ትራምፕ ቻይና ሰራሹ ቲክቶክ ላይ እርምጃ ሊወስዱ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በመጪዎቹ ቀናት በቻይና ሰራሹ ቲክቶክ ላይ እርምጃ ሊወስዱ መሆኑን ማይክ ፖምፔፖ ገለጹ።
የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ማይክ ፖምፔዮ፤ ፕሬዝደንቱ ቲክቶክ ላይ እርምጃ መውሰድ ያስፈለጋቸው የስልክ መተግበሪያው በአሜሪካ ላይ የብሔራዊ ደህንነት ስለጋረጠ ነው ብለዋል።
ቻይና ስሪቱ የተንቀሳቃሽ ምሥል መጋሪያ ድር ቲክቶክ በመላው ዓለም በተለይም በወጣቶች ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ ነው።
የቪዲዮ መጋሪያው መተግበሪያ “ለቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ መረጃ በቀጥታ ከሚያስተላለፉት መካከል ነው” ብለዋል ፖምፔዮ። ዶናልድ ትራምፕም በቀጣዩ ጥቂት ቀናት የቲክቶክን እጣ ፈንታ ላይ ይወስናሉ ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዎ።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም ቲክቶክን በአሜሪካ እንዳይሰራ አግዳለሁ ሲሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል። ቲክቶክ ግን ለቻይና መንግሥት መረጃ እንደማያቀብል እንዲሁም ቁጥጥር እንደማይደረግበት በተደጋጋሚ ሲያስተባብል ቆይቷል።
ፖምፔዮ ለፎክስ ኒውስ ሲናገሩ፤ አሜሪካ የሚሰሩ እና ለቻይና መንግሥት መረጃ የሚያቀብሉ በርካታ ኩባንያዎች አሉ ብለዋል። ኩባንያዎቹ ለአሜሪካ መንግሥት ከሚያቀብሏቸው መረጃዎች መካከል በሰዎች ሰልክ ቁጥር ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙ አድራሻዎች እና ስልክ ቁጥሮች ይገኙበታል።
ትራምፕ ባለፈው አርብ ነበር በአሜሪካ ብቻ 80 ሚሊዮን ወርሃዊ ደንበኞች ያሉትን ቲክቶክን ለመዝጋት ፍጹማዊ ፕሬዝዳንታዊ ሥልጣናቸውን እንደሚጠቀሙ ያስታወቁት።
ባይትዳንስ በሚባል የቻይና ኩባንያ ባለቤትነት የተመዘገበው ይህ የቪዲዮ መጋሪያ በብዛት እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች በሆኑ ወጣቶች ዘንድ ይወደዳል።
ይህ በእንዲህ እያለ የአሜሪካ ግዙፉ ኩባንያ ማይክሮሶፍት ቲክቶክን ለመግዛት እየተነጋገረ እንደሆነ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ተሰምቷል። የማይክሮሶፍት አለቃ ሳትያ ናዴላ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር በጉዳዮ ዙርያ ትናንትና እሑድ መወያየታቸውን ኩባንያው ይፋ አድርጓል።
ቻይናና አሜሪካ ከቅርብ ወራት ወዲህ ከረር ወዳለ የንግድና የዲፕሎማሲ ጦርነት ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል።














