የአሜሪካ ምርጫ፡ በ152 አመታት ውስጥ ለኦስቲን ምክር ቤት በመመረጥ ታሪክ የሰራው ትውልደ ኢትዮጵያዊ

የፎቶው ባለመብት, Obala Obala
ከሰሞኑ የአሜሪካ ምርጫ ጋር ተያይዞ የትራምፕና የባይደን ትንቅንቅ አሜሪካውያንን ብቻ ሳይሆን የመላው አለምን ቀልብ ሰቅዞ ይዞ ነበር።
ከዲሞክራቱ ባይደን ከፍተኛ ድምፅ አግኝቶ በፕሬዚዳንትነት ከመመረጣቸው በተጨማሪ የሚኒሶታ ግዛት ኦስቲን ከተማ በታሪኳ ጥቁር፣ አፍሪካዊ፣ ኢትዮጵያዊ እንዲሁም ስደተኛ በከተማ ምክር ቤት አባልነት መርጣለች።
የ27 አመቱ ኦባላ ኦባላ ትውልዱ ኢትዮጵያ፣ ጋምቤላ ነው። በስደት ወዳቀናባት አሜሪካ ዜግነቱን ያገኘው ከአንድ አመት በፊት ነው። ኦባላ በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት በዩኒቨርስቲ ካምፓሶች ላይ ያለው የምግብ ደህንነትና የኤሌክትሮኒክስ መፅሃፎችን አቅርቦት በተመለከተ ከፍተኛ ቅስቀሳ ማድረጉ የተነገረ ሲሆን በምርጫውም ተፎካካሪውን በ481 የድምፅ ብልጫ እንዳሸነፈ ተዘግቧል።
ስለ ምርጫው፣ በምክር ቤት አባልነቱ ስለሚያከናውናቸው የወደፊት እቅዶች፣ የስደት ጉዞውና ሌሎች ጉዳዮችም ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርጓል።
ቢቢሲ፦ በሚኒሶታ ግዛት፣ ኦስቲን ከተማ፣ የከተማዋ ምክር ቤት አባልነትን መቀመጫ ማሸነፍ ችለሃል። ማሸነፍህን ስትሰማ ምን አይነት ስሜት ተሰማህ? በወቅቱስ ምን አልክ? እንዴትስ ገለፅከው?
ኦባላ፦ከመጠን በላይ ደስታ ነው የተሰማኝ! ምክንያቱም ይሄ ታሪካዊ ነው። በ152 አመታት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሚኒሶታ በከተማው ምክር ቤት አባልነት ጥቁር ስትመርጥ እኔ የመጀመሪያው ነኝ ። ከኔ በፊት የተመረጠ ጥቁር አልነበረም። የምረጡኝ ቅስቀሳ በማደርግበትም ወቅት አሸንፋለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር ምክንያቱም የምወዳደርበትና የወከልኩት አካባቢ (ዲስትሪክት) በሙሉ ነጮች ስለሆኑ። ነገር ግን ማሸነፌን ሳውቅ ከመጠን በላይ ደስታ ተሰማኝ። በከተማው ምክር ቤትም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሆኜ መመረጤ ከፍተኛ ደስታ ነው የሰጠኝ
ቢቢሲ፡ እስቲ ወደ ምርጫ ቅስቀሳህ እንመለስና፤ መቼ ነው በምርጫው ለመወዳደር የወሰንከው? የምረጡኝ ቅስቀሳውስ ምን ይመስላል? የተወዳደርክበት አካባቢ የህዝቡ መዋቅርስ ምን ይመስላል?
