የዘር ጭፍጨፋ ወይም ጄኖሳይድ ምንድን ነው?

ፍርድ ቤቱ በሩዋንዳ ጉዳይ ፍርድ ያሳለፈው 85 ሰዎች ላይ ሲሆን፤ ከነዚህ 29ኙ የተፈረደባቸው በዘር ጭፍጨፋ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዘር ጭፍጨፋ (ጄኖሳይድ) ድርጊት እጅግ ከፍተኛው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ነው። አንድ ቡድን ላይ አነጣጥሮ በርካታ አባላቱን መፍጀት በሰው ልጆች ታሪክ አሰቃቂ ጠባሳ ትቶ ያለፈባቸው ወቅቶች በክፉ ይታወሳሉ።

በ1940ዎቹ (እአአ) ናዚዎች አይሁዳውያንን በጅምላ የጨፈጨፉበት ወቅት ይጠቀሳል።

ከሕግ ትርጓሜ አንጻር የዘር ማጥፋት የሚባሉት ምን አይነት ጭፍጨፋዎች ናቸው? የሚል ጥያቄ ይሰነዘራል። የዘር ማጥፋት የሚለው አገላለጽ የሚሠራው በየትኞቹ ሁኔታዎች ነው? የሚለውም እንዲሁ።

የዘር ጭፍጨፋ ወይም በእንግሊዘኛው ጄኖሳይድ [Genocide] የሚለው ቃል፤ እንደ አውሮፓውያኑ በ1943 በአይሁድ ፓላንዳዊው ጠበቃ ዶ/ር ራፋኤል ለምኪን ነው ጥቅም ላይ የዋለው።

ቃሉ የግሪኩ ጄኖስ [Genos] እና የላቲኑ ሳይድ [Cide] ቃላት ጥምረት ነው። ጄኖስ ዘር ወይም ብሔር ማለት ሲሆን ሳይድ ደግሞ ግድያን ያመለክታል።

ከአንድ ወንድሙ ውጪ መላ ቤተሰቡን በአይሁዳውያን ላይ በተፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋ (ሆሎኮስት) ወቅት ያጣው ዶ/ር ራፋኤል፤ የዘር ጭፍጨፋ በዓለም አቀፍ ሕግ ወንጀል ተብሎ እንዲመዘገብ ንቅናቄ አድርጓል።

ንቅናቄው፤ የተባበሩት መንግሥታት የዘር ጭፍጨፋን በሚመለከት ስምምነት ላይ እንዲደርስ አስችሏል። ይህ የሆነው በአውሮፓውያኑ በ1948 ሲሆን፤ ስምምነቱ መተግበር የጀመረው ከሰኔ 1951 ወዲህ ነው።

የስምምነቱ ሁለተኛ አንቀጽ የዘር ጭፍጨፋን የሚተረጉመው "የአንድ አገር፣ ብሔር፣ ዘር ወይም ሐይማኖት አባላትን ሙሉ በሙሉም ይሁን በከፊል ለማጥፋት የተቃጣ" ብሎ ነው።

ይህም የአንድ ቡድን አባላትን መግደል፣ ከፍተኛ የሆነ አካላዊ እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ማድረስን ያካትታል።

በተጨማሪም የቡድኑ አባላት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲጠፉ ማሴር፣ የቡድኑ አባላት ልጆች እንዳይወልዱ ማድረግ እና ልጆችን በግዳጅ ወደ ሌላ ቡድን መውሰድን ያካትታል።

የተባበሩት መንግሥታት ስምምነትን የተቀበሉ አገራት የዘር ጭፍጨፋን የመግታት እና የዘር ጭፍጨፋ ሲፈጸም የመቅጣት ግዴታ አለባቸው።

በእርግጥ ይህ የተባበሩት መንግሥታት ስምምነት ከጸደቀ በኋላ የተለያዩ ትችቶች ተሰንዝረውበታል። በዋነኛነት የቀረበው ቅሬታ ስምምነቱን በልዩ ሁኔታዎች ውስጥ ለመተግበር አስቸጋሪ መሆኑ ነው። የዘር ጭፍጨፋ ትርጓሜ ጠባብ ነው ብለው የሚተቹ አሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ የዘር ጭፍጨፋ የሚለው ገለጻ በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ መዋሉ ቃሉ ዋጋ እንዲያጣ አድርጎታል የሚል መከራከሪያ ይነሳል።

ሴሬብሬኒሳ ውስጥ የተገደሉ ከሰባት ሺህ በላይ ሙስሊሞች ስም ዝርዝር

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ሴሬብሬኒሳ ውስጥ የተገደሉ ከሰባት ሺህ በላይ ሙስሊሞች ስም ዝርዝር

