አሜሪካ ኢትዮጵያን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ልዩ መልዕክተኛ ሾመች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ በኢትዮጵያና በአካባቢዋ ባሉ አገራት ውስጥ ስላሉ ጉዳዮች በቅርበት የሚከታተሉላትን ልዩ መልዕክተኛ መሾሟን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታወቀ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ይፋ እንዳደረጉት በተለይ ኢትዮጵያ ለምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጄፍሪ ፌልትማንን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አድርገው መሾማቸውን ገልጸዋል።
አሜሪካ አዲስ የሾመቻቸው የአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን በተለይ በኢትዮጵያና በዙሪያዋ ስላሉ ሁኔታዎች የተለየ ትኩረት እንደሚሰጡ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ አመልክቷል።
በዚህም መሠረት በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ግጭት ጨምሮ በአገሪቱ ያለው ተለዋወጭ ሁኔታ፣ ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር አለመግባባት እንዲሁም በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለው ውዝግብ የልዩ ልዑኩ ቀዳሚ ሥራ እንደሚሆን ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በመግለጫው ላይ እናዳለው ቁልፍ በሆነው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ "በአሁኑ ጊዜ መሠረታዊ ለውጥ እየተካሄደበት ነው" ብሏል።
የአዲሱን ልዩ መልዕክተኛ አስፈላጊነት በተመለከተም በአካባቢው "በትውልዶች ውስጥ አንድ ጊዜ ለሚያጋጥም የለውጥ ዕድል አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የግጭት ስጋትን ለማስቀረት በከፍተኛ የሥልጣን ደረጃ የአሜሪካ ተሳትፎ አስፈላጊ" በመሆኑ ነው ብሏል።
ይህ የልዩ መልዕክተኛ ሹመት የባይደን አስተዳደር በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን ተያያዥ የሆኑትን ፖለቲካዊ፣ የደኅንነትና የሰብአዊ ጉዳዮች ምፍትሔ እንዲያገኙ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን ለመምራት ያለውን ቁርጠኝነት ያመለክታል ተብሏል።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥና በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ የሰሩት ጄፍሪ ፌልትማን በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ላይ ለረጅም ዘመን ልምድ እንዳላቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም ፌልትማን በርካታ አገራትን ባካተቱ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሚደረጉ ድርድሮችና ሽምግልናዎች ውስጥ የአሜሪካንን ተያያዥ ስትራቴጂን በማስፈጸም ልምድ አላቸው ብሏል ሹመታቸውን ያሳወቀው መግለጫ።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትና በተባበሩት መንግሥት ውስጥ በተለያዩ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ በመሥራት ሠፊ ልምድ እንዳላቸው የሚነገርላቸው የ62 ዓመቱ ጄፍሪ ፌልትማን በዓለም አቀፍ ፖለቲካ የጥናት ተቋማት ውስጥ እጉልህ ሚና አላቸው።
ፌልትማን ማን ናቸው?
ፌልትማን በድርድርና የሽምግልና ጉዳዮች ላይ ጥናትን በማካሄድና በአደራዳሪነትም ከፍ ያለ ልምድ እንዳላቸው ይነገራል።
ፌልትማን በፖለቲካዊና በውጭ ጉዳዳ ፖሊሲዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞውንና የአሁኑን ሊቃነ መናብርት ባን ኪሙን እና አንቶኒዮ ጉቱሬዝን ያማከሩ ሲሆን፤ ለጸጥታው ምክር ቤት በሠላምና በደኅንነት ጉዳዮች ማብራሪያዎችን በመስጠት ይታወቃሉ።
በተባበሩት መንግሥታት ቆይታቸው ወቅትም በልዩ መልዕክተኝነት አገልግለዋል፤ በተጨማሪም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ ለ26 ዓመታት ያገለገሉት ፌልትማን በሌባኖስ፣ በኢራቅ፣ በእስራኤል፣ በቱኒዚያ፣ በሃንጋሪና በሄይቲ ከፍተኛ ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል።
አሜሪካ በትግራይ ክልል ውስጥ ወታደራዊ ግጭት ከመከሰቱ በፊት በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚደረገው ድርድር ውስጥ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማካይነት ጭምር ስትሳተፍ መቆየቷ ይታወሳል።
በተለይ በትግራይ ክልል ውስጥ የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ ከፍተኛ የአገሪቱ ባለስልጣንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ ከሌሎች የኢትዮጵያው ባለሥልጣናት ጋር በተደጋጋሚ መወያየታቸው ሲነገር ቆይቷል።
ባለፈው መጋቢት ወርም የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ሴናተር ክሪስ ኩንስ ለቀናት የቆየ ጉብኝት በአዲስ አበባ አድርገው ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር ተወያይተው ነበር።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ትግራይ ውስጥ ስላለው ግጭትና የሰብአዊ ጉዳዮች ሁኔታ በተደጋጋሚ ጠንከር ያሉ መግለጫዎችና ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሞ ማሰማቱ ይታወሳል።