ኦባላ፡ የወከልኩት (የተወዳደርኩበት) አካባቢ 99 በመቶ ነጮች ናቸው። አፍሪካውያንና ሌሎች አናሳ ህዝቦች በጣም ዝቅተኛውን ስፍራ 0.05 ይሆናሉ። በከተማዋ ሌሎች ክፍሎች ስደተኞች ቢኖሩም እኔ የወከልኩትና ያሸነፍኩበት አካባቢ የነጮች ቦታ ነው። የምረጡኝ ቅስቀሳዬን የጀመርኩት ባለፈው አመት ግንቦት ወር አካባቢ ሲሆን በጣምም ፈታኝ ነበር፤ ምክንያቱም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ጋር ተያያይዞ በርካታ ዝግጅቶችን ማዘጋጀትም አልቻልንም። ሆኖም በመጨረሻ ሁሉ ነገር በሰላም ተጠናቀቀ።
ቢቢሲ፡ የአሜሪካ ዜግነትህን ያገኘኸው ከአንድ አመት በፊት መሆኑን ሰምተናል? መረጃው ትክክል ነው?
ኦባላ፦አዎ ልክ ነው። የአሜሪካዊ ዜግነቴን ያገኘሁት ታህሳስ 7 2012 ዓ.ም ነው።
ቢቢሲ፦ ታዲያ መቼ ነው ለመወዳደር የወሰንከው?
ኦባላ፦ለመወዳደር የወሰንኩት በግንቦት ወር፣ ከጥቂት ወራት በፊት ነው።
ቢቢሲ፦ በተወዳደርክበት አካባቢ ዋነኛ ተቀናቃኝህ (ተፎካካሪ ) የነበሩት እነማን ነበሩ?
ኦባላ፦ዋነኛ ተቀናቃኜ የነበረችው ሄለን ጃር የምትባልና የ66 አመት ግለሰብ ናት። ግለሰቧ እዚሁ ኦስቲን ከተማ የተወለደች ናት። ሙሉ ህይወቷንም በዚሁ ከተማ ነው የኖረችው። በምርጫው ወቅት ከፍተኛ ተፎካካሪዬም ነበረች ሆኖም የኦስቲን ህዝብ እኔን ለመምረጥ ወሰነ።
ቢቢሲ፦ ወደኋላ እንመለስና እስቲ ስለ ልጅነትህ፣ አስተዳደግህና እዚህ ስለደረስክበት ጉዞ እናውራ። በኬንያ ውስጥ ባለው የዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ እንደነበርክ እናውቃለን። በዳዳብ በነበርክበት ጊዜ አንድ ቀን በአሜሪካ ባለ ምክር ቤት አሸንፋለሁ ብለህ አስበህ ታውቃለህ? በዚያን ጊዜስ ህልምህ ምን ነበር?
ኦባላ፦በአሜሪካ ምክር ቤት አሸንፋለሁ የሚል ሃሳብም ሆነ ህልሙም አልነበረኝ። ነገር ግን በዳዳብ ካምፕ ውስጥ ስደተኛ እያለሁ አንድ ቀን አሜሪካ ሄጄ የተሻለ ህይወት እኖራለሁ፤ እንዲሁም ጥሩ ትምህርትም አገኛለሁ የሚል ነበር እንጂ በአሜሪካ ፖለቲከኛ እሆናለሁ ብዬ አላለምኩም። አስቤውም አላውቅ።
ቢቢሲ፡ ጋምቤላ በነበርክበት ወቅት በህፃንነትህ ከፍተኛ ፈተናዎች እንዳጋጠሙህ አንብበናል እናም ምን ነበር ያጋጠመህ? እስቲ ስለ አስተዳደግህ ትንሽ ንገረን። ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ያደረግከው ጉዞስ ምን ይመስላል?
ኦባላ፦የተወለድኩት በኢትዮጵያ፣ ጋምቤላ ነው። ታህሳስ 3/1996 ዓ.ም በጋምቤላ በደረሰው የዘር እልቂት (ጂኖሳይድ) ከ420 በላይ የአኝዋክ ህዝቦች ተገድለዋል። ያንንም ፍራቻ ነው ለመሰደድ የተገደድነው። ሸሽተንም ኬንያ በስደተኝነት መጣን። ከዚያ በፊት የነበረው የልጅነት ጊዜዬ መልካም ነበር።
ቢቢሲ፦ ከዚያስ ኬንያ ነው የደረስከው?
