በዩናይትድ ኪንግደም የፓርላማ አባሉ በመድፈር ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው

በለንደን የሚገኘው ፓርላማ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

በዩናይትድ ኪንግደም በመድፈር ወንጀል ተጠርጥረው የወግ አጥባቂው የፓርላማ አባል ታስረው የነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በዋስ መለቀቃቸው ተገልጿል።

ዘ ሰንደይ ታይምስ እንደዘገበው የፓርላማ አባሉ ላይ ክስ የተመሰረተባቸው በቀድሞ የፓርላማው ሰራተኛ ነው።

ግለሰቡ ላይ የቀረበባቸው ክስ በባለፈው ሐምሌና በተያዘው ዓመት ጥር ወር መካከል ባሉት ጊዜያት ከተፈፀሙ አራት የተለያዩ ድርጊቶች ጋር የተያያዘ መሆኑንም የከተማው ፖሊስ አስረድቷል።

ወግ አጥባቂው ፓርቲ በበኩሉ እንዲህ ዓይነት ክሶችን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚያየው ገልጿል።

ዜናውን ቀድሞ የዘገበው ጋዜጣው፤ ግለሰቧ ትንኮሳ እንደደረሰባትና ወሲብ እንድትፈፅም እንደተገደደች እና በዚህም ሳቢያ በደረሰባት የአእምሮ ጉዳት ሆስፒታል ለመሄድ መገደዷን አትቷል።

የከተማው ፖሊስም በክሱ ላይ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።

ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት ፖሊስ ከወሲባዊ ጥቃት ጋር የተያያዙ አራት የተለያዩ ተጨማሪ ክሶች መቀበሉንም በመግለጫው አስታውቋል።

እነዚህ ጥቃቶች የተፈፀሙት በዌስትሚኒስተር ላምቤዝ እና ሃክኒይ በተባሉ ቦታዎች ሲሆን ድርጊቱም በባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር እና በተያዘው ዓመት ጥር ወር መካከል ባሉት ጊዜያት የተፈፀሙ ናቸው ብሏል።

በ50ዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኙት ግለሰቡ በመድፈር ወንጀል ተጠርጥረው ትናንት በቁጥጥር ሥር የዋሉ ቢሆንም ከሳምንታት በኋላ እንዲቀርቡ ታዝዘው በዋስ ተለቀዋል።

የወግ አጥባቂው ፓርቲ ቃል አቀባይም "እንደዚህ ዓይነት ክሶችን በትኩረት ነው የምናየው ፤ አሁን ጉዳዩ በፖሊስ የተያዘ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ሃሳብ መስጠት ትክክል አይሆንም" ሲሉ ዝርዝር ሃሳብ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በሌላ በኩል የወግ አጥባቂው ፓርቲ አፈ ጉባኤ ማርክ ስፔንሰር በግለሰቧ የቀረበውን ክስ ያውቁ እንደነበርና ከዚህ ቀደም ተጎጅዋን አነጋግረው እንደነበር ተዘግቧል።

ይሁን እንጂ አፈ ጉባዔው የክሱን መጠን ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እንደማያውቁ የቢቢሲ ምንጮች ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩም "አፈጉባዔው ሁሉንም የትንኮሳና ጥቃት ክሶች በትኩረት እንዳዩት ገልፀው፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ ያነጋገሯቸውን ግለሰቦች የሚመለከታቸውን አካላት እንዲያነጋግሩ ሲያበረታቱ ነበር" ብለዋል።