አምስት የአፍሪካ አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ አቋረጡ

የፎቶው ባለመብት, Nur Photo/Getty Images
በቻይና በተስፋፋው የኮሮናቫይረስ ምክንያት አምስት አየር መንገዶች ወደ ቻእና የሚያደርጉትን በረራ አቋረጡ።
የኬንያ፣ የሩዋንዳ፣ የማዳጋስካር፣ የሞሪሸስ እና የሞሮኮ አየር መንገዶች ወደ ቻይናና ከቻይና ያደርጓቸው የነበሩትን ሁሉንም ጉዞዎች ለጊዜው ማቆማቸውን አስታወቀዋል።
አየር መንገዶቹ ከዚህ ውሳኔያቸው በፊት ወደ ቻይና ወይም ከቻይና ለመጓዝ ትኬት ቆርጠው የነበሩ ደንበኞቻቸውን ገንዘብ ለመመለስ ወይም በሌላ መስመር እንዲመጡ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
በአፍሪካ ካሉ ጥቂት ግዙፍ አየር መንገዶች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ትናንት ሐሙስ እንዳስታወቀው ወደ ቻይና የሚያደርጋቸው ሁሉም በረራዎቹ ይቀጥላሉ።
አየር መንገዱ "መንገደኞቹንና ሠራተኞቹን" ካለው ስጋት ለመጠበቅ ከቻይናና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየሰራ ነው።
የዓለም የጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ የወቅቱ ዋነኛ የጤና ስጋት መሆኑን ማወጁን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና በሚያደርጋቸው በረራዎች ላይ እስካሁን የለወጠው ነገር የለም።
ትናንት የዓለም የጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ አሳሳቢ መሆኑን ቢያውጅም፤ ወደ ቻይና የሚደረግ ጉዞና ንግድን የሚያስተጓጉል ምንም ምክንያት እንደሌለ ገልጾ ነበር።
በወረርሽኙ ምክንያት ከ200 በላይ ሰዎች ቻይና ውስጥ የሞቱ ሲሆን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቢያንስ በሌሎች 18 አገራት ውስጥ ተገኝተዋል።
ስድስት በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎች በአፍሪካ ውስጥ ተገኝተው የነበሩ ቢሆንም በተደረገላቸው ምርመራ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ተረጋግጧል።
በሽታው ከተቀሰቀሰባት የቻይናዋ ዉሃን ከተማ ማክሰኞ ዕለት ወደ ኬንያ የተመለሰ አንድ ተማሪ በበሽታው ተጠርጥሮ በተለየ ቦታ ምርመራና ክትትል ሲደረግበት ቆይቶ ከበሽታው ነጻ መሆኑ ታውቋል።
ኢትዮጵያ ውስጥም አራት በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎች ተገኝተው የነበረ ቢሆንም የደም ናሙናቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኮ ቫይረሱ እንደሌለባቸው ተረጋግጧል።
የኬንያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚደረጉ በረራዎችን ላልተወሰነ ጊዜ ማቋረጡን ካሳወቀ በኋላ፤ የበረራ እገዳው ምን ያህል ጊዜ ሊቆይ እንደሚችል ከአገሪቱ የጤናና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር እየተማከረ መሆኑን አሳውቋል።
አየር መንገዱ አክሎም በቻይና መስመር ወደ ታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ የሚያደርገው በረራ ግን ባለበት እንደሚቀጥል ገልጿል።