ኦባላ፦ከጋምቤላ ሸሽተን ለሁለት ሳምንት ያህል በእግራችን ተጉዘን የደቡብ ሱዳንን ድንበር ተሻገርን። ደቡብ ሱዳን ቆየን ከዚያም ወደ ኬንያ። በኬንያ የስደተኞች ካምፕም ውስጥ ለአስር አመት ያህል ቆይተናል። በ2013 (በጎሮጎሳውያኑ አቆጣጠር) የአምላክ ፈቃድ ሆኖ ወደ አሜሪካ አቀናን
ቢቢሲ፦ አንድ ዜና ላይ ወደ ከንቲባው ቢሮ ዘው ብለህ ሄደህ በምን መንገድ አስተዋፅአኦ ማድረግ እችላለሁ? የሚል ነገር ተናግረህ ነበር የሚል አንብበናል፤ እስቲ በዝርዝር ስለ ጉዳዩ ንገረን
ኦባላ፦አሜሪካ ከመጣሁ በኋላ በሳውዝ ዳኮታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀቅኩ። ከዚያም እናቴ ሚኒሶታ ከተማ ኦስቲን ግዛት መኖር ጀምራም ስለነበር ወደዚህ መጣሁ።ነዋሪነቴን በኦስቲን ካደረግኩ ከሶስት ወራትም በኋላ ከተማው ጥሩ እንደሆነ ተረዳሁ። እናም በኦስቲን የሚኖሩ የአኝዋክ ጓደኞቼን ሳዋራም ' የኦስቲንን ከንቲባ ታውቃላችሁ ?" እንዲሁም እነማን መሪዎቻችን እንደሆኑ ለምሳሌ የፖሊስ ኃላፊው ማን እንደሆነ ታውቃላችሁ ብዬ ስጠይቃቸው። ሁሉም አናውቅም አሉኝ። ከንቲባ እንዳለ እናውቃለን ግን አግኝተናቸው አናውቅም አሉኝ።
የከንቲባውን ፅህፈት ቤት አድራሻ በጉግል ፈለግኩና ወደቢሮአቸው ሄድኩኝ። ከንቲባውን እንዳየሁዋቸውም ስሜ ኦባላ ኦባላ ይባላል። በቅርብ ከሶስት ወራት በፊት ነው ወደ ኦስቲን ሚኒሶታ የመጣሁት። አሁን ተማሪ ነኝ። የኦስቲንን ከተማም ሆነ ነዋሪውን ለማገዝ ማድረግ የሚያስፈልግ ነገር ካለ አለሁኝ፤ የኦስቲንን ከተማ ለማገዝ በየትኛውም መንገድ አለሁ። ምክንያቱም ኦስቲንን በጣም ነው የምወዳት ከንቲባውም አዩኝና ማን ነህ አሉኝ? ከዚያም ያልኩዋቸውን ደግሜ ከስሜ ጀምሮ ነገርኩዋቸው። ከንቲባው ሳቁና ያሉኝ ነገር ቢኖር ቢሮዬ መጥተህ በምን መንገድ አስተዋፅኦ ላድርግ? በማህበረሰቡስ ልሳተፍ ያልከኝ የመጀመሪያው ስደተኛ ነህ። በኔና በከንቲባው መካከል ያለውም ግንኙነት እየጠነከረ መጣ። ከዚያም ከአመት በኋላ፣ በጎሮጎሳውያኑ 2016 የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ውስጥ ሾሙኝ፤ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቦርድም ከ2016 ጀምሮ አገልግያለሁ።
ቢቢሲ፦ በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ለህዝቡ እሰራለሁ ብለህ የገባሃቸው ጉዳዮች ይኖራሉ። ምንድን ናቸው ቅድሚያ ሰጥተህ የምትሰራባቸው?
