ተዋናይቷ በ54 ዓመቷ ሴት ልጅ ተገላገለች

ተዋናይት ብሪጌት ኒልሰን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሪጌት ኒልሰን ትባላለች። ዴንማርካዊት ስትሆን ዕውቅ ተዋናይት ናት። አምስተኛ ልጇን በ54 ዓመቷ ከሰሞኑ ተገላግላለች። አራቱ ልጆቿ ሁሉም ወንዶች ነበሩ።

ጣሊያናዊው ባለቤቷ የ39 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን ባለቤቱ በ54 ዓመቷ ልጅ ስለወለደችለት "ደስታዬ ወሰን የለውም" ሲል ተናግሯል።

ብሪጌት ኒልሰን ብዙ ሰው የሚያውቃት "Rocky IV" እና "Cobra" በተሰኙት በተለይም ከሁለተኛ ባሏ ሲልቨስተር ስታሎን ጋር መሪ ተዋናይት ሆና በተወነችባቸው ፊልሞች ነበር።

ኒልሰን በፊልም ብቻም ሳይሆን በሞዴሊንግና በቴሌቪዥን ትዕይንቶች ዓለም አቀፍ ዝናን ተቀዳጅታለች።

ሁለቱ ጥንዶች ለፒፕል መጽሔት እንደተናገሩት አዲስ ልጅ በማግኘታቸው ደስታቸው ወሰን አጥቷል።

ኒልሰን የ39 ዓመቱን ዴሲን ያገባችው በ2006 ሲሆን አምስተኛ ባሏ ነው።

ቀደም ያሉት አራት ልጆቿ ከ23 እስከ 34 ዕድሜ ያላቸው ሲሆን ሁሉም ወንዶች ነበሩ። ኒልሰን ነፍሰ ጡር ስለመሆኗ በማኀበራዊ መገናኛ ብዙኃን ስትገልጽ ሰፊ መነጋገሪያ ለመሆን ችላ ነበር።

በ2008 የአደንዛዥ ዕጽ ሱሰኞች ማገገሚያ ውስጥ ገብታ እንደነበር ይታወሳል።

በዚህም ብሪጌት ኒልሰን ዕድሜያቸው ከገፉ በኋላ የወለዱ ዕውቅ ሰዎችን ቡድን ተቀላቅላለች። ጃኔት ጃክሰን ባለፈው ዓመት በ50 ዓመቷ ልጅ ያገኘች ሲሆን ሬችል ዊዝ በተመሳሳይ በ48 ዓመቷ ልጅ እየጠበቀች ነው።