የሃጫሉን ግድያ ተከትሎ የ166 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, SOPA Images
የታዋቂው ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ተቃውሞና አለመረጋጋት የ166 ሰዎች ህይወት ማለፉን በትናንትናው ዕለት ፓሊስ አስታውቋል።
ድምፃዊው ሰኞ ሰኔ 22፣ 2012ዓ.ም ገላን አካባቢ መገደሉን ተከትሎ 145 ሰላማዊ ሰዎችና 11 የፀጥታ ኃይሎች መሞታቸውን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር ግርማ ገላን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ከዚህም በተጨማሪ 167 የሚሆኑ ግለሰቦችም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል። ከአለመረጋጋቱና ሁከቱም ጋር በተያያዘ 1 ሺህ 84 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ኮሚሽነሩ ግርማ አክለው ገልፀዋል።
ባለስልጣናቱ ለህይወት መጥፋት ምክንያት ያሉት ከፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት እንዲሁም በተለያያዩ ብሔሮች መካከል በተፈጠረ ሁከት የተያያዘ ነው ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ የስምንት ነዋሪዎችና የሁለት ጸጥታ አስከባሪዎች ህይወት ማለፉን የከተማዋ ፖሊስ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ከሰሞኑ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት መግለጫ ነዋሪዎች "ህይወታቸው ያለፈው "በቦምብ፣ ጥይት፣ በድንጋይ እና በመሳሰሉት ነው" ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ 57 የሚሆኑ የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ላይ ጉዳት መድረሱንና ብረትነታቸው የግለሰብ እና የመንግሥት የሆኑ 250 ተሽከርካሪዎች ተሰባብረዋል፣ 20 ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል ሲሉም አክለዋል








