የወር አበባ ፈቃድ የከለከሉት የአየር መንገድ ኃላፊ ተፈረደባቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞ የደቡብ ኮሪያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሴት የአየር መንገዱ ሠራተኞች በሕግ የተፈቀዳላቸውን የወር አበባ ፈቃድ በመከልከላቸው ተቀጡ።
የእስያን አየር መንገድ የቀድሞው ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ኪም ሶ ቼዎን ከ15 የበረራ አስተናጋጀች የቀረበላቸውን 138 የእረፍት ጥያቄዎችን እኤአ ከ2014 እስከ 2015 ባለው ግዜ ውስጥ ከልክለዋል።
ባለሥልጣኑ ተቋሙ ሴት ሠራተኞች በወር አበባ ጊዜያቸው ሊያገኙ የሚገባውን ፈቃድ በመከልከላቸው ጉዳዩ ፍርድ ቤት ቀርቦ 1800 ዶላር እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል።
ኪም በበኩላቸው ፈቃድ ያልሰጡት የበረራ አስተናጋጆቹ በወር አበባ ላይ እንደነበሩ ማስረጃ አላቀረቡም ሲሉ የመከራከሪያ ሃሳብ አቅርበዋል።
በደቡብ ኮሪያ ሴቶች በወር አበባ ወቅት ከፍተኛ ህመም ከተሰማቸው በወር አንድ ቀን እረፍት የመውሰድ መብት ከ1953 ጀምሮ ተረጋግጦላቸዋል።
ነገር ግን በርካታ አጠራጣሪ የእረፍት ጥያቄ ማመልከቻዎች እንደነበሩ ጠቅሰው ሲከራከሩ የነበሩት ኪም፤ ሠራተኞች የወር አበባ እረፍትን ከዓመት በዓሎች እና ከሌሎች ረፍቶቻቸው ጋር አቀራርበው ይጠይቁ ነበር ሲሉም ተናግረዋል።
በጉዳዩ ላይ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን በይግባኝ የተመለከተው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሴቶች በወር አበባ ላይ እንደሚገኙ ማስረጃ መጠየቅ አይገባም ብሏል።
ማስረጃ መጠየቅ የሰብአዊ መብቶቻቸውን ብሎም የግል ምስጢራቸውን የመጠበቅ መብታቸውን ይጋፋል ሲል የስር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አጽንቷል።