ይህንን ስምምነት በተመለከተ የሚነሱ ትችቶችን በዝርዝር እንመልከት፦

  • ስምምነቱ የፓለቲካ እና ማኅበራዊ ቡድን አባላት ላይ ያነጣጠረ ጥቃትን አያካትትም።
  • የቃሉ ትርጉም የሚያተኩረው ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ቀጥተኛ ጥቃትን ብቻ ስለሆነ እነዚህ ሰዎች የሚኖሩበት አካባቢ ወይም ባህላዊ መገለጫዎቻቸው ላይ የሚቃጣ ጥቃትን ችላ ይላል።
  • አንድን ቡድን ለማጥፋት ታስቦ የተሰነዘረ ጥቃት የሚለውን ከጥርጣሬ ባለፈ በማስረጃ ለመደገፍ ያስቸግራል።
  • የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት ሌሎች የድርጅቱ አባል አገሮችን ጥፋተኛ ለማለት ወይም ጣልቃ ለመግባት ቆራጥ እርምጃ አይወስዱም። እንደ ምሳሌ የሩዋንዳ ዘር ጭፍጨፋን መጥቀስ ይቻላል።
  • ስምምነቱ ከግምት ያስገባቸው መለኪያ ነጥቦችን የሚያብራራ ዓለም አቀፍ የሕግ አካል የለም። በእርግጥ የተባበሩት መንግሥታት የጦር ወንጀሎች ልዩ ፍርድ ቤት ክስ በመጀመሩ ነገሮች እየተለወጡ ነው።
  • የዘር ጭፍጨፋ የሚባለው ምን ያህል ሰው ሲገደል ነው የሚለውን ለመተርጎም ወይም ለመለካት አዳጋች ነው።

ከላይ የተሰነዘሩት ትችቶች እንዳሉ ሆነው፤ የዘር ጭፍጨፋ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው የሚል ነጥብ የሚያነሱ አሉ።

ስለ ሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ መጽሐፍ ያሳተሙት አለን ደስታቼ "የዘር ጭፍጨፋ ከሌሎች ወንጀሎች የሚለየው በኢላማው ነው" ይላሉ።

የዘር ጭፍጨፋ ከሌሎች ሰብዓዊ መብትን የሚጥሱ ወንጀሎች የሚለየው አንድን ቡድን ለማጥፋት ታስቦ የሚደረግ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

"የዘር ጭፍጨፋ እጅግ የከፋ ወንጀል ነው" በማለትም ያክላሉ።

ቃሉ ጥቅም ላይ የሚውልባቸው ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው? የሚለው ላይ ግን ጥያቄ አላቸው። በተመሳሳይ ጥያቄ የሚነሳበት ቃል "ፋሺስት" ነው።

በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ የሰብዓዊ መብት ፖሊሲ ማዕከል የቀድሞ ዳይሬክተር ማይክል ኢግናቲፍ ቃሉ ሁሉንም አይነት ጥቃቶች ለመግለጽ ሲውል እንደሚስተዋል ይናገራሉ።

"ለምሳሌ ባርነት የዘር ጭፍጨፋ ነው ይባላል። ባርነት የሚኮነን ድርጊት ሲሆን፤ ሰዎችን የማጥፋት ሳይሆን የመበዝበዝ ሥርዓት ነበር" ይላሉ።

ባለፈው ምዕተ ዓመት የተፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ ሆሎካስት ብቻ ነው የሚሉ አሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP

ምን ያህል የዘር ጭፍጨፋዎች ተፈጽመዋል?

የዘር ጭፍጨፋን የተመለከቱ የተለያዩ ትርጓሜዎች አሉ። ይህ ልዩነት በ20ኛው ክፍለ ዘመን ምን ያህል የዘር ጭፍጨፋ ተፈጽሟል? የሚለው ላይ አለመስማማትን ፈጥሯል።

ባለፈው ምዕተ ዓመት የተፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ ሆሎኮስት ብቻ ነው የሚሉ አሉ። በሌላ በኩል የ1948ቱን የተባበሩት መንግሥታት ስምምነት በመጥቀስ ሦስት የዘር ጭፍጨፋዎች ተፈጽመዋል ይባላል።

እነዚህ ሦስት የዘር ጭፍጨፋዎች ከ1915 እስከ 1920 በኦቶማን ቱርክ፤ አርመናውያን ላይ የተፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ፣ ከስድስት ሚሊዮን በላይ አይሁዳውያን የተፈጁበት ሆሎኮስት እና ወደ 800,000 ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች የተፈጁበት የ1994ቱ የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ናቸው።

በቅርቡ የዘር ጭፍጨፋ ተብለው የተመዘገቡም አሉ። አንደኛው በ1995 በቦስንያ የተፈጸመው ነው። የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ዓለም አቀፍ የወንጀል ልዩ ፍርድ ቤት ነው የዘር ጭፍጨፋ ብሎ የፈረጀው።

ሌላው በዩክሬን ከ1932 እስከ 1933 በሶቭየት አማካይነት የተከሰተው ሰው ሠራሽ ረሀብ ነው። የ1975ቱ ኢንዶኔዥያ በምሥራቅ ቲሞር ላይ የጸፈመችው ወረራ፣ 1.7 ሚሊዮን ሰዎች በግድያ፣ በረሀብና በጉልበት ብዝበዛ ያለቁበት የ1970ዎቹ የካምቦዲያ በኬምር ሩዥ የተፈጸመው ግድያ ይጠቀሳሉ።

