ምርጫ 2013፡ የሐረሪ ክልል ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን መክሰሱን አስታወቀ

የሐረር ከተማ የጀጎል በር

ከሐረሪ ክልል ውጭ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚኖሩ የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጅ አባላት በሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ አባላት ምርጫ ላይ መሳተፍ አይችሉም የሚለውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ በመቃወም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዱን የሐረሪ ክልል አስታወቀ።

የሐረሪ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ጽህፈት ቤት ኃላፊና የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብዱልሃኪም ኡመር ለቢቢሲ እንደገለፁት ቦርዱ "ሕጋዊ አግባብን አልተከተለም፤ የሕግ ጥሰት ፈፅሟል" በማለት ለከፍተኛው ፍርድ ቤት መክሰሳቸውን አስታውቀዋል።

የሐረሪ ክልል ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ከመውሰዱ በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት "ለምርጫ ቦርድ የላካችሁት ሰነድ ማህተም የሌለውና ፍትሃዊ ባለመሆኑ ውድቅ ተደርጓል" በሚል አቤቱታ ማቅረባቸውን ይናገራሉ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰነዶቹን ማህተም አድርጎ ለምርጫ ቦርድ ቢልክም ውሳኔው ባለመቀልበሱ ወደ ፍርድ ቤት ማምራታቸውን ይናገራሉ።

የሐረሪ ሕዝብ ክልል ምክር ቤት፣ የሐረሪ ሕዝባዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤትና የሐረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የሐረሪ ሕዝብ የክልሉ ምክር ቤት አካል ለሆነው ለሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ እንዲመርጡ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄያቸውን አቅርበው ነበር።

ጥያቄው መነሻውን ያደረገው መጋቢት 6/1987 የሽግግር መንግሥቱ የተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀውን ውሳኔ ተንተርሶ መሆኑንም ከምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ከዚህም በተጨማሪ የሐረሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 50 ቁጥር 2 እንደሚያትተው የክልሉ ምክር ቤት አባላት የሆኑትና 14 አባላት ያሉት "የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አባላት በክልሉ ውስጥና ከክልሉ ውጭ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎችና ከተሞች ከሚኖሩ የሐረሪ ብሔረሰብ አባላት ይመረጣል" የሚለውን መሰረት ያደረገ እንደሆነ አቶ አብዱልሃኪም ያስረዳሉ።

ምርጫ ቦርድም ክልሉ ያቀረባቸውንና በ1987 የሽግግር መንግሥት ተወካዮች ምክር ቤት የወሰናቸውን ውሳኔዎችና ሰነዶቹን ከሕገ መንግሥት አንፃር እንደመረመረ አስታውቆ፤ ከክልሉ ውጭ ያሉ የሐረሪ ተወላጆች በመጪው ምርጫ የመሳተፋቸውን ውሳኔ ውድቅ ማድረጉን ሚያዝያ 1/2013 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ቦርዱ ለዚህም ሕገ መንግሥቱን የጠቀሰ ሲሆን "ቦርዱ በሕገ መንግሥቱ መሰረት በአንድ ክልል የመንግሥት መዋቀር ውስጥ የሚገኙ የምክር ቤት አባላት መመረጥ የሚኖርባቸው በክልሉ ድምፅ መስጠት በሚችሉ ነዋሪዎች ነው" በማለት ገልጿል።

ጨምሮም "ከዚህ ውጭ ሕገ መንግሥቱ አንድ ቁጥሩ አነስተኛ የሆነ ብሔረሰብ ለክልል ምክር ቤቶች ሲያስመርጥ ከክልሉ ውጭ ያሉ የብሔረሰብ አባላት እንዲመርጡ የደነገገው እንዲሁም ለዚህ ብሔረሰብ አባላት ለብቻው የተለየ አሰራር መተግበር የሚያስችል በሕገ መንግሥቱ ላይ ያለ ድንጋጌ በምርመራው ቦርዱ ያገኘው ነገር የለም" ብሏል።

የሐረሪ ክልል ብሔራዊ ጉባኤ ሚያዝያ 3/2013 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እንደማይቀበል አስታውቆ ነበር።

"ምርጫ ቦርድ ይህንን የመወሰን ስልጣን የለውም" የሚሉት አቶ አብዱልሃኪም እንደ ምክንያትነት የሚያቀርቡትም የሽግግር መንግሥቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወሰነውን ውሳኔና የክልሉን ሕገ መንግሥት በመጥቀስ ሲሆን "በሕግ የተደነገገ ነው" ይላሉ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ1987 ውሳኔ ባልተሻረበት ሁኔታ የክልሉ ሕገ መንግሥት በግልፅ ባስቀመጠበት ሁኔታ "እነዚህን ሕጎች መፃረሩ ከአንድ ትልቅ ተቋም የሚጠበቅ አይደለም" ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ምርጫ ቦርዱ የሽግግር መንግሥት ተወካዮች ምክር ቤት የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ከክልሉ ውጭ ነዋሪ በሆኑ የብሔረሰቡ አባላት ይመረጣል የሚለውን ውሳኔ የሚደግፍ ሕገ መንግሥታዊ አንቀፅ አለመጠቀሱን ምርጫ ቦርድ ገልጿል።

