በኮሮናቫይረስ ሳይያዙ አይቀሩም ተብለው የተጠረጠሩት ኢትዮጵያውያን ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን ተነገረ

ኮሮና ቫይረስ

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto

በኮሮናቫይረስ ሳይያዙ አይቀሩም ተብለው የተጠረጠሩት አራት ኢትዮጵያውያን ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን መረጋገጡን የጤና ጥበቃ ሚንስቴር አስታወቀ።

ከሁለት ቀናት በፊት በኮሮናቫይረስ ሳይያዙ አይቀሩም ተብለው የተጠረጠሩ አራት ኢትዮጵያውያን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መገኘታቸውን የጤና ጥበቃ ሚንስቴር አስታውቆ ነበር።

በወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ለተጠርጣሪ ህመምተኞቹ የላብራቶሪ ናሙና ተወስዶ ለምረመራ ወደ ደቡብ አፍሪካ መላኩን አስታውቆም ነበር።

በዚህም መሠረት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለተጨማሪ የላብራቶሪ ምርመራ የተላኩት የአራቱ ተጠርጣሪዎች ውጤት ከኖቭል ኮሮናቫይረስ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል ተብሏል።

ከአራቱ ኢትዮጵያውያን መካከል 3ቱ ቫይረሱ በተከሰተበት ዉሃን ግዛት ተማሪ እንደነበሩ ተገልጿል።

በበሽታው የተጠረጠሩት ግለሰቦቹ በለይቶ ማከሚያ ማዕከል ተለይተው ክትትል እንደሚደረግላቸው በወቅቱ ተነግሮ ነበር።

በአሁኑ ወቅት በቻይና አንድ ግዛት ውስጥ የተቀሰቀሰው የኮሮናቫይረስ መላ ቻይናን ማዳረሱንና በበሽታው የሞቱ ሰዎች ቁጥርም 170 መድረሱ ተነግሯል።