ኮሮናቫይረስ፡ አውሮፕላኖች እንዴት ነው በፀረ- ተህዋሲያን የሚፀዱት?

የፎቶው ባለመብት, Getty
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ቀጥ ብሎ የነበረውን የአለም የንግድ እንቅስቃሴን ለመመለስ በርካታ ጥረቶች እየተደረገ ነው።
በተለያዩ አገራትም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ጥለዋቸው የነበሩ መመሪያዎችን እያላሉ ይገኛሉ።
የወረርሽኝ ስርጭቱን ለመግታት አገራት አስተላልፈዋቸው ከነበሩ መመሪያዎች መካከል ዓለም አቀፍ በረራዎችን ማቆም፣ አየር ማረፊያዎቻቸውንና ድንበሮቻቸውን መዝጋት ይገኙበታል።
በዚህም የተነሳ በርካታ የኢንዱስትሪ ዘርፎች በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱ ሲሆን በተለይም የአየር ትራንስፖርት ዘርፉ እንዲሽመደመድ ምክንያት ሆኗል።
ከሰሞኑ አገራቱ ዘግተዋቸው የነበሩ ድንበሮቻቸውን ከፍተዋል፤ አለም አቀፍ አየር መንገዶቹም በረራዎችን ጀምረዋል።
የአለም አቀፉ አቪየሽን ድርጅት የአየር ትራንስፖርቱ ዘርፍ እንዲያንሰራራና ተጓዦችም ደህንነታቸቸው በተጠበቀ መልኩ እንዲጓዙ ለማድረግ እንደ መመሪያነት የሚያገለግል አንድ ሰነድ አውጥቷል።
በዚህም መመሪያ ውስጥ ከተካተቱት ጉዳዮች መካከል አውሮፕላኖች በምን መንገድ በፀረ- ተህዋሲያን መፀዳት እንዳለባቸውና የፅዳት ድግግሞሽንም ይመለከታል።
እንዲሁ ከላይ ከላይ ሲታይ የአየር በረራና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ የሚጣጣሙ አይመስሉም ።
ነገር ግን ተቆጣጣሪ አካላት የተለያዩ ፕሮቶኮሎችን በማውጣት አስፈላጊ የሚባሉ የፅዳት መመሪያዎችን ለመተግበር ቀን ተሌት ደፋ ቀና በማለት ላይ ናቸው።
ለአየር በረራዎች በዋነኝነት የሚያስፈልገው ፈጣንና፣ በቅልጥፍና የተሞላ ውጤታማ ፀረ- ተህዋሲያን የፅዳት ስርዓት መዘርጋት ነው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ፍቃድ ያላቸው የፀረ- ተህዋሲያን ፅዳት በሚታዩና፣ ተደራሽ በሆኑ አካላት ላይ ጨርቅን እንዲሁም ተንቀሳቃሽ መርጫን በመጠቀም ማፅዳት ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ።
ነገር ግን ሁለቱም የማፅጃ መንገዶች በሰዎች አማካኝነት የሚካዱ ከመሆናቸው አንፃር ውጤታማነታቸውን የሚቀንስ ሲሆን መደረስ የማይችሉ የአውሮፕላኑ አካላትም ላይ ክፍተትን ይፈጥራሉ ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty
ኦክስጅንና ኦዞን
በሌላ መልኩ "አቶሚክ ኦክስጅንን" እንደ ፀረ-ተህዋሲያነት በመጠቅም አካባቢን ለማፅዳት ተጀምሯል።
ከዚህም በተጨማሪ አምቡላንሶችን ለማፅዳት የሚጠቀሙበትን ፀረ ተህዋሲያንንም ለአውሮፕላን የውስጥ ክፍል ለማፅዳት እየታሰበበት ነው።
ነገር ግን እነዚህ ማፅጃዎች ባላቸው የንጥረ ነገር በተለይም 'ኦክሳይድ' ባለው ባህርይ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች ላይ ጉዳት ሊፈጥሩ ይችሉ ይሆን በሚለው ስምምነት ላይ አልተደረሰም።
መቶ በመቶ ውጤታማ የፀረ ተህዋሲያን ማፅጃ በሌለበት ሁኔታ ሌላኛው አማራጭ "የኦዞን" ንጥረ ነገሮችን መጠቀም ነው።
በአሁኑ ወቅት ኦዞን በአውሮፕላን አካላት ላይ አገልግሎት ላይ ባይውልም በመጠጥ ቤቶችና በተለያዩ የንግድ ተቋማት ላይ በፀረ-ተህዋሲያን ማፅጃነት እያገለገለ ይገኛል።
አካባቢውን የኦዞን ንጥረ ነገሮችን በመርጨት ውጤታማ የሆነ ፅዳትን ማግኘት ይቻላል።
ነገር ግን ይህ ንጥረ ነገር በከፍተኛ መጠን ሲሆን ለሰዎች ጎጅ በመሆኑ ባለሙያን በመጠቀም መንገደኞች በሌሉበት ሁኔታ ሊረጭ ይገባል።