ይህንን በተመለከተም አቶ አብዱልሃኪም እንደሚሉት ምርጫ ቦርድ የአገሪቱንና የክልሎችን ሕገ መንግሥት መሰረት ባደረገ መልኩ እንደሚሰራ ጠቅሰው፤ አንዳንድ የፌደራል ሕገ መንግሥት ላይ ያልተጠቀሱ ጉዳዮች በክልል ሕገ መንግሥቶች ላይ በዝርዝር ሊቀመጡም እንደሚችሉ ይናገራሉ።

እንደ ምሳሌነትም የደቡብ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤትን ይጠቅሳሉ። የብሔረሰቦች ምክር ቤት በፌደራል ሕገ መንግሥት ባይቀመጥም በክልሉ ሕገ መንግሥት የተቀመጠና ምርጫ ቦርድም ይህንኑ መነሻ አድርጎ ነው ምርጫውን እያስፈፀመ ነው ያለው ይላሉ።

ቦርዱ የክልሎችን ሕገ መንግሥቶች ባከበረ መልኩ ነው ሲሰራ የነበረው። ከዚህም በተጨማሪ ምርጫ ቦርድ በስድስተኛውም የአገር አቀፍ ምርጫ የምርጫ ክልሎችን (ጣቢያዎችን) ሲያቋቁም መነሻው የፌደራል እንዲሁም የክልሉ ሕገ መንግሥት እንደሆነ ያወሳሉ።

ምርጫ ቦርድ ከዚህም በተጨማሪ መጋቢት 6/1987 የሽግግር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 102ኛ መደበኛ ስብሰባ ውሳኔ የምክር ቤቱ ማህተም ያረፈበት ስላልሆነ ውሳኔው አግባብ አለመሆኑ አመልካች ነው፤ እንዲሁም የሰነዱን ተቀባይነት ችግር ላይ ጥሎታል ብሏል።

ሰነዱ ማህተም የለውም ወይ? የሚል ጥያቄ ከቢቢሲ የቀረበላቸው አቶ አብዱልሃኪም በበኩላቸው ለምርጫ ቦርድ ስለቀረቡ ሰነዶች ምላሽ አላቸው።

ስድስት ገፆች ያሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ከመሸኛ ደብዳቤ ጋር የተያያዘ ሲሆን መሸኛ ደብዳቤው ላይ ቀን፣ ቁጥርና ማህተም አለው። ከዚህም በተጨማሪ በጊዜው የነበረው ኮሚቴ ያቀረበው ሪፖርት 17 ገጽም ተያይዟል።

የተያያዙት ሰነዶች ላይ ምንም አይነት ማህተም እንደሌለው የሚናገሩት አቶ አብዱልሃኪም "በዚህኛው ውሳኔ ብቻ የተፈጠረ ነው? ወይስ ከዚህም በፊት የነበሩ ውሳኔዎች ተመሳሳይ ሂደት ነው ያላቸው? አሰራሩን መፈተሽ ያለበት ምርጫ ቦርድ ነው" ይላሉ።

እንደ አቶ አብዱልሃኪም ምርጫ ቦርድ ሰነዶቹ ማህተም የላቸውም ከተባለ ውሳኔውን ከማሳለፉ በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት አቅርቦ ጠይቆ፣ ፈትሾና መርምሮ በዚያ መሰረት መወሰን ይገባው ነበር ይላሉ።

"በዚያ መነሻነት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ መሆን አለመሆኑን ሲያረጋግጥላቸው ምላሹን ከሰሙ በኋላ ውሳኔ መወሰን በተገባቸው ነበር። ተቋማዊ አሰራር ያልተከተለ ነው" ይላሉ።

የሐረሪ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰነዶቹ ተቀባይነት እንደሌላቸው ጠቅሶ አቤቱታ ማስገባቱን ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበኩሉ የ1987 ሰነዶችን መነሻ በማድረግ የራሱንም ውሳኔ ጨምሮ ክልሉ ያቀረበለትን ደብዳቤ ጨምሮ ወደ 39 ገጽ በራሱ ማህተም ለምርጫ ቦርድ መላኩንም ይናገራሉ።

ምርጫ ቦርድ በበኩሉ "የወሰንነውን ውሳኔ መልሰን የምናይበት አግባብ ስለማይኖር ሌላ ውሳኔ የሚሰጥ አካል ውሳኔ የሚሰጥበት መንፈስ ያለው አይነት ምላሽ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ቦርድ ልኳል" ይላሉ።

