እህል በአፏ የማይዞረው ታዋቂዋ ምግብ አብሳይ

አሚ ሜይሜንት

የፎቶው ባለመብት, AMY MAIDMENT

ሎሬታ ሃርሜስ ለስድስት ዓመታት ምግብ የሚባል ነገር ወደ አፏ አላስጠጋችም። ምግብ ከማብሰል የሚያግዳት ግን አልሆነም።

ሎሬታ የምትሠራው ምግብ ጨው ይብዛው ይነሰው መቅመስ ባትችልም በኢንስታግራም መድረክ በርካታ ወዳጆች አፍርታለች።

ሎሬታ ቀቅላ የጠበሰችውን ድንች በሹካ እየፈረካከሰች እንፋሎቱን ትምጋለች። ሎሬታና እናቷ ጁሊ ይህን ማዕድ በጥንቃቄ ያበሰሉት ምናልባትም ይህ የመጨረሻዋ ይሆናል ብለው አስበው ነው።

በደቂቃዎች ውስጥ አንድ ከበድ ያለ ስቃይ ሆዷን እየቦረቦረ እንደሚገባ ታውቀዋለች። ይህን ለምዳዋለች። እህልና ፈሳሽ ወደ አፏ ሄዱ ማለት ስቃይ ነው ትርፉ።

ነገር ግን የመጣው ይምጣ ብላ ስቃይዋን ተቀብላ በቤተሰቦቿ ኩችና ወንበር ላይ ትውላለች። ኩችናው ማብሰል የተማረችበት አስኳላ ነው።

"ከእናቴና እህቴ ጋር አንድ አፍታ ቁጭ ብሎ መመገብ የሚሰጠው ደስታ ለየት ያለ ነው።"

ጊዜው በፈረንጆቹ 2015 ነበር። የ23 ዓመቷ ሎሬታ ለዓመታት በፈሳሽ መልክ በሚሰጣት ምግብ ነው የምትንቀሳቀሰው። ቤተሰቦቿ ለእራት ጠረጴዛ ሲከቡ እሷ ተለይታ ክፍሏ ውስጥ ከመቀመጥ ያለፈ ዕጣ አልነበራትም።

በነጭ ሽንኩርትና ሎሚ ያበደውን የዶሮ ሥጋ አንስቶ መግመጥ ይቅርና ቢላና ሹካ ማንሳት ራሱ ብርቅ ነው የሚሆንባት።

ነገር ግን ይኸው ዛሬ አንድ ጊዜ እንኳ ከቀረበላት ማዕድ ላይ ምግብ አንስታ እንድትበላ ሆነች። ይህን ያደረገው አንድ ባለሙያ ነው። ባለሙያው ሎሬታ ለምን ምግብ ስትበላ እንደሚያማት፣ ለምንስ ሽንት ቤት መጎብኘት እንደማትችል ለመመርመር ነው ዕቅዱ።

ሎሪታ

የፎቶው ባለመብት, LORETTA HARMES

ሎሬታ የዚያን ቀን ጠዋት ለንደን ወደ ሚገኘው ቅዱስ ማርቆስ ሆስፒታል አቅንታ በአፍንጫዋ ወደታች በተላከ አንድ ቀጭን ቱቦ የትንሹ አንጀቷን ጤንነት ተመርምራ መጥታለች።

ሎሬታ ጨቅላ ሳለች በቴሌቪዥን መስኮት የሚታዩ የምግብ ዝግጅት ቅንብሮችን አስመስላ ለቤተሰቦቿ ታቀርብ ነበር። ምግብ ማብሰል መክሊቷ ነው ብንል ማጋነን አይሆንም።

የ11 ዓመት ታዳጊ ሳለች ዘወትር ማክሰኞ እናቷ ከሥራ አምሽታ እንደምትመጣ ስለምታውቅ እራት አሰናድታ ትጠብቃት ነበር።

እናቷ ጁሊ እንደምትለው ሎሬታ ማብሰል የጀመረችው በቲማቲም ስልስ የተቀመመ ፓስታ በመሥራት ነው። ነገር ግን ትንሽ ቆይታ ከበድ ያሉ ምግቦችን ማሰናዳት ተያያዘችው።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እየተከታተለች ሳለ የምግብ ማብሰል ውድድር ላይ ተሳትፋ አሸንፋለች። ከትምህርት ቤት አልፋ በሌሎች ውድድሮች ላይ ታላላቆቹን ሳይቀር ረትታ ዋንጫ ይዛ መጥታለች።

"የሎሬታ ትልቁ ብቃቷ ኩችና ውስጥ ባለው ነገር የሆነ ምግብ መሥራት መቻሏ ነው" ትላለች እናቷ ጁሊ።

15 ዓመት ሲሞላት የምግብ መብላት መመሰቃቀል የሚያስከትለው 'ኢቲንግ ዲስኦርደር' የተሰኘው በሽታ አገኛት። ነገር ግን እሷ እንደምትለው በሽታው ከአንድ ዓመት በላይ አልቆየም።

ቢሆንም በታዳጊነት ዘመኗ የምግብ አለመፈጨት በጣም ያስቸግራት እንደነበር ታስውሳለች። ይህ ምግብ በበላች ቁጥር የሚጎረብጣት ስሜት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ መጣ።

