በኮሮናቫይረስ ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ በረራዎች እየተጀመሩ ነው

የኬንያ አየር መንገድ

የፎቶው ባለመብት, TONY KARUMBA

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት አገራት አስተላልፈዋቸው ከነበሩ መመሪያዎች መካከል ዓለም አቀፍ በረራዎችን ማቆም፣ አየር ማረፊያዎቻቸውንና ድንበሮቻቸውን መዝጋት ይገኙበታል።

በአሁኑ ወቅት እነዚህ መመሪያዎች እየተሻሻሉ ሲሆን ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች በረራቸውን እንደገና የጀመሩ ሲሆን በርካቶችም ከሐምሌ 25/2012 ዓ.ም ጀምሮ በረራዎችን እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።

ከእነዚህም ውስጥ ኬንያ ትገኝበታለች። በወረርሽኙ ምክንያት ዘግታው የነበረውን አየር ማረፊያዋን እንዲሁም በረራዎች በነገው ዕለት እንደሚጀመሩ የኬንያው የጤና ሚኒስትር ሙታይ ካግዌ ገልፀዋል።

ምንም እንኳን በረራ ይጀመራል ቢባልም የጤና ሚኒስትሩ እንዳሳወቁት ከጥብቅ ቁጥጥርና መመሪያዎች ጋር መሆኑን እንዲሁም ተጓዦች ሁኔታዎች ሊቀየሩና በነዚህም ምክንያቶች መጉላላት ሊያጋጥም እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።

በመጀመሪያው ዙር ከሁሉም አገራት የሚመጡ ተጓዦች ሳይሆኑ ወደ አገሯ እንዲገቡ የፈቀደችው ለይታ አስራ የአንድ አገራትን ዝርዝር አውጥታለች።

እነዚህም አስራ አንድ አገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ካናዳ፣ ዚምባብዌ፣ ፈረንሳይ፣ ኡጋንዳ፣ ናሚቢያ፣ ሞሮኮና ሩዋንዳ ናቸው።

አገሪቷ የኮሮናቫይረስ የማኅበረሰብ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ያሳወቀች ሲሆን በዛሬው ዕለት 723 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 20 ሺህ 636 ደርሷል። ከዚህ በተጨማሪም ኬንያ እስካሁን 341 ዜጎቿንም በቫይረሱ አጥታለች።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቋርጧቸው የነበሩ በርካታ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ፣ የአውሮፓና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በረራዎቹን በዚህ ወር መልሶ መጀመሩንና ወደ ተቀሩትንም መዳረሻዎቹ በተከታይነት በረራዎችን ማካሄድ እንደሚጀምር አስታውቋል።

በአፍሪካ ውስጥ ወደ ምዕራብ አፍሪካዋ ካሜሩን ሁለት ከተሞች በረራ ማድረግ የጀመረ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ ጂቡቲ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ዘግታው የነበረውን አየር ማረፊያዋን ክፍት ማድረጓን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ ወር ወደ ጂቡቲ የሚያደርገውን በረራ ጀምሯል።

ከአፍሪካ ግዙፉ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስካሁንድ ድረስ ከአርባ አገራት በላይ ዓለም አቀፍ በረራዎችን እያደረገም ይገኛል።

የምርመራ ውጤት

አገራት አየር ማረፊያቸውን መክፈት እንዲሁም በረራዎችን ቢጀምሩም ኢትዮጵያን ጨምሮ አገራቱ መንገደኞቹ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የኮቪድ- 19 ሰርቲፊኬት ይዘው እንዲመጡ ያስገድዳሉ።

ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ከአምስት ቀናት በፊት የተደረገ 'አርቲ ፒሲአር' የተባለውን የኮሮናቫይረስ ምርመራ አድርገው የነፃ ሰርቲፊኬት መያዝ የሚጠበቅብዎ ሲሆን፤ ከደረሱም በኋላ ሙቀትዎት ተለክቶ፣ መረጃዎት ተወስዶ በቤትዎ ለአስራ አራት ቀናት በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቀመጡ ይጠየቃሉ።

በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን አገሪቷ አትቀበልም። የነፃ ሰርቲፊኬት ካልያዙ አገሪቷ በመረጠቻቸው ለይቶ ማቆያዎች ውስጥ ለሰባት ቀናት እንዲገቡ ይደረጋሉ፤ ምርመራም ይደረጋል።

ወደ ኬንያም ለመግባት የሚያስቡ መንገደኞች ከተመረመሩ 96 ሰዓታት በታች የሆነውና ነፃ መሆንዎትን የሚያሳይ የኮቪድ-19 ሰርቲፊኬት ማሳየት አለብዎት። ከዚህም በተጨማሪ የኮሮናቫይረስ ምልክቶች የሆኑትን ሳል፣ ከ37.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት በላይ ሊያሳዩ አይገባም።

ኮሮና
Banner