በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የጣልያን አምባሳደር በታጣቂዎች ተገደሉ

የጣሊያን ባንዲራ

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የጣልያን አምባሳደር በተፈፀመባቸው ጥቃት መገደላቸውን የጣልያን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

አምባሳደር ሉቻ አታናሲዮ የተገደሉት ዛሬ ሲሆን ወደ ጎማ ለጉብኝት ከተንቀሳቀው የዓለም ምግብ ድርጅት ቡድን ጋር አብረው ነበሩ ተብሏል።

የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለፈረንሳይ የዜና ወኪል እንዳረጋገጡት አምባሳደሩ ጥቃቱ እንደደረሰባቸው "ወዲያውኑ ሕይወታቸው አልፏል" ።

አምባሳደሩን ለህልፈት ያበቃው ጥቃት የተፈፀመው በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ክፍል ነው።

ከአምባሳደሩ በተጨማሪ የጣሊያን ፖሊስ ኃይል አባል የሆኑ ግለሰብ በካንያማሆሮ ከተማ አቅራብያ መገደላቸውን የጣሊያን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጨምሮ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

የፈረንሳይ ዜና ወኪል በበኩሉ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኙ የአገሪቱን ጦር ኃይል ቃል አቀባይ ጠቅሶ እንደዘገበው ሁለት ሰዎች በጥቃቱ የተነሳ ህይወታቸው አልፏል።

ቃል አቀባዩ ግን የሟቾችን ማንነት ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

የቪሩንጋ ብሔራዊ ፓርክ ባለሥልጣን እንዳሉት ጥቃቱ እገታ ለመፈፀም ያለመ ነበር።

በርካታ ታጣቂ ቡድኖች በሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ድንበር አካባቢ በሚገኘው የፓርኩ አካባቢ ይንቀሳቀሳሉ።

የፓርኩ ጠባቂዎች በተደጋጋሚ በታጣቂዎች ጥቃት ይደርስባቸዋል፤ ይገደላሉም ተብሏል።

የቪሩንጋ ብሔራዊ ፓርክ በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ሲሆን በርካታ አገር ጎብኚዎች የሚያዘወትሩት ስፍራ ነው።

ይህ በተራሮች እና በጥቅጥቅ ደኖች የተከበበው ብሔራዊ ፓርክ በ689 ጠባቂዎች ቢጠበቅም 200 ያህሉ በሥራ ላይ እያሉ መገደላቸውን የፓርኩ ባለስልጣናት ይናገራሉ።