ኮሎኔል ሪጃል ዑመር፡ 'ወጣት መሳዩ' የ108 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ?

ሲያዩዋቸው የ40 ዓመት ጎልማሳ ነው የሚመስሉት፤ የፈረጠመ ሰውነት ነው ያላቸው፤ እሳቸው ግን 108ኛ ዓመቴን ደፍኛለሁ ይላሉ።
አቋማቸው ከዕድሜያቸው ጋር አልስተካከል ያላቸው ግን ብዙዎች ናቸው። ቢቢሲ ከእኝህ የዕድሜ ባለጸጋ ነኝ ከሚሉት ኮሎኔል ሪጃል ኡመር ጋር ቆይታ አድርጓል።
ቢቢሲ፡ ፎቶግራፍዎን አይቼ 'አንቱ' ለማለት ተቸገርኩ'ኮ?
ኮሎኔል ሪጃል፡ እንዴ በቅርብ የወደድኳት አንድ ጓደኛዬ አለች። ከዚያ ደግሞ የልጅ ልጅ ልጄ (አራተኛ የልጀ ልጄ) 'አንተ ሪጃል!' ብላ ነው እንጂ የምትጠራኝ፤ 'አንቱ' ያለኝ ሰው እስካሁን የለም።
ቢቢሲ፡ በቅርብ የወደድኳት ልጅ ነው ያሉኝ?
ኮሎኔል ሪጃል፡ አለች። አዎ!
ቢቢሲ፡ አሁን ወደድኳት ያሉኝ ሴት ዕድሜዋ ስንት ነው?
ኮሎኔል ሪጃል፡ ስንት ዓመትሽ ነው አንቺ? ዕድሜሽ ስንት ነው? (ጠየቁዋት) እዚህ አጠገቤ ነው ያለችው... 35 ዓመቷ ነው።
ቢቢሲ፡ ምኗን ነው የወደዱት?
ኮሎኔል ሪጃል፡ አቋሟ ደስ ይላል!.. እዚህ አጠገቤ ነው ያለችው ታናግርህ።
[ኮለኔል ስልኩን አሳልፈው ፍቅረኛዬ ለሚሏት ፀሐይ አቀበሉ። ሠላምታ ተለዋወጥን ጥያቄያችንንም ለእሳቸው አስከተልን።]
ቢቢሲ፡ ወድጃታለሁ ፍቅር ላይ ነን ይላሉ ኮለኔል?
ወ/ሮ ፀሐይ፡ አዎ! እኔም ወድድድ...... አድርጌዋለሁ።
ቢቢሲ፡ ምናቸውን ወደድሽ? ዕድሜው ገፋ ያለ ሰው ብዙም ....።
ወ/ሮ ፀሐይ፡ እኔ ደግሞ ጠና ያለ ሰው በጣም ነው የምወደው።
ቢቢሲ፡ አሁን ያንቺዕድሜ በእርሳቸው ዕድሜ ሲሰላ ሦስት እጥፍ ማለት እኮ ነው... ሦስት እጥፍ ከሦስት ዓመት
ወ/ሮ ፀሐይ፡ እኔ ተመችቶኛል፤ እንግባባለን። ከዚያ በላይ ምን አለ ብለህ ነው? ቁመናውን፣ ሁሉንም ነገሩን ወድጃለሁ። ፍቅር እንግዲህ ዕድሜን አይወስንም። ደሞ ፍቅር እንዲህ ነው ተብሎ ለሰው አይገለፅም።
ቢቢሲ፡ ኮሎኔልን ስታያቸው በጣም ብዙ ዕድሜ ነው የሚታይሽ ወይስ ወጣት ሆነው ነው?
ወ/ሮ ፀሐይ፡ ለእኔ ወጣት ነው! ስንት ልበልህ?... በቃ አለ አይደል...እኔ በአርባዎቹ የዕድሜ ክልል ነው የሚመስለኝ።
[አሁን ደግሞ ለኮሎኔል ስልኩን አቀበሉ]
ቢቢሲ፡ ኮሎኔል ፍቅር ዕድሜ ያረዝማል እንዴ?
