ዝነኛው ድምጻዊ በአስገድዶ መድፈር ጥፋተኛ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በአፍሪካ ታዋቂ ከሚባሉት ድምጻዊያን መካከል አንዱ የሆነው ኮፊ ኦሎሚዴ የቀድሞ ዳንሰኛው የነበረችን ሴት 15 ዓመት እያለች አስገድዶ ደፍሯል በሚል ጥፋተኛ ተባለ።
የድምጻዊውን ጉዳይ ተመልክቶ በገደብ የሁለት ዓመት እስር የወሰነው ፈረንሳይ ውስጥ የሚገኝ ፍርድ ቤት ሲሆን ተከሳሹ በብይኑ ወቅት ፍርድ ቤት አልተገኘም ነበር።
በዚህ ውሳኔ መሰረት ኮንጓዊው ታዋቂ ድምጻዊ ላይ የተሰጠው ብይን ተግባራዊ የሚሆነው ሌላ ወንጀል ከፈጸመ ብቻ ነው።
የስድሳ ሁለት ዓመቱ ድምጻዊ ኦሎሚዴ ጥቃቱ ለተፈጸመባት የቀድሞ ዳንሰኛው 5 ሺህ ዩሮ እንዲከፍል የተወሰነበት ሲሆን፤ በተጨማሪም ሦስት ሴቶች በህገወጥ መንገድ ወደፈረንሳይ እንዲገቡ አድርጓል ተብሎ ተመሳሳይ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎበታል።
የድምጻዊው ጠበቃ ግን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኦሎሚዴ ላይ የተላለፈውን ዓለም አቀፍ የእስር ማዘዣ የሚያስነሳለት በመሆኑ ትልቅ ድል ነው ሲል ለጋዜጠኞች ተናግሯል።
ኮፊ ኦሎሚዴ በአፍሪካ ውስጥ በስፋት በሚወደዱት የሩምባና የሱኩስ የሙዚቃ ስልቶች ታዋቂ ድምጻዊ ነው።
ኦሎሚዴ ላይ መጀመሪያ ክስ የቀረበበት ከሰባት ዓመታት በፊት ከባድ አስገድዶ የመድፈር ጥቃት ሲሆን በኋላ ላይ ክሱ ዝቅ እንዲልለት ተደርጓል።
ከድምጻዊው ጋር ሲሰሩ የነበሩ አራት ተወዛዋዦች ለፍርድ ቤት እንደተናገሩት ከዓመታት በፊት ወሲባዊ ጥቃት ተፈጽሞብናል ብለዋል። ጥቃቱም በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ፈረንሳይ ውስጥ እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል።
ሴቶቹ ጨምረውም በወቅቱ ፓሪስ በሚገኝ በአንድ ቪላ ውስጥ ተዘግቶባቸው እንዲቆዩ መደረጉንና አንድ ምሽትም አምልጠው መውጣታቸውን ተናግረዋል። ቢሆንም ግን የበቀል ጥቃት ይደርስብናል በሚል ስጋት ወደሃገራቸው ኮንጎ ለመመለስ እንደፈሩ ገልጸዋል።
አቃቢ ህጎች በድምጻዊው ላይ የሰባት ዓመት እስር እንዲበየንበት ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ ተፈጸመ የተባለውን ድርጊት ሳይቀበለው በመቅረቱ ቅጣቱ ዝቅ ብሏል።
ኦሎሚዴ ከአስር ዓመታት በፊት ከፈረንሳይ ሸሽቶ ኮንጎ ውስጥ መኖር የጀመረ ሲሆን እራሱን ለመከላከል ፍርድ ቤት እቀርባለሁ ብሎም ነበር። ነገር ግን ብይኑ በተሰጠበት ጊዜ ወደ ፈረንሳይ ሳይመጣ ቀርቷል።
በካሳሾቹ ጥያቄ መሰረት የፍርድ ሂደቱ ፓሪስ ውስጥ በዝግ ችሎት ነበር የተከናወነው።
በትክክለኛ ስሙ አንቷን አግቤፓ ሙምባ በመባል የሚታወቀው ኮፊ ኦሎሚዴ ከዚህ ቀደም ሲልም በተደጋጋሚ ጊዜያት ክስ ገጥሞት ነበር።
• ከአንድ ዓመት በፊት ፎቶግራፍ አንሺን በመደብደቡ ዛምቢያ ውስጥ ተከሶ ነበር
• ከሦስት ዓመት በፊት ኬንያ ውስጥ አንድ ተወዛዋዥን በመደብደቡ ተይዞ ከሃገር እንዲባረር ተደርጓል
• ከሰባት ዓመት በፊት ኮንጎ ውስጥ የሥራ ባልደረባውን በመደብደብ ተከሶ በገደብ የሦስት ወራት እስር ተፈርዶበት ነበር
• ከአስር ዓመት በፊት ደግሞ ኮንጎ ውስጥ በሙዚቃ ድግስ ወቅት የቴሌቪዥን ካሜራ ባለሙያን በመምታት ካሜራውን ቢሰብርም ኋላ ላይ ጉዳዩ በእርቅ እንዲያልቅ ተደርጓል።












