በአዲስ አበባ በጅምር ላይ የነበረ ህንጻ ተደርምሶ የሦስት ሰዎች ሕይወት አለፈ

በአዲስ አበባ ከተማ በጅምር ላይ የነበረ ህንጻ ተደርምሶ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተነገረ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ ለቢቢሲ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ካዛንቺስ ጁፒተር ሆቴል ፊት ለፊት ነው።
እንደ ቡድን መሪው ገለጻ ከሆነ አደጋው ትላንት ሚያዝያ 15 2013 ዓ.ም. ከጠዋቱ 5 ሰዓት አከባቢ ነበር የደረሰው።
ለሦስት ሰዎች ሕልፈት ምክንያት የሆነው አደጋው የደረሰው ጅምር ላይ ህንጻ በመደርመሱ መሆኑን ጠቁመው ለጅምር ህጻው መደርመስ ግን እስካሁን መንስኤው አልተለየም ብለዋል።
ሕይወታቸው ያለፈው ሦስቱ ግለሰቦች በ23 እና የ24 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች እንደነበሩ አቶ ጉልላት ገልጸዋል።
በህንጻው መደርመስ ሕይወታቸው ካለፈው ወጣቶች በተጨማሪ አራት ሰዎች ጉዳት የደረሰ ሲሆን ሦስቱ ቀላል፤ አንደኛው ላይ ግን ከባድ ጉዳት እንደደረሰ አቶ ጉልላት አስረድተዋል።
"በሥራው ላይ ተሰማርተው የነበሩ 112 ሠራተኞች ነበሩ" ያሉት አቶ ጉልላት "ከአዲስ አበባ ፖሊስ እና ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመተባበር 109 ሰዎችን ማትረፍ ተችሏል" ብለዋል።
አደጋውን ለመቆጣጠር 35 የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች፤ 3 ከባድና 4 ቀላል ተሽከርካሪዎች እና 3 አምቡላንሶች ተሠማርተዋል። አደጋውን ለመቆጣጠርም 2 ሰዓታት የፈጀ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በአደጋው 100 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ጉዳት ሲደርስበት 2 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ንብረት ለማትረፍ መቻሉን አቶ ጉልላት ተናግረዋል።
ሰፊ የግንባታ ሥራዎች በሚከናወኑባት አዲስ አበባ ከተማ በጥንቃቄ ጉድለት ምክንያት ከዚህ ቀደ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ሲደርስ ተስተውሏል።