ኮሎኔል ሪጃል፡ (ሳቅ) እኔ ከመጀመሪያ ጀምሮ ጥል አላውቅም፤ አንድ ወቅት የሶማሊያ ወታደር በማረኩ ጊዜ የራሴን ልብስ ነው አውልቄ ያለበስኩት፤ ፍቅር ብቻ ነው የማውቀው።
ቢቢሲ፡ እርስዎ ልጅ እያሉ አንድ በግ ዋጋው ስንት ነበር?
ኮሎኔል ሪጃል፡ በግ ዋጋ የለውም። እኔ አንድ ጊዜ ትዝ የሚለኝ ወደ ኮሪያ ለመሄድ ብዬ ላሞች ነበሩና ሁለት ጥጃ ያላትን ላምና አንድ በሬ (ሦስቱን) በሰባት ብር ሸጬ ነው በ1943 ዓ. ም ወደ ኮሪያ የሄድኩት።
ቢቢሲ፡ ከኮሪያ ዘማቾች ከተመለሱ በኋላ ዘማቾች ጃንሆይ ላይ የደመወዝ ጥያቄ አንስተው ነበር ይባላል...
ኮሎኔል ሪጃል፡ አዎ! ልክ ነህ። ደመወዝ ከ20 ብር ወደ 60 ብር ይደግልን የሚል ነበር ጥያቄው። የኃይለ ሥላሴ ታማኝ ስለነበርኩና ቤተመንግሥት ውስጥ ስለማገለግል እኔ አመጹ ላይ አልተሳተፍኩም።
ቢቢሲ፡ ከደርግ ባለሥልጣናት ማንን ያውቃሉ?
ኮሎኔል ሪጃል፡ ጀኔራል ተፈሪ በንቲን። እንዲያውም አንዱን ልጄን ተፈሪ ያልኩት በጀኔራሉ ስም ነው። አዲስ አበባ ነው የሚኖረው... ፀጉሩን ተመልጧል እንጂ... አረጀ!
ቢቢሲ፡ ዶክተር ዐብይን ያውቋቸዋል?
ኮሎኔል ሪጃል፡ አዎ አውቃቸዋለሁ! ያባ ፊጣ ልጅ ናቸው።
ቢቢሲ፡ ማናቸው ደግሞ አባ ፊጣ?
ኮሎኔል ሪጃል፡ አባ ፊጣ አሊ ነው የሚባሉት። ብዙ ዕውቅና ባይኖረኝም አውቃቸዋለሁ።
ቢቢሲ፡ ዶ/ር ዐብይን አግኝተዋቸዋል?
ኮሎኔል ሪጃል፡ ማግኘት አልፈልግም።
ቢቢሲ፡ ለምንድን ነው የማይፈልጉት? ብዙ ሰው ጠቅላይ ሚንስትሩን ማግኘት ይፈልጋል።
ኮሎኔል ሪጃል፡ (ረዥም ሳቅ) እኔ አኮ... እየውልህ... ንጉሡ ከአገር ሸሽተው በኖሩበት ጊዜ በባዶ እግሬ አገሪቷን ነፃ ለማውጣት ጫካ የገባሁ ነኝ (ቆፍጠን አሉ) ንጉሥ ፈላጊ አይደለሁም! ኢትዮጵያዊነትና ነፃነት ፈላጊ እንጂ...

የፎቶው ባለመብት, FBC
ቢቢሲ፡ በማን ዘመን ነበር የተወለዱት ኮሎኔል?
ኮሎኔል ሪጃል፡ በዳግማዊ ሚንሊክ ነበር። ከዚያ በኋላ በልጅ እያሱ ዘመን እረኛ ነበርኩ፤ ምን እንደነበር ግን አላውቅም።
ቢቢሲ፡ አፄ ምንሊክ ትዝ ይሉዎታል? አይተዋቸው ያውቃሉ በሩቁም ቢሆን?