እነዚህ ካምቦዲያውያን ኢላማ የተደረጉት በፖለቲካዊ አቋማቸው ወይም ማኅበረሰቡ ውስጥ ባላቸው ቦታ ነው የሚለው ብዙዎችን ያከራክራል። ይህ ማለት ደግሞ ግድያውን ከተባበሩት መንግሥታት የዘር ጭፍጨፋ ትርጓሜ ውጪ ያደርገዋል ማለት ነው።

ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እንደ በአውሮፓውያኑ 2010 በቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር ላይ የእስር ማዘዣ አውጥቷል።

ሰባት ዓመታት በፈጀ ውጊያ በአገሪቱ የዳርፉር ግዛት ውስት 300,000 ሰዎች መሞታቸውና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በመፈናቀላቸው ሳቢያ አልበሽር በዘር ጭፍጨፋ ተከሰዋል።

በ2016 አሜሪካ፤ ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) በኢራቅ እና ኢራን ባሉ ክርስቲያኖች፣ ያዚዲዎችና የሺአ ማኅበረሰብ አባላት ላይ የዘር ጭፍጨፋ ፈጽሟል ስትል ከሳለች።

የዚያን ጊዜው የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ "አይኤስ በመርህ፣ በተግባርና ለራሱ በሰጠው ስም መሠረት ዘር አጥፊ ነው" ብለዋል።

በ2017 ጋምቢያ ለዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት ያስገባችው ክስ ሚያንማር፤ በሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ የዘር ጭፍጨፋ ፈጽማለች ይላል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የሮሂንጋ ሙስሊሞች ከሚያንማር ሸሽተው ባንግላዲሽና ሌሎችም አገሮች ተጠልለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ መገደላቸውም ተዘግቧል።

በ2021 አሜሪካ፣ ካናዳ እና ኔዘርላንድስ በአንድነት ቻይና፤ በዢንዣንግ ውስጥ የዊጋ ማኅበረሰብ ላይ የዘር ጭፍጨፋ ፈጽማለች ሲሉ ከሰዋል። ሌሎች አገራትም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤታቸው አማካይነት ተመሳሳይ ክስ አሰምተዋል።

ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት ቻይና፤ የዊጋ ማኅበረሰብን በግዳጅ በማምከን፣ በጅምላ በማገት፣ ጉልበት በመበዝበዝ፣ በመድፈርና በማሰቃየት ጥቃት አድርሳለች።

እነዚህ ጥቃቶች የዘር ጭፍጨፋ የሚባሉ ቢሆንም ቻይና ክሱን አጣጥላለች።

በኬምር ሩዥ የተገደሉ ሰዎች መታሰቢያ ሙዚየም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኬምር ሩዥ የተገደሉ ሰዎች መታሰቢያ ሙዚየም

የዘር ጭፍጨፋ የፍርድ ሂደት

በዘር ጭፍጨፋ በግንባር ቀደምነት ፍርድ ቤት የቀረበው ሁቱ እና የሩዋንዳዋ ታባ ከተማ ከንቲባ የነበረው ዣን ፖል አካይሱ ነበር።

ጉዳዩን የዳኘው ልዩ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት መስከረም 2/1998 ግለሰቡን በዘር ጭፍጨፋና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች ፈርዶበታል።

ፍርድ ቤቱ በሩዋንዳ ጉዳይ ፍርድ ያሳለፈው 85 ሰዎች ላይ ሲሆን፤ ከእነዚህ 29ኙ የተፈረደባቸው በዘር ጭፍጨፋ ነው።

2010 ነሐሴ ላይ ሾልኮ የወጣ የተባበሩት መንግሥታት ሰነድ እንደሚያሳየው፤ ጥቃት ፈጻሚዎቹ የሩዋንዳ ሁቱዎች ተመሳሳይ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

በ2001 የቀድሞው የቦሲኒያ ጄነራል ራዲስላቭ ክርስቲች በዓለም አቀፉ ልዩ የወንጀል ችሎት የተፈረደበት የመጀመሪያው ሰው ሆኗል።

ጄነራሉ አቤቱታ ያሰማው "የሞቱት ሰዎች ቁጥር 8,000 ነው። ይህም የዘር ጭፍጨፋ አያስብለውም" ብሎ ነበር። 2004 ላይ ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን ውድቅ አድርጎታል።

በ2007 የቀድሞው የቦሲኒያ ሰርብ ኮማንደር ራትኮ ምላዲች በዘር ጭፍጨፋ፣ በጦር ወንጀል እና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተከሶ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።

ይህ ግለሰብ "የቦሲኒያው ጨፍጫፊ" በሚል ይጠራል።

በ2018 ከኬምእ ሩዥ ግድያ ጋር በተያያዘ የ92 ዓመቱ ኑዎን ቺያ እና የ87 ዓመቱ ኪው ሳምፒን በዘር ጭፍጨፋና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተከሰው የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል።