የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጋዜጠኞች መታሰር እንዳሳሰበው ገለፀ

የፎቶው ባለመብት, EHRC Facebook page
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ ያሉ ጋዜጠኞች መታሰር እንዳሳሰበው ገልጿል።
የአዲስ ስታንዳርድ መፅሄት አዘጋጅ መድሃኔ እቁባሚካኤል እንደገና ለእስር መዳረግ፣ የአውሎ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ በቃሉ አላምረው በቁጥጥር ስር መዋሉ እንዳሳሰባቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
በትናንትናው ዕለት ህዳር 1/ 2013 ዓ.ም ይህንን መልእክት ያሰፈሩት ኮሚሽነሩ ከሚዲያ ጋር የተገናኘ ጥፋት ጠፍቶም ከሆነ ፍትሃዊ በሆነ መንገድና ስርአትን በተከተለ ሁኔታም እንዲካሄድ ጥሪ አቅርበዋል።
ሁኔታውንም በቅርበት እንደሚከታተሉም በትዊተር ገፃቸው መልዕክታቸውን አስፍረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች ሃፍቱ ገብረ እግዚአብሐር፣ ፀጋዬ ሃዱሽና አብርሃ ሃጎስ እንዲሁም የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርኩ ጋዜጠኛ ኡዲ ሙሳ ተጨማሪ አራት ጋዜጠኞች በአንድ ምሽት መታሰር ስጋት እንደፈጠረባቸውም በዛሬው ዕለት ህዳር 2/ 2013 ዓ.ም አክለው አስፍረዋል።
"በማንኛውም ጊዜ የሰዎችን ከህግ አግባብ ውጪና ኢፍትሐዊ በሆነ መልኩ ያለመታሰር መብት እንዲከበር ጥሪ እናቀርባለን" በማለትም ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ አትቷል።
ሃብቶም ገብረ እግዚአብሔርና ፀጋዬ ሃጎስ በኢፕድ ስር በሚታተመው የእንግሊዝኛው ሄራልድ ጋዜጣ አዘጋጆች ሲሆኑ አብርሃ ሃጎስ ደግሞ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአረብኛው ክፍል አል አለም በሪፖርተርነት ይሰራል።
ቅዳሜ እለት ጥቅምት 28/2013 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው መድሃኔ ቢለቀቅም ሰኞ እለት ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም እንደገና እንደታሰረም ተገልጿል።
ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በተጨማሪ በጋዜጠኞች መብት ላይ የሚሰራው ሲፒጄ በበኩሉ የአውሎ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ በቃሉ አላምረው እንዲፈታ ለኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጥሪ አቅርቧል።
ጋዜጠኛው ጥቅምት 25/ 2013 ዓ.ም በቁጥጥር ስር እንደዋለና ክስም እንዳልተመሰረተበት አስፍሯል።
ሶስት የፖሊስ መለዮና አንድ የሲቪል ልብስ የለበሱ ግለሰቦች አዲስ አበባ ወደሚገኘው የአውሎ ሚዲያ ማዕከል ቢሮ በማምራት በቃሉን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ሲፒጄ የአውሎ ሚዲያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወልደጊዮርጊስ ተክላይን ጠቅሶ በዛሬው ዕለት ህዳር 2/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫው አካቷል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
የአውሎ ሚዲያ ባወጣው መግለጫም ፖሊሶቹ የእስር ትዕዛዝም ይሁን የፍርድ ቤት ወረቀት እንዳላቀረቡና ጋዜጠኛውንም በቁጥጥር ስር ለምን እንዳዋሉትም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች የሚዲያው ሰራተኞችንም ስለ እስሩ እንዳይናገሩ ትእዛዝ ሰጥተዋል ብለዋል።
የፖሊስ አባላቱ ቢሯቸውን በመፈተሽ ሶስት ላፕቶፖችን እንደወሰዱና፣ የበቃሉ ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ ማስታወሻ፣ የድምፅ መቅጫና 'ሃርድ ዲስክ' መውሰዳቸውንም ሲፒጄ ወልደጊዮርጊስን ዋቢ አድርጎ አስፍሯል።
ጥቅምት 27/ 2013 ዓ.ም በፌደራል አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤት በቦሌ ክፍለ ከተማ ቀርቦ የነበረ ሲሆን ሃሰተኛ መረጃን በማሰራጨትና የኢትዮጵያ መንግሥትን በማዋረድ፣ በምዕራብ ወለጋ የተገደሉ አማራዎችን በተመለከተ የብሄር ግጭት በማነሳሰት መወንጀሉም ተገልጿል። ፖሊስ የጠቀሳቸው ሪፖርቶች እንደለሌም ወልደጊዮርጊስ ይናገራል።
በጠቅላይ አቃቤ ህግ የሰብዓዊ መብቶች አክሺን ፕላን ቢሮ ኃላፊ ይበቃል ግዛው በበኩላቸው በጥላቻ ህግና ሃሰተኛ መረጃን በማሰራጨት ህጉ ተጠርጥሮ እንደተከሰሰ አስረድተዋል።
አቶ ይበቃል በቃሉ በሰራው ሪፖርት መንግሥትና መከላከያ ሰራዊት በምዕራብ ወለጋ 200 አማራዎችን ገድለዋል በማለት መንግሥትን በጥቃቱ ቀጥታ ተሳታፊ በማድረግ እንደሰራ ጠቅሰዋል።
የትኛው ሪፖርት እንደሆነ ባይጠቅሱም የሟቾች ቁጥር ግን 34 ነው ብለዋል። ወልደጊዮርጊስ በኩሉ ሚዲያው የሟቾችን ቁጥር አስመልክቶ በጥቃቱም ሆነ ከጥቃቱ በኋላ ከባለስልጣናት የተሰጡ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን ዋቢ በማድረግ ነው ብሏል።
ሚዲያዎችም ሆነ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በጥቃቱ የሞቱትን ትክክለኛ ቁጥር ማወቅ እንዳልተቻለ ዘግበዋል።
ወልደጊዮርጊስ በበኩሉ መንግሥትን በግድያዎቹ ጥፋተኛ ባያደርጉም መንግሥትን የሚተቹ ሪፖርቶች አቅርበናል በማለት መናገሩን ሲፒጄ አስፍሯል።