ኮሎኔል ሪጃል፡ አላየሁም፤ ዘውዲቱንም አላየሁም፤ ኢያሱንም አላየሁም። በዐይኔ ያየኋቸውና እግራቸውን ያጠብኳቸው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ነው።
ቢቢሲ፡ የመጀመሪያ ልጅዎት ስንት ዓመቱ ነው?
ኮሎኔል ሪጃል፡ 75 ዓመቱ ነው፤ ባለፈው ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው።
ቢቢሲ፡ አሁንም ልጆች መውለድ ይፈልጋሉ?
ኮሎኔል ሪጃል፡ዛሬም ድረስ ልጅ መውለድ እፈልጋለሁ። ልጅ ወልጄ ማሳደግ እችላለሁ።
ቢቢሲ፡ ስንት ልጆች አለዎት?
ኮሎኔል ሪጃል፡የልጆቼን ቁጥር አልናገርም። ልጅ አይቆጠርም። አሁን አንተን ሳዋራህ ራሱ ቤቴ [በልጆች ብዛት] ሆስፒታል መስሏል። ለሁሉም ልጆቼ ማውረስ የምችለው ቤት አለኝ። የሁሉንም ልጆቼን ስም አላውቅም። ይሄ ደግሞ ማነው እያልኩ እጠይቃለሁ።
ቢቢሲ፡ ከልጆቸችዎ መካከል አብልጠው የሚወዱት ማንን ነው?
ኮሎኔል ሪጃል፡ ልጆቼን አብዝቼ የምወዳቸው 8 ዓመት እስኪሞላቸው ነው። ከዚያ በኋላ ግን አልወዳቸውም።
ቢቢሲ፡ እንደ እርስዎ 108 ዓመትና ከዚያ በላይ መኖር እፈልጋለሁ። ይምከሩኝ እስቲ ኮሎኔል?
ኮሎኔል ሪጃል፡ ማንም ሰው የፈለገውን ቢጨማለቅ እንደ ቆሻሻ መቁጠር፤ ለተሳዳቢ ጆሮ አለመስጠት፤ እሳት የነካው ሥጋ አለመብላት፤ ስፖርት ሳይሠሩ ቁርስ አለመብላት።
ቢቢሲ፡ ድሮ ሙዚቃ የማንን ነበር የሚውዱት? በምንድን ነበር የሚዝናኑት?
ኮሎኔል ሪጃል፡ ( ማንጎራጎር ጀመሩ)
መላ መላ በሉ እስኪ መላ፣
ልቤ ወዳንች እኮ አደላ፣
የማር እሸት፣ የማር ዛላ፣
የኔ ፍቅር የኔ ገላ ... የሚለውን እንዲሁም የይርጋ ዱባለን 'ዘብ ይቁም ሁሉም ለሀገሬ' የሚለውን ነው።
[ኮሎኔሉ ሲያንጎራጉሩ ድምፃቸው በጉልበት የተሞላና ኩልል ያለ ነበር። በእርግጥም ይህን የሰማ ኮሎኔሉ የ108 ዓመት አዛውንት ለማመን ቢቸገር አያምንም?]