ኦባላ፦ዋነኛ ቅድሚያ ሰጥቼ የምሰራው የመኖሪያ ቤቶችን ችግር ነው። በኦስቲን በርካታ ቤቶችን፣ አፓርትመንቶችን መገንባት ይኖርብናል። ስደተኞች ወደ አሜሪካ በሚመጡበት ወቅት ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ቤት መከራየት አይችሉም። ሁለተኛው ደግሞ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ የህፃናት ማቆያ ማዕከል ማግኘት ነው። በኦስቲን ተመጣጣኝ ዋጋ በሆነም ማቆያ ባለመኖሩ ብዙዎች ይቸገራሉ። ከዚያም በተጨማሪ ከሁሉ ነገር በላይ በኦስቲን በርካታ የስራ እድልን መፍጠር ነው። ከሁሉ ነገር በላይ የሚያነሳሳኝ ጉዳይ በማህበረሰቡ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ነው። እንደ ወጣት መሪም መሳተፍ፤ ድምፄንም ለየት ባለ መንገድ በዚህች ከተማም ሆነ ነዋሪውን ለማገዝ መጠቀም እፈልጋለሁ።
ቢቢሲ፦ ስደተኛ ሆነህ ማሸነፍህ ለህፃናት በተለይም ሌሎች ስደተኛ ህፃናትን በማነቃቃት ደረጃ እንዴት ታየዋለህ?
ኦባላ፦በኔ አስተሳሳብ ለየትኛውም ህፃን የማስተላልፈው መልዕክት በኢትዮጵያም፣ በደቡብ ሱዳን፣ ታንዛንያ በየትኛውም የአፍሪካ አገራት ለሚኖሩ ስደተኞች ይሁኑ ሌላ ህልማችሁ ትክክለኛ፤ ተገቢ ነው። በህፃንነታችሁ አሜሪካም መጥታችሁ ከሆነ በትልቅነታችሁም ከሆነ ጠንክራችሁ ከሰራችሁ የአሜሪካ ህልማችሁን ታሳካላችሁ። አሜሪካ ታላቅ ከሆኑ አገራት አንዷ ናት። በርካታ እድሎችም አሉባት። እነዚህ እድሎችም በቀላሉ አይመጡም፤ መውጣት መውረድ ያስፈልገዋል። የተሻለ ሰውነትም ይፈልጋል። ይሄንን መንገድም ነው ለነዚህ ህፃናት እየከፈትኩላቸው ያለሁት። በተለይም ማድረግ አልችልም ብለው ለሚያስቡ ህፃናት፤ አሜሪካም መጥቼ ይሄንን መፈፀም አልችልም ለሚሉ ነው። ትችላላችሁ! የሚል መልእክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ። በአሜሪካም በህይወት መቆየት ከቻላችሁ የምታልሙትን ነገር በሙሉ ማከናወን ትችላላችሁ።
ቢቢሲ፦27 አመትህ ነው። ገና ወጣት ነህ። ቀጣዩ የፖለቲካ ህይወትህ ምን ይሆናል?
ኦባላ፦ብዙም ሩቅ አላስብም። በአሁኑ ወቅት በሚቀጥሉት አራት አመታት ዋናው አትኩሮቴ የኦስቲንን ከተማ መቀየር እንዲሁም ማሸጋገር ነው። ኦስቲን ሁሉን ተቀባይ እንደትሆን ማድረግና ሁሉም የሚበለፅግባት ከተማ እንድትሆን መስራት ነው። ከዚያ በኋላ የወደፊቱ ምን እንደሚሆን አላውቅም፤ ይሄ በራሱ ትልቅ ሃላፊነት ነው። በሚቀጥሉት አራት አመታት ለህዝቡ ቃል የገባሁትን በሙሉ መስራት አለብኝ።የአምላክ ፈቃድ ሆኖም ሌላ እድል ከመጣም እሱንም ለመቀበል ዝግጁ ነኝ። በሚቀጥሉት አመታት ኦስቲን ለህፃናትና ለነዋሪዎቿ የተሻለች ቦታ ማድረግ እፈልጋለሁ።