ነገር ግን አሁንም ቢሆን ኦዞን ላይ ያለው ዋነኛ ጥያቄም የኦክሳይድ ንጥረ ነገር መጠኑ ነው፤ 'በአውሮፕላን የውስጥ አካልና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ላይ ያለው ተፅእኖ ላይ መስማማት አልተቻለም።
'አየኖችና የአልትራቫዮሌት ጨረር '
በላብራቶሪ ውስጥ ተሞክሮ ውጤታማ የሆነው ከከባቢ አየር የሚለቀቀውን የውሃ ትነት ውስጥ የኦክስጅንና ሃይድሮጅን ንጥረ ነገሮችን ለይቶ በማውጣት ፀረ ተህዋሲያንን መፍጠር ነው።
ይህ የፀረ ተህዋሲያን ማፅጃ መንገድ በጣም አድካሚና ለሁለት ሰዓታት ያህልም የሚወስድ ጊዜን ይፈጃል።
ሆኖም ይሄ መንገድ በከፍተኛ ሁኔታ ውጤታማና መቶ በመቶ የሚተማመኑበት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ፀረ ተህዋሲያኑ ቀላልና ተንቀሳቃሽ በሆነ መልኩ ትልልቅ የአውሮፕላን አካሎችን ማፅዳት ቢቻልም ለማፅዳት ግን ረዘም ያለ ጊዜ መውሰድ ያስፈልጋል።
ሌላኛው ደግሞ ሲ የሚባለው የአልትራቫዮሌት ጨረር ሲሆን ይህ ጨረር ሳርስ የተባለውን የኮሮናቫይረስ አይነት ማጥፋት ይችላል።
ለዚያም ነው ከፍተኛ ወጪ የሌላቸው ጨረሮች የአውሮፕላን አካላትን ለማፅዳት እየተነደፉ እንዲሁም እየተመረቱ ያሉት።
ይህንም ተከትሎ በገበያው ላይ የነዚህ ጨረሮች ፍላጎት በመጨመሩ ምክንያት የአልትራቫዮሌት ጨረሮችን የሚያመርቱ ኩባንያዎች ምርታቸው በሚቀጥሉት አራት አመታት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምርም ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በርካታ አማራጮች
በርካታ የፀረ ተህዋሲያን ማፅጃ አማራጮች ከመኖራቸው አንፃር በተለያየ ሂደትም ላይ ናቸው።
አሁንም ቢሆን የትኛው የበለጠ ተስማሚ እንደሆነም እስካሁንም አይታወቅም።
የትኛው የፀረ ተህዋሲያን ስርአት የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆን መለየት ከተቻለ በኋላ ምን ያህል ጊዜም ይወስዳል የሚለውን ማየት አስፈላጊ እንደሆነም እየተነገረ ነው።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አሁንም ስጋት ሆኖ ባለበት ወቅት በርካታ አየር መንገዶች በረራ መጀመራቸው ጋር ተያይዞ ቫይረሱ እንዳይሰራጭ የማድረግ ከፍተኛ ኃላፊነትና ሸክም ተጥሏባቸዋል።
የአውሮፕላኑ ሰራተኞች፣ መንገደኞችን ደህንነት በሚያስጠብቅ መልኩ አውሮፕላኖቹ በፀረ ተህዋሲያን መፀዳትም ግዴታ ነው።
እነዚህ የፀረ ተህዋሲያን ማፅጃ ዘዴዎች ቫይረሱን መግታት ብቻ ሳይሆን የአየር መንገድ ኃላፊዎችም ሆነ ተቆጣጣሪዎች የሚያስወጣቸውን ዋጋና እንዲሁም ቀልጣፋና ውጤታማ በሆነ መንገድ መፅዳት የሚችሉበትን ሁኔታ መገምገም ይጠበቅባቸዋል።
በአንድ መልኩ የአየር ትራንስፖርቱ ወደቀደመ ሁኔታ እንዲመለሱ ግፊት እያደረጉ ሲሆን በሌላ መልኩ በዚህ ወረርሽኝ መካከል የተጓዦች ደህንነት በተጠበቀ መልኩ አገልግሎታቸውን መመለስና በወረርሽኙ ምክንያት ያጡትን ገቢ ለማግኘትም አጣጥመው መሄድ ይጠበቅባቸዋል።
በተለይም አውሮፕላኖቹ የሚፀዱበትን ደረጃና ያለውን የስጋት መጠንን መቀነስና፤ የሚፀዳበትን ጊዜ አጣጥመው መሄድም ይጠበቅባቸዋል።
የመንገደኞችን ጤንትና ደህንነት ቅድሚያ በመስጠትም አየር መንገዶቹ እነዚህን ተግባራት እንዲያከናውኑም አለም አቀፉ አቪየሽንም መመሪያ ሰጥቷል።
ከአለም አቀፉ አቪየሽን ቡድንና፣ የትራንስፖርት ዘርፍ ተመራማሪዎች የተውጣጡ ግለሰቦችም ውጤታማ የሆኑትን የፀረ ተህዋሲያን የማፅጃ ዘዴዎችንም ለመቀየስ ከፍተኛ ምርምሮችን እያደረጉም ነው፤ የተለያዩ መመሪያዎችንም በማውጣትም ላይ ይገኛሉ።