ኮሎኔሉ ከወይዘሮ ምስኩ አባተማም ጋር በ1990 ዓ. ም. ጋብቻ ፈጽሚያለሁ ይላሉ።
ባለቤታቸው ወ/ሮ ምስኩን ስለ ባለቤታቸው ኮሎኔል ሪጃል እንዲህ አጫውተውናል።
"እኔ ዕድሜው አላውቅም። የመጨረሻ ሚስታቸው ነኝ። እኔን ጨምሮ 12 ሚስቶች አግብተዋል። የመጀመሪያ ሚስታቸው ትብለጽ ትባል ነበር። አሁን ሞታለች። ስትሞት ወደ 70 ዓመት ሆኗት ነበር። አግኝቻት ነበር።
ፋጡማ፣ ሲቲና፣ ፋጤ የሚባሉ ሚስቶቻቸውን አውቃለሁ። አግኝቻቸዋለሁም።
ዕድሜያቸው ከ100 ዓመት በላይ ነው። ትልልቅ ልጆች አሏቸው። ከኔ ጋ ግን የመጀመሪያ ልጃችን 20 ዓመቱ ነው። የመጨረሻዋ ልጃችን ደግሞ አስማ ትባላለች። ሁለት ዓመቷ ነው። ከሁለት ዓመት በፊት ነው የወለድናት።"
ኮሎኔል ሪጃልና ወ/ሮ ምስኩ የመጨረሻ ልጃቸውን የወለዱት ከሁለት ዓመት በፊት እንደሆነ ይናገራሉ። ኮለኔሉ እንደሚሉት አሁን 108 ዓመታቸው ከሆነ የመጨረሻ ልጃቸውን የወለዱት በ106 ዓመታቸው ነው ማለት ነው።
ወ/ሮ ምስኩን ባለቤታቸው በ106 ዓመታቸው ስለመውለዳቸው ስንጠይቃቸው እንዲህ መልስ ሰጥተውናል።
"አሁንም ቢሆን መውለድ ይችላሉ። ሦሰቱን ልጆቼን በቀዶ ህክምና ነው የወለድኳቸው። አሁንም መውለድ እፈልግ ነበር። ነገር ግን ሐኪሞቹ ከአሁን በኋላ መውለድ እንደሌለብኝ ነገሩኝ። ጥሩ አይደለም አሉኝ።
ባለቤታቸው ወ/ሮ ምስኩ ጨምረው እንደሚሉት ከሌላ ሚስት የወለዱዋቸው ልጆቻቸው ትልልቆች ሰዎች ናቸው። አንዱ ልጃቸው አዲስ አበባ ነው የሚኖው። ጸጉሩ የገባ ነው። ዕድሜው ከ50 ዓመት በላይ ይሆናል።"
ለወ/ሮ ምስኩ ሌላው ያቀረብነው ጥያቄ ስለ ኮለኔል ሪጃል አመጋገብ ነው። እሳቸው እንደሚሉት ኮሎኔሉ ብዙም እንጀራ መብላት አይወዱም። እራት አይመገቡም፤ የሚወዱት ጥራጥሬ ነገሮችን ነው። ጥሬ ሥጋም ነፍሳቸው ነው።
ለኮለኔሉ ባለቤት ያቀረብነው የመጨረሻ ጥያቄ ኮሎኔል ሪጃል ጸባያቸው እንዴት ያለ ነው? የሚል ነበር።
"ባህሪያቸው. . እምም. እሳቸው ሰው ያናድዳሉ እንጂ አይናደዱም።"
ዕድሜን በሳይንስ እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል?
በተለያዩ ጊዜያት እንደ ኮሎኔል ሪጃል በዕድሜ እንደገፉ የሚናገሩ ሰዎች የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ያገኛሉ። ከዚህ ቀደም ኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ውስጥ የ165 ዓመት የዕድሜ ባለ ጸጋ ነኝ ያሉትን ግለሰብ መጥቀስ ይቻላል።
ሆኖም እነዚህ ግለሰቦች ዕድሜያቸው እንደሚሉት ስለመሆኑ እስከአሁን በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም። ኮ/ል ሪጃል ግን የኮሪያ መንግሥት ከዚህ ቀደም ገንዘብ ሊሰጠኝ ፈልጎ ዕድሜዬን ማመን ስለቸገራቸው ከጥርሴ ናሙና ወስደው መርምረው እኔ ስለመሆኔ አረጋግጠዋል። ዕድሜዬንም 101 ገምተውታል ብለዋል። ከዚያ በኋላ ገንዘብ እየተከፈላቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
