ፌስቡክ የብራዚሉን ፕሬዚዳንት ደጋፊዎች አካውንት እንዲዘጋ ታዘዘ

ፕሬዚዳንት ጄይር ቦልሶናሮና ባለቤታቸው ሚሸል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ ፌስቡክ የፕሬዚዳንት ጄር ቦልሶናሮ በርካታ ደጋፊዎች የፌስቡክ ገፅ እንዲዘጋ ትዕዛዝ አስተላለፈ።

የደጋፊዎች ቡድኑ የተከሰሰው በዳኞች ላይ ሃሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ሲሆን የማህበራዊ ሚዲያ ተቋሙ ፌስቡክ ግን ውሳኔው ከመናገር ነፃነት ጋር የሚፃረር ነው ሲል በጉዳዩ ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቅ አስታውቋል።

ፌስቡክ ኮንግረሱንና ጠቅላይ ፍርድቤቱ እንዲዘጋ ለማድረግ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ለመጥራት አገልግሎት ላይ ውሏል ብሏል- ፍርድ ቤቱ።

ግንቦት ወር ላይ ፌስቡክ 12 ገፆችን እንዲዘጋ የታዘዘ ሲሆን ትዊተርም 16 ገፆችን እንዲዘጋ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።

አርብ ዕለት የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፌስቡክ እነዚህ የፌስቡክ ገፆች ከየትኛውም የዓለም ክፍል አገልግሎት እንዳይሰጡ አልዘጋም በማለቱ 368 ሺህ ዶላር የቀጣ ሲሆን፤ በወቅቱ ፌስቡክ ገፆቹ ከብራዚል ብቻ መጠቀም እንዳይቻል ለመዝጋት ነበር የተስማማው።

ከዚህም በተጨማሪ የተላለፈውን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ አልተገብርም በማለቱ በቀን 19 ሺህ 184 ዶላር እንዲከፍል ወስኖበታል።

ይሁን እንጂ ቅጣቱ በተመሳሳይ መልኩ በትዊተርም ላይ ስለመጣል አለመጣሉ የታወቀ ነገር የለም።

ፌስቡክ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ከዓለም አቀፍ ሕግ እና ሥልጣን ጋር የሚጋጭ ነው ሲል ተቃውሞታል።

ድርጅቱ አክሎም ለፍርድቤቱ ይግባኝ እንደሚል ጠቅሶ " በአገሪቷ ባሉ የድርጅቱ ሰራተኞች ላይ የወንጀል ተጠያቂነት ስጋት የፈጠረ በመሆኑ፤ የፌስቡክ ገፆቹ ከየትኛውም የዓለም ክፍል አገልግሎት እንዳይሰጡ የተላለፈውን ውሳኔ ከመተግበር ውጪ በዚህ ጊዜ ሌላ አማራጭ የለንም" ብሏል።

በዚህም መሠረት ከተዘጉ ገፆች መካከል የፓርቲው መሪና የፕሬዚዳንቱ ታማኝ ሮበርቶ ጀፈርሰን እና ሉሲያኖ ሃንግ የተባሉ የብራዚል ታዋቂ የቢዝነስ ሰው ይገኙበታል።

ፌስቡክ ሐምሌ ወር ላይም ጋዜጠኛና የዜና ገፆች በመምሰል የተከፈቱ በርካታ ሃሰተኛ የፌስቡክና የኢንስታግራም ገፆችን ዘግቷል።

እነዚህ ገፆች በፕሬዚደንቱ ጽህፈት ቤቶች ሰራተኞች እንዲሁም ከልጆቻቸው ኤድዋርዶ እና ፈላቪዮ እና ሌሎች ጋር የተያያዙ እንደነበሩ ፌስቡክ ገልጿል።

ፌስቡክና ትዊተር የጥላቻ ንግግሮችን እና ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመዋጋት በሚያደርጉት ጥረት ውጥረት ውስጥ ናቸው።