ምርጫ 2013 ፡ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ መጀመራቸውን ይፋ አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, EZEMA/FB
በመጪው ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫው የሚያደርጉትን ቅስቀሳ መጀመራቸውን ይፋ አደረጉ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክረሲና (ባልደራስ) እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በጋራ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የምርጫ ቅስቀሳ መጀመራቸውን ባካሄዷቸው ሥነ ሥርዓቶች በይፋ አድርገዋል።
ቅዳሜ የካቲት 13/2013 ዓ.ም "ንቁ ዜጋ፤ ምቹ አገር" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ የግዮን ሆቴል የምርጫ ቅስቀሳ ጅማሬውን ይፋ ያደረገው ኢዜማ፤ "ይህ ምርጫ ከዚህ በፊት እንደነበሩት የይስሙላ ወይም የሙከራ ሳይሆን፤ በትክክል የመጀመሪያ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲሆን" ኃላፊነት እንዳለባቸው የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል።
የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋም ምርጫው ዜጎች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የምንጥልበትና አገሪቱ ወደተረጋጋ ስርዓት የምትሸጋገርበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
"ጊዜው አሁን ነው!" በሚል መሪ ቃል በምርጫው የሚሳተፈው አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፤ በአዲስ አበባ ጉዳናዎች ላይ ባካሄደው መርሐ ግብር ከባልደራስና ከመኢአድ ጋር በመሆን የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻው መጀመሩን ይፋ አድርጓል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የአብን ሊቀ መንበር አቶ በለጠ ሞላ በምርጫው ስጋት ብቻ ሳይሆን እድልም እንደሚሚመጣ ጠቅሰው "ሁላችንም ከቀደመው የፖለቲካ አዙሪትና የምርጫ ተሞክሮ ተምረን ለአገራችን የመጀመሪያው የተሳካ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ልናደርገው እንችላለን" ብለዋል።
አብን ከአዲስ አበባ ባሻገር በባሕር ዳር፣ በጎንደርና በደሴ ከተሞች የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻው መጀመሩን ባካሄዳቸው ሥነ ሥርዓቶች ይፋ አድርጓል።

የፎቶው ባለመብት, ANM/FB
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወጣው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት የመራጮች ምዝገባና የምርጫ ቅስቀሳ ሰኞ የካቲት 08/2013 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፤ ገዢው የብልጽግና ፓርቲ ባለፈው ሳምንት ሊቀመንበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በተገኙበት ሥነ ሥርዓት ላይ የምርጫ ማኒፌስቶውንና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በዚህ ወቅት የፓርቲው ሊቀመንበር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) እንደተናገሩት "ዋናው ፍላጎታችን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን አሸናፊ የሚያደርግ ምርጫ ማድረግ ነው። ይህም ማለት ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ሁሉም በነጻነት የሚሳተፍበት፣ በሀሳብ ልዕልና የሚመረጥ ወይንም የሚወድቅበትን ሁኔታ መፍጠር ነው" ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ወደዚህ ዓመት ከተሸጋገረ በኋላ በመጪው ግንቦት ማብቂያና በሠኔ ወር መጀመሪያ ላይ ለማካሄድ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ዝግጅት እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል።
ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ከትግራይ ክልል በስተቀር በሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ይካሄዳል በተባለው ምርጫ ከአገሪቱ ሕዝብ ግማሽ ያህሉ በመራጭነት ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ምርጫ ቦርድ ገልጿል።
በዚህ ምርጫ በመላው አገሪቱ ድምጽ የሚሰጡባቸው ከ50 ሺህ በላይ የምርጫ ጣቢያዎች፣ ከ152 ሺህ በላይ የመራጮች ምዝገባን የሚያከናውኑ ባለሙያዎችና ከ254 ሺህ በላይ ምርጫ አስፈጻሚዎ እንደሚሰማሩ ተገልጿል።