የኮሎኔል ሪጃል ዕድሜና አካል አለመመሳሰል በተመለከ ያነጋገርናቸው ዶ/ር ኑረዲን ሉኬ ዕድሜ በትክክል የሚታወቅበት ሳይንሳዊ መንገድ እንዳለ ያረጋግጣሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ዓይነት የዕድሜ ይገባኛል ጉዳይ አጋጥሞ ስለማወቁ እንደማያውቁ የሚናገሩት ዶክተሩ፤ አስገድዶ መድፈር የተፈፀመባቸውና ያለዕድሜ ጋብቻ የተዳረጉ ሴቶች ዕድሜ ለማረጋገጥ ግን ምርመራ እንደሚደረግ ይናገራሉ።
ዕድሜያቸው ከ22 ዓመት በታች ለሆኑት በተለይ በክንድና በእጅ አንጓ በሚሠራ የራጅ ምርመራ መረጃ ይገኛል። ነገር ግን ከዚያም በላይ ለሆኑት "200 ናኖ ግራም የሚሆን ዘረ መል ተወስዶ የሚደረግ ምርመራ ይኖራል" ይላሉ። ይሁን እንጂ በአገር ውስጥ እንዲህ ዓይነት አሠራር ስለመኖሩ ወቅታዊ መረጃ እንደሌላቸው ነግረውናል።
የዚህ ዓይነት የዘረ መል ምርመራ የስህተት ህዳግ 5 ዓመት ሲሆን ከ22 ዓመት በታች ለሆናቸው የሚደረገው የራጅ ምርመራ የስህተት ህዳጉ ሁለት ዓመት ብቻ እንደሆነም አስረድተዋል።
የኮ/ል ሪጃልን ሁኔታና ዕድሜዬ ነው የሚሉትን ቁጥር ጠቅሰን ያነጋገርናቸው ሌላው ባለሞያ ዶ/ር ዳንኤል ናቸው። ዶ/ር ዳንኤል በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፌዲዮሎጂ ስፔሻሊስት ሲሆኑ እዚያው ትቁር አንበሳ በመምህርነትም ያገለግላሉ።
ዶ/ር ዳንኤል እንደሚሉት በኢሜጂንግ (ራጅ፣ ኤም አይ አር እና ሲቲ ስካንን ይጨምራል) በመጠቀም የኮ/ል ሪጃልን ዕድሜ ልናውቅ የምንችልበት እድል የለም። ይህም የሚሆነው የርሳቸው አጥንት እድገቱን ከጨረሰ ረዥም ጊዜ በመሆኑ ነው። በነዚህ የኢሜጂንግ ዘዴዎች በመጠቀም 95 ከመቶ ትክክለኛ ዕድሜ መናገር የሚቻለው አጥንታቸው በእድገት ላይ ያሉ ወጣቶች ላይ ነው። ይህም ዕድሜያቸው በሀያዎቹና በአስራዎቹ የሚገኙትና ከዚያ በታች ያሉትን ያጠቃልላል።
ብዙዎቹ አጥንቶቻችን ዕድገት በጊዜ ሲያቆም ከ25 እስከ 30 ዓመት ዕድሜ ድረስ እድገት የሚያሳዩ አጥንቶቻችን መቀመጫችንን የሚሸከሙና ወገባችንና መቀመጫችን መሐል የሚገኝ አጥንት እንዲሁም ከትከሻ ወደ መሀል የሚወርደው አጥንት ነው ይላሉ ዶ/ር ዳንኤል።
የኮ/ል ሪጃልን ዕድሜ ማወቅ የሚቻልበት ዕድል አገር ውስጥ ይኖር እንደሁ የተጠየቁት ዶ/ር ዳንኤል ምናልባት በሆርሞንና ቦንዴሴቶሜተር በሚባል ዘዴ የካልሺየም መጠንን በሚለካ መንገድ ፍንጭ ሊገኝ እንደሚችልና ይህ ግን እኛ አገር ስለመኖሩ እርግጠኛ እንዳልሆኑ ነግረውናል።
ቢቢሲ አማርኛ ኮ/ል ሪጃል ነኝ የሚሉትን ዕድሜ በተመለከተ የሚያቀርቧቸው የሰነድ መረጃዎችን በገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።














