የደኅንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል፡ ብሔራዊ ደኅንነትን በሚፈታተኑ ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ተጀምሯል

የፎቶው ባለመብት, Federal Police, END, NISS, INSA
የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነትን በሚፈታተኑ ጉዳዮች ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የደኅንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።
ግብረ ኃይሉ ይህንን ያለው የአገሪቱ የጸጥታና የደኅንነት ተቋማት የጸረ-ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ እንደማይታገስ የገለጸበትን መግለጫ አርብ ምሽት ባወጣበት ጊዜ ነው።
ጨምሮም "ሕዝባዊ እምቢተኝነትን በመፍጥር አገሪቱን ወደ ግጭትና ትርምስ ውስጥ ለመክተት የውስጥና የውጭ ኃይሎች ተጣምረው እንቅስቃሴዎች እያደረጉ መሆኑን የሚያመለክት በበቂ መረጃና ማስረጃ አረጋግጫለሁ" ሲል የደኅንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይሉ አስታወቋል።
ይህ የደኅንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ከአገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና ከመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የተውጣጣ ነው።
መንግሥት አግባብ በሆነ መልኩ ከማንነት፣ ከአስተዳደር ወሰንና ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ለመመለስ እየሠራ በሚገኝበት ወቅት እነዚህ ኃይሎች ተጣምረው አገሪቱን ወደ ትርምስ ለማስገባት ጥረት እያደረጉ ነው ብሏል።
ግብረ ኃይሉ ይህን ተልዕኮ ለመፈጸም የተዘጋጁ ሰነዶችና የጥፋቱን ተዋናይ አካላትንም የሚግልጽ መረጃ በደኅንነትና በጸጥታ መዋቅሩ እጅ መግባቱንም ጠቁሟል።
የቅርብ ጊዜያት ግድያ እና መፈናቀል
ግብረ ኃይሉ የጥፋት ኃይሎች ሰሞኑን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መንግሥትን ያሳዘን ሕዝብን ያስቆጣ በንጹሃን ዜጎች ላይ ሞትና መፈናቀል ፈጽመዋል ብሏል።
በዚህም መግለጫው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረስብ አስተዳደር አካባቢ በተፈፀሙ ጥቃቶች የንጹሃን ዜጎች ህይወት ማለፉን፣ ንብረት መውደሙን እንዲሁም በርካታ ሰዎች ከቀዬቻው መፈናቀላቸውን አውስቷል።
ለዚህም ክስትት "ከውስጥና ከውጭ የተደራጁ የጥፋት ኃይሎች" ተጠያቂ ናቸው በማለት በመግለጫው ላይ ከሷል።
በተጨማሪም በአማራ ክልል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የቅማንት ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃትም የፀጥታ አካላትን ጨምሮ የንፁሃን ዜጎች ህይወት ማለፉን እና ንብረት መውደሙን መግለጫው አትቷል።
ከዚህ በተጨማሪም በአፋርና በሱማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የንጹሃንን ሕይወት የቀጠፉ ግጭቶች ማጋጠማቸውን በመግለጫው ተጠቅሷል።
ሕዳሴ ግድብ
የግብረ ኃይሉ መግለጫ "በቅንጅት የሚሠሩት የውስጥና የውጭ ጸረ ሰላም ኃይሎች የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በታለመለት ጊዜ እንዳይካሄድና እንዲስተጓጎል የጉሙዝ ታጣቂዎችን አሰልጥነውና አስታጥቀው በአካባቢው አሰርማርተዋል" ይላል።
ይህንንም ተከትሎ የእነዚህን ኃይሎች ሴራ ለማክሸፍ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የደኅንነት ግብረ ኃይሉ መግለጫ አመልክቷል።
የግብረ ኃይሉ መግለጫ የኦነግ-ሸኔ ታጣቂ ቡድን የመንግሥትን ትኩረት ለመበተን በንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያዎችን እና ጥቃቶችን እንደሚፈጽም ገልጿል።
"ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት ያለው የኦነግ-ሸኔ ታጣቂ ቡድንን . . . ሙሉ በሙሉ ለማስቆም በቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃም ተጠናክሮ መቀጠሉን የጋራ ግብረ ኃይሉ ማሳወቅ ይወዳል" ብሏል።
ግብረ ኃይሉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎችንና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ አካላትን ጭምር በመጠቀም የአገር ሕልውናን አደጋ ላይ ለመጣል እየተረባረቡ መሆኑን ሕዝቡ ሊገነዘብ ይገባል ሲል አሳስቧል።
ግብረ ኃይሉ ይህንን መግለጫ ያወጣው አገሪቱ ብሔራዊ ለማካሄድ በተዘጋጀችበት ጊዜ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ከባድ ጥፋትን ከፈጸሙ በኋላ ነው።
በተለይ በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ባለፈው ሳምንት በተፈጸመው ጥቃት አስካሁን ቁጥሩ በውል ያልተገለጸ ሰው ህይወት ያለፈ ሲሆን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ለመፈናቀል መዳረጋቸውን የአካባቢው ባለሥልታናት ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ በአማራ ክልል ውስጥ ባሉ አካባቢዎች እየተጠናቀቀ ባለው ሳምንት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለተከታታይ ቀናት በሚፈጸሙ ጥቃቶች በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመውን ግድያ አዕተቃወሙ ነው።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከልና ካማሺ ዞኖች፣ በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋና በኦሮሞብሔረሰብ ዞን በርካታ ሰዎችን ለህልፈት የዳረጉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በታጣቂዎች መፈጸሙ ይታወሳል።