በሕዝብ ተወካዮች በኩል ያለው ጉዳይ በራሱ እየሄደ ቢሆንም በፍርድ ቤትም በኩል እንዲወሰን በመሻት ክልሉ መክሰሱን ይናገራሉ።

በሌላ በኩል አቶ አብዱልሃኪም ምርጫ ቦርድ ባለፉት አምስት ብሔራዊ ምርጫዎች ይጠቀምበት የነበረውን መመሪያ "በዚህ ውሳኔ እውቅናን ነፍጓል" ቢሉም ቦርዱ በበኩሉ መመሪያውን ከጽህፈት ቤቱ ማግኘት እንዳልቻለ ገልጿል።

ዝርዝር መመሪያው የ1987ቱን የተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት ያደረገና የባለፉትንም አምስት ምርጫዎች በዚሁ መልኩ ሲያስፈጽም የነበረ መሆኑ ተጠቅሷል።

አቶ አብዱልሃኪም በዚህ አባባል አይስማሙም "ሥራ ላይ ያሉት መመሪያዎች የእኔ አይደሉም፤ አላውቃቸውም ማለቱ ትክክል አይደለም" ይላሉ።

ነገር ግን ቦርዱ በፃፈው ደብዳቤ እንደጠቀሰው ምንም እንኳን ለሐረሪ ጉባኤ የሚመረጡ ተወካዮች ከክልሉ ውጭ ባሉ የብሔረሰብ አባላት ምርጫ ቦርድ ሲያስመርጥ ቆይቶም ከሆነ ሕገ መንግሥታዊና የምርጫ ሕጉ መሰረት የሌላቸውን አሰራሮች እንደማይከተል አስታውቋል።

ቦርዱም በምርጫ ማሻሻያው እንዲህ አይነት ልምዶች እንዲቀሩ እየሰራ ነው ብሏል።

ምንም እንኳን ላለፉት አስርት ዓመታት የተተገበረ ጉዳይ ነው ብሎ ቦርዱ ቢወስን "ሌሎች አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ብሔረሰቦች ከክልላቸው ውጭ ያሉ አባሎቻቸው በምርጫው እንዲሳተፉ ቢጠይቁ ቦርዱ ልፈፅም አልችልም ቢል የቦርዱን በፍትሐዊነት እና በገለልተኛነት ምርጫን የማስተዳደሩ ጉዳይ አደጋ ላይ እንዲወድቅ ያደርጋል" ይላል።

አቶ አብዱልሃኪም በበኩላቸው "ባለው ነገር ላይ መጨመር ነው እንጂ ሌሎች አናሳ ብሔሮችም እንዲህ አይነት የመብት ጥያቄ ቢጠይቁኝ መመለስ ስለማልችል የናንተንም በዚህ ወቅት ማስተናገድ አልችልም የሚለው ትክክል አይደለም" ይላሉ።

ኢትዮጵያም ውስጥ የመከላከያ ሰራዊት፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በየአካባቢያቸው የሚመርጡበት አሰራር እንዳለና በሌሎች አገራትም እንዲሁ በየኤምባሲዎቻቸው የሚመርጡበት ሁኔታ ልምድ መኖሩን ጠቅሰው የ "ሃረር የተለየ እንዳዳልሆነ" ይናገራሉ።

"አገራችን ላይ ሕጉ አለ፤ ይሄንንም በተመለከተ ምርጫ ቦርድ መመሪያ ያወጣል የሚል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ አለ፤ የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅም ላይ አለ" ይላሉ አቶ አብዱልሃኪም።

"ያንን ከመተግበር አንፃር የኢኮኖሚ አቅማችንና የእድገታችን ደረጃ ገና ስለሆነ ይሄ የመተግበርና ያለ መተግበር ጉዳይ ነው" ሲሉ ያክላሉ።

የሐረሪ ሕዝብ ክልል ምክር ቤት ከሁለት ጉባኤዎች የተዋቀረ ሲሆን እነዚህም የሕዝብ ተወካዮች ጉባኤና የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ናቸው።

የሕዝብ ተወካዮች ጉባኤ 22 አባላት ሲኖሩት የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ደግሞ 14 የሐረሪ ብሔረሰብ አባላትን የያዘ ነው።

ምርጫ ቦርዱ በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ የሐረሪ ተወላጆች በጉባኤው ምርጫ መሳተፍ አይችልም የሚል ውሳኔን ቢያስተላልፍም የሐረሪ ጉባኤ 14 መቀመጫ በሐረሪ ብሔረሰብ አባላት የመያዙን ሁኔታ አይቀይረውም።

ጉባኤው ከሐረሪዎች ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ በተያያዘ ማንነትና ህልውናቸው እንዲቀጥል ከማድረግ ጋር የተያያዙ ውሳኔዎችን የሚያስተላልፍና በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው የሚኖሩ የሐረሪ ተወላጆችን የሚያስተሳስር እንደሆነ አቶ አብዱልሃኪም ይናገራሉ።