለሙያዎች፣ የሕግ ባለሙያዎች እና የዳታ ባለሙያዎች ይገኙበታል።

'አምናቸዋለሁ'

ኤሊ ከዚህ ቀደም መረጃዎችን በቀላል መንገድ ለመራጮች የማድረስ ሥራ አከናውናለች።

ከዚህ ልምድ በመነሳት የኤፕስቲን ሰነዶችን ለማብራራት እየሞከረች ነው።

ዋነኛ ግቧ ተጎጂዎች ፍትሕ እንዲያገኙ ማስቻል እንደሆነ ትናገራለች።በኤፕስቲን ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ታሪካቸውን ሲናገሩ የሚያምኗቸው ጥቂቶች ናቸው።

"ሴቶች ጥቃት እንደደረሰባቸው ሲናገሩ አምናቸዋለሁ። ታሪካቸውን አምናለሁ" ስትል ኤሊ ታስረዳለች።

"የሚናገሩትን ነገር አዳምጬ ታሪካቸው እውነተኛ መሆኑ እንዲታወቅ ማድረግ እፈልጋለሁ" በማለትም ታክላለች።

ኤሊ ያሰባሰበቻቸው ሰዎች የኤፕስቲን ሰነዶችን የሚመለከቱበት መንገድ ከመገናኛ ብዙኃን የተለየ ነው።

አዲስ ከተለቀቁት ሰነዶች ውስጥ የበርካቶችን ትኩረት የሳቡት በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ተለቀዋል። ምሥሎች እና ጽሑፎች በስፋት ተዘዋውረዋል።

የኤሊ ቡድን ትኩረት ከዚህ የተለየ ነው።

"አዳዲስ ሰነዶች ይፋ ሲደረጉ ሰዎች በተደጋጋሚ የሚያወሩባቸው ጉዳዮች አሉ። እነዚህም የሰነዶቹ መጀመሪያ ላይ ያሉ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው። እኔ የማተኩረው ደግሞ የሰነዱ አጋማሽ እና መጨረሻ ላይ ያለው ይዘት ላይ ነው" ትላለች።

አብዛኛው ሰው ትኩረት የማይሰጣቸው የሰነዱ ክፍሎች ላይ በማተኮር መረጃዎችን ለሕዝቡ ለማድረስ ትሞክራለች።

የተለያዩ ሰዎች ሰነዱ ውስጥ ያገኙትን መረጃ የሚያመሳክሩበት መንገድ እና ክፍተቶችን የሚሞሉበት መንገድ ነው የቀየሰችው። ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ሰነዶች ላይ ሁሉም ሰው እንዳያተኩር ሰነዱን ከፋፍለው ይቃኛሉ።

የተቃቀፉ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty

'ፍትሕ መስፈን አለበት'

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አብዛኛውን ጊዜ ከኤፕስቲን ሰነዶች ጋር በተያያዘ ትኩረት የሚሰጠው ታዋቂ ለሆኑት ሰዎች መሆኑን ኤሊ ትናገራለች።

ታዋቂ ግለሰቦች የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረትም ይስባሉ።

ኤሊ እንደምትለው፤ ሌሎች ሰነዱ ውስጥ የተጠቀሱ እና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችም ችላ ሊባሉ አይገባም።

"ጥቃቅን የሚመስሉ ነገር ግን ትልቅ ትርጓሜ ያላቸው የሰነዱ ክፍሎች አሉ። የኢሜል ልውውጦች እና ትንሽ የሚመስሉ ማስረጃዎች የተጎጂዎችን ታሪክ ይናገራሉ" ትላለች።

የኤፕስቲንን ስም በ1990ዎቹ ለባለሥልጣናት የሰጠች ሴትን በምሳሌነት ትጠቅሳለች።

"ማርያ ፋርሜር በ1996 ለኤፍቢአይ ስለ ኤፕስቲን አስታውቃለች። ስትናገር የነበረው እውነት እንደሆነ ለዓመታት የተሰበሰቡ ማስረጃዎች ይመሰክራሉ" ትላለች።

ለኤፕስቲን ትሠራ የነበረችው አርቲስት ለኤፍቢአይ እንደተናገረችው፤ ኤፕስቲን የ12 እና 16 ዓመት ልጆቿን ፎቶዎች ሰርቋል።

ምሥሎቹን እንደሚሸጣቸው በመስጋት ስትጋፈጠው መረጃውን ካወጣች ቤቷን እንደሚያቃጥለው ዝቶባታል።

ኤፕስቲን ከታዳጊ ሴቶች ጋር መዋኛ ገንዳ ውስጥ ሆኖ ፎቶ እንድታነሳው እንደጠየቃትም ተናግራለች።

የኤፕስቲን ሰነድ ይፋ ሲደረግ ከ30 ዓመታት በፊት የተናገረችው ነገር እውነት መሆኑ ስለተረጋገጠ "እፎይታ" እንደተሰማት ገልጻለች።

የታሪክ ፍሰቱን መስመር ለመከተል እና ክፍተቶችን ለመሙላት ጥቃቅን መረጃዎች ጉልህ ሚና እንዳላቸው ኤሊ ትናገራለች።

"ሰዎች ምን እያሰቡ እንደነበረ፣ ከማን ጋር እየተነጋገሩ እንደነበረ፣ እነ ማን ጓደኞቻቸው እንደሆኑ፣ በየትኛው ወቅት የትኛውን መረጃ እንደሰጡ ማወቅ የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው" ስትል ታስረዳለች።

ብዙዎች ከሰዎች ጋር የሚነጋገሩበት ጉዳይ ለሕዝብ ይፋ አይሆንም ብለው ሲያስቡ ብዙ መረጃ እንደሚያሾልኩ ትገልጻለች።

መገናኛ ብዙኃን የኤፕስቲን ሰነዶችን ሲተነትኑ ሙያዊ አሠራር መከተል ይጠበቅባቸዋል። የኤሊ ትኩረት ደግሞ መረጃዎችን በቀላል መንገድ ማቅረብ ነው።

በእርግጥ ጋዜጠኞችን ታማክራለች።

"በጣም ያበረታቱኛል። ታሪኩን በቻልኩት መጠን በትክክል እንድናገር ያግዙኛል" ትላለች።

ይሄንን ሥራ እንደ እናት ሆና የምታከናውነው "ተጠያቂነት እንዲሰፍን ነው" ስትል ታስረዳለች።

"እናት ነኝ። ለልጆቼ የተሻለ ዓለም ለመገንባት የአቅሜን አደርጋለሁ። የምርመራ ሥራዬ ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች ፍትሕ እንዲያገኙ ይረዳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።"