ምርጫ 2013፡ ግማሽ ያህል የምርጫ ጣቢያዎች አልተከፈቱም፣ በአፋርና በሶማሌ ምዝገባ አልተጀመረም

የፎቶው ባለመብት, NEBE/FB
ሊካሄድ ሰባት ሳምንት ብቻ በቀረው ስድስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ላይ የመራጮች ምዝገባ ይካሄድባቸዋል ከተባሉት የምርጫ ጣቢያዎች ወደ ግማሽ የሚጠጉት አለመከፈታቸውን የምርጫ ቦርድ ገለጸ።
የመራጮች ምዝገባ ከተጀመረ ከሦስት ሳምንት በላይ ሲሆነው በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ተከፍተው ድምጽ ሰጪዎችን ይመዘግባሉ ተብለው ከታቀዱት 50 ሺህ ያህል የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ምዝገባ እያካሄዱ ያሉት 25 ሺህ 151ዱ ሲሆኑ ከ24 ሺህ በላይ የሚሆኑት ግን ሥራ አልጀመሩም።
ከዚህም ውስጥ የሶማሌና የአፋር ክልሎች ውስጥ የመራጮች ምዝገባ እንዳልተጀመረም ተገልጿል።
ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባና አጠቃላይ የምርጫ ሥራዎች ሂደትን በተመለከተ በምርጫው ከሚሳተፉ ፓርቲዎች አስካሁን ያለውን ሁኔታ በገለጸበት ወቅት ነው።
በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ከትግራይ ክልል ውጪ በመላው የአገሪቱ አካባቢዎች በ674 በሚሆኑ የምርጫ ክልሎች ባሉ 50 ሺህ በሚደርሱ የምርጫ ጣቢያዎች መራጮችን ለመመዝገብ ቢታቀድም ከግማሽ በላይ በሚሆኑት ውስጥ ብቻ ምዝገባው እየተካሄደ መሆኑ ተነግሯል።
የመራጮች ምዝገባው እየተካሄደባቸው ባሉት የምርጫ ጣቢያዎችም ምዝገባው በተፈለገው መልኩ እየሄደ ነው ማለት እንደማይቻል ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።
ለማሳያነትም የአገሪቱ መዲና በሆነችውና ከአምስት ሚሊዮን በላይ ነዋሪ በሚኖርባት በአዲስ አበባ፣ ምዝገባው ከተጀመረ ከሦስት ሳምንታት በኋላ ለመምረጥ የተመዘገበው ሰው ወደ 201 ሺህ የሚጠጋ ብቻ እንደሆነ ተገልጿል።
በአዲስ አበባ ከተማ 1 ሺህ 848 የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው መራጮችን ይመዘግባሉ ተብሎ ቢታቀድም፣ ባለፉት ሳምንታት ውስጥ 186 ጣቢያዎች እንዳልተከፈቱ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመልክቷል።
መጋቢት 16 የተጀመረው የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቅ 10 ቀናት ያህል የቀሩት ሲሆን በቀሩት ቀናት ውስጥ የሚጠበቀውን ያህል ሰዎች ካልተመዘገቡ በቀጣይ ምን አማራጮች እንዳሉ ገና የተገለጸ ነገር የለም።
ምርጫና የፀጥታ ሁኔታ
የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የመራጮች ምዝገባ በሁሉም ጣቢያዎች መካሄድ ያልተቻለው በተለያዩ ችግሮች ምክንያት እንደሆነ ገልጸው፤ ከዚህም ውስጥ በ4126 የምርጫ ጣቢያዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ እንዳልሆኑ አመልክተዋል።
በዚህም ሳቢያ የመራጮች ምዝገባ ሂደት በተለያዩ አካባቢዎች በተፈለገው ፍጥነት እየተከናወነ እንዳልሆነ ወ/ት ብርቱካን ተናግረው፤ ለዚህም በበርካታ ቦታዎች ላይ ባጋጠሙ የጸጥታና የትራንስፖርት ችግሮች የተነሳ ለምዝገባው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ማድረስ ባለመቻሉ የምርጫ ጣቢያዎችን መክፈት አልተቻለም ብለዋል።
በዚህም መሠረት በጸጥታ ችግር ምክንያት የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደባቸው ካልሆኑት ስፍራዎች መካከል በኦሮሚያ ክልል አራት ዞኖች ሲኖሩ እነሱም ምዕራብ ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉድሩ እና ቄለም ወለጋ፤ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን፣ አርጎባና ዋግ ኽምራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል እና በካማሺ እንዲሁም ደቡብ ክልል ጉራፈርዳ፣ ሱርማና ዘልማም እንደሆኑ ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።
ከእነዚህ ውስጥም የመራጮች ምዝገባ ተጀምረው እንዲቋረጡ የተደረገባቸው ሲኖሩ በተጨማሪም በአንዳንድ ስፍራዎች መልሰው እንዲጀመሩ የተደረጉ እንዳሉ ተመልክተዋል።
ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የመራጮች ምዝገባ ማድረግ ካልተቻለባቸው ስፍራዎች ባሻገር በትራንስፖርት ችግር አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ባልደረሱባቸው አካባቢዎች አስፈላጊውን ጥረት በማድረግ የምርጫ ጣቢያዎቹ እንዲከፈቱ እንደሚደረግ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።
ነገር ግን ቦርዱ በቀጣይነት በሚያደርገው ውይይት የመራጮች ምዝገባ ቀናትን እና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት እንደሚመክርና በአጠቃላይ የምርጫ ጣቢያዎችን መክፈት እንዲሁም ምዝገባን በተመለከተ የሚቀጥሉት ሰባት ቀናት የሚኖረውን ሁኔታ እንደሚያሳወቅ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ሕዝቡ በአገራዊው ምክር ቤትና ለክልሎች ምክር ቤቶች ተወካዮቹን ለመምረጥ እንዲችል ቀድሞ እንዲመዘገብ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ መልዕክት አስፍረዋል።
"ዜጎች የመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይጠበቃል። የአገራችንን የነገ ዴሞክራሲ ለመወሰን፣ ዛሬ የመራጮች ምዝገባ መታወቂያ ካርድ እናውጣ። ካርድ ለማውጣት ነገ አትበሉ፤ ነገ ከዛሬ ይጀምራል" በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩጥሪ አቅርበዋል።
ሊካሄድ ሰባት ሳምንታት ያህል በቀሩት አገራዊ ምርጫ ላይ 50 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ድመጻቸውን ይሰጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ባለው የመራጮች ምዝገባ ላይ በተለያዩ ምክንያቶች በርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ሥራ አለመጀመራቸው ተገልጿል።
ቀኑ እስካልተራዘመ ድረስ የምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መጋቢት 16 የመራጮች ምዝገባ በተጀመረባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ምዝገባው በመጪው ሳምንት አርብ ሚያዚያ 15/2013 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ይሆናል።
ምርጫ 2013
ባለፈው ዓመት ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ወደዚህ ዓመት ከተሸጋገረ በኋላ፤ በመጪው ግንቦት ማብቂያና በሠኔ ወር መጀመሪያ ላይ ለማካሄድ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ዝግጅት እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል።
ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ከትግራይ ክልል በስተቀር በሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ይካሄዳል በተባለው በዚህ ምርጫ 50 ሚሊዮን መራጮች ማለትም ከአገሪቱ ሕዝብ ወደ ግማሽ የሚጠጋው ድምጽ በመስጠት ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ምርጫ ቦርድ ገልጿል።
በምርጫው ከሚሳተፉት 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በርካታ ቁጥር ያላቸውን ዕጩዎች በማቅረብ በኩል ገዢው ፓርቲ ብልጽግና 2432 ዕጩዎችን በማስመዝገብ ቀዳሚው መሆኑ በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።
ከዚህ አንጻር ከብልጽግና በመከተል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ዕጩዎች በማስመዝገብ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) 1385 ዕጩዎችን እንዲሁም እናት ፓርቲ ደግሞ 573 ዕጩዎችን አስመዝግበዋል።
ሦስቱን ፓርቲዎች ጨምሮ በምርጫው ለመወዳደር በፓርቲና በግል ለመወዳደር ከስምንት ሺህ ሁለት መቶ በላይ ዕጩዎች መመዝገባቸውን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።