የሆነ ሆኖ ይህን ስሜት እየታገለች ምግብ ማብሰሏንና መመገቧን ቀጠለች።

ሎሬታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንደጨረሰች ለንደን ውስጥ ያለ አንድ ትልቅ የምግብ ዝግጅት ጥበብ ኮሌጅን ተቀላቀለች።

ነገር ግን የሦስቱን ዓመት ኮርስ መማር የቻለችው ለአንድ ዓመት ብቻ ነው። ለዚህ ተጠያቂው ደግሞ የጤናዋ ሁኔታ ነበር።

አሚ ሜይሜንት

የፎቶው ባለመብት, AMY MAIDMENT

በ19 ዓመቷ ትምህርቷን አቋርጣ፣ ከምትወደው ኩችና ተነጥላ አልጋዋ ላይ ስቃይዋን እያስታመመች መኖር ሆነ ሥራዋ።

በሽታው ሥጋዋን መጦ ከሰውነት ተራ እንድትወጣ አደረጋት። አልፎም የአእምሮ ጤናዋ ተቃወሰ።

ሎሬታ በአንድ ወቅት ክብደቷ ሲለካ መመዘኛው ላይ የሚታየውን ብዙዎች ማመን አልቻሉም። 25 ኪሎ ይላል። ይህ ደግሞ ለሕይወቷ ጭምር አስጊ እንደሆነ ዶክተሯ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል።

ምንም እንኳ ስቃዩ ለጠላቷ የማትመኘው ቢሆንም እየቻለችውን መመገብና ክብደቷን ማስተካከል እንዳለባት አመነች።

ሎሬታ የአመጋገብ መመሰቃቀል ያመጣባትን ጫና ተከትሎ የአእምሮ ጤናዋም ይዳከም ጀመር። በርካታ ጊዜ ራሷን ለማጥፋት ሙከራ እንዳደረገች ትናገራለች።

እርዳታ እንድታገኝ የተላከችበት ካምፕ ውስጥ ስድስት ጊዜ መመገብ ግዴታ ነው። ሦስት ጊዜ ዳጎስ ያለ ምግብ፤ ሦስቱን ደግሞ ብስኩት የመሳሰሉ ቀለል ያሉ ምግቦችን መብላት ግድ ነበር።

ታማሚዎች የቀረበላቸውን ምግብ በተመደበላቸው ደቂቃ የመጨረስ ግዴታ አለባቸው። ሎሬታ ግን ብዙ ጊዜ ራሷን የምታገኘው ምግቡ ላይ ስታፈጥ ምግቡም ሲያፈጥባት ነው።

እሷ ማዕዷን ሳታገባድ ማንም ሰው ከጠረጴዛው ላይ እንዲነሳ አይፈቀድለትም። በዚህ ምክንያት ብዙዎቹ ታማሚዎች ቂም ይቋጥሩባታል።

ሁሉም ታካሚዎች ምግብ ከበሉ በኋላ ለአንድ ሰዓት ያክል ቁጥጥር ይደርግላቸዋል። ምክንያቱ ደግሞ ዞር ብለው ጣታቸውን ከተው እንዳያወጡት በሚል ነው።

ከዓመታት ምርምርና ጥናት በኋላ የሎሬታ ሆድ ዕቃ በግማሽ ከጥቅም ውጭ እንደሆነ ተደረሰበት። በሽታው በዘር የሚመጣ እንደሆነም ሐኪሞች አወቁበት።

ሎሬታ እንድትበላ ማስገደድ ምንም ዋጋ እንደሌለው የተደረሰበት ይሄኔ ነው።

ሎሬታ ከምግብ አለመብላት ጋር ከባድ የራስ ምታት፣ ድካምና የልብ በፍጥነት መምታት ያጋጥሟት ነበር።

ይህ በሽታ እስኪደረስበት ድረስ ከ10 እስከ 14 ዓመት ድረስ ሊወስድበት እንደሚችል ዶክተር አላን ሐኪም ይናገራሉ።

ሎሬታ ምግብ በአፏ ከዞረ ስድስት ዓመታት አልፈዋል። ከዚህ በኋላ ድጋሚ እህልም ሆነ ፈሳሽ ወደ አፏ እንደማታስገባ ታውቀዋለች።

አሁን ምግብ የምታገኘው በቀን ለ18 ሰዓታት አንጠልጥላ በምትዞረው ቱቦ አማካይነት ነው። ቱቦው በደረቷ በኩል ገብቶ ወደ ደም ዝውውሯ በፈሳሽ መልክ ምግብ ያሰራጫል።

ሎሬታ ይህን ሁሉ አልፋ፤ አሁን ምግብ ለማብሰል ያላትን ፍቅር የማትበላውን ኧረ እንደውም የማትቀምሰውን ማዕድ በማሰናዳት እየተወጣች ነው።

የምትሠራውን ምግብ የማትቀምስ አብሳይ መሆኗ በኢንስታግራም ተጠቃሚዎች ዘንድ ታዋቂነትን አትርፎላታል።

ሁሌም ከጎኗ የሆኑት እናቷና እህቷ እንዲሁም አብራት የምትኖረው ባልንጀራዋ የሎሬታን ጣት የሚያስቆረጥሙ ምግቦች በፍቅር ይጎርሳሉ።

ሎሬታ ግን ሕይወቷን በቱቦ በሚተላለፍ ምግብ ትገፋለች።