ቲክቶክ ከህጻናት ላይ ከሚሰበስበው መረጃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ክስ ቀረበበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቲክቶክ የህጻናት መረጃ የሚሰበስብበትንና የሚጠበቀምበትን መንገድ በተመለከ በቀድሞ የእንግሊዝ የህጻናት ኮሚሽነር አን ሎንፊልድ ክስ ቀረበበት።
ክሱ የቀረበው በዩናይትድ ኪንግደም እና አውሮፓ ሕብረት ውስጥ በሚገኙ በሚሊየኖች በሚቆጠሩ ህጻናት ስም ሲሆን ታዋቂው የማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያ ትልቅ ጫና ሊደርስበት እንደሚችል ተገምቷል።
ክሱ ተቀባይነት አግኝቶ ቲክቶክ ጥፋተኛ የሚባል ከሆነ እነዚህ ህጻናት በሺዎች የሚቆጠር ፓውንድ በካሳ መልክ ሊከፈላቸው ይችላል። ቲክቶክ በበኩሉ ክሱ መሰረት የሌለው እንደሆነና እስከ መጨረሻው እንደሚከራከር ገልጿል።
ክሱን የመሰረቱት ጠበቆች እንደሚሉት ቲክቶክ እንደ ስልክ ቁጥር፣ ቪዲዮ፣ አድራሻ እና አሻራ ጭምር ያሉ የህጻናትን የግል መረጃ ያለእውቅናቸው አልያም ያለቤተሰቦቻቸው እውቅና ይወስዳል። መረጃውን ለምን እንደሚጠቀመውም ግልጽ አላደረገም ብለዋል።
ይህንን ተከትሎ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በማጋራት የሚታወቀው ቲክቶክ "የግል መረጃ እና ደኅንነት የድርጅታችን ቀዳሚ ኃላፊነት ነው። ይህንን ለመቆጣጠርም ጠንከር ያሉ ፖሊሲዎች፣ አሰራሮችና፣ ቴክኖሎጂዎች አሉን። ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች የተጠቃሚዎቻችንን መረጃዎች እንጠብቃለን። የቀረበብን ክስ መሰረተ ቢስ ነው፤ እኛም እስከመጨረሻው እንታገለዋለን" ብሏል።
ቲክቶክ በመላው ዓለም እስከ 800 ሚሊዮን የሚደርሱ ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን፤ ቲክቶክን የሚያስተዳድረው 'ባይትዳንስ' የተባለው ድርጅት ባለፈው ዓመት ብቻ በቢሊዮን የሚጠሩ ዶላሮችን አትርፏል። አብዛኛው ትርፉ የተገኘው ደግሞ ከማስታወቂያ ነው።
ክሱ የተመሰረተው ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ መተግበሪያውን ሲጠቀሙ በነበሩ ህጻናት ስም ሲሆን በዚህ ክስ መሳተፍ የማይፈልጉ ህጻናት ያለመካተት መብት አላቸው ተብሏል።
የቀድሞዋ የእንግሊዝ የህጻናት ኮሚሽነር አን ሎንፊልድ ለቢቢሲ ሲናገሩ ምንም እንኳን ሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሰዎችን መረጃ ቢሰበስቡም ቲክቶክ ግን በተለየ መልኩ በከፍተኛ ሁኔታ መረጃ ይሰበስባል ብለዋል።
"በዚህ አስቸጋሪ የወረርሽኝ ወቅት ህጻናት ከጓደኞቻቸው ጋር ለመገናኘት ቲክቶክን በጣም ይጠቀሙ ነበር። ነገር ግን ከአዝናኞቹ ቪዲዮዎችና ዳንሶች ጀርባ ያልታወቀ ተግባር እየተከናወነ ነው።"
የቀድሞዋ ሚኒስትር አክለውም ቲክቶክ የህጻናትን ቤተሰቦች ጭምር ሆን ብሎ እና በተሳካ መልኩ በማሳሳት መረጃ ሲሰበስብ ነበር ብለዋል።
በአውሮፓውያኑ 2019 የቻይናው ድርጅት የህጻናትን መረጃ በአግባቡ ባለመያዝ በሚል ክስ ቀርቦበት በፌደራል የንግድ ኮሚሽን 5.7 ሚሊየን ዶላር ቅጣት ተላልፎበት ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ ቲክቶክ ደቡብ ኮሪያ እና ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የህጻናትን መረጃ ከመሰብሰብ ጋር በተያያዘ ምርምራ ተደርጎበታል።
በዩናይትድ ኪንግደም የመገናኛ ብዙሃንን የሚቆጣጠረው 'ኦፍኮም' የተሰኘው ተቋም በሰራው ጥናት መሰረት በአገሪቱ ቲክቶክን ከሚጠቀሙ ታዳጊዎች መካከል 44 በመቶ የሚሆኑት ከስምንት እስከ 12 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
በቲክቶክ ፖሊሲ መሰረት ግን እድሜያቸው ከ13 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት መጠቀም አይችሉም።
















