ቻይና ዜጎቿን ለኮሮናቫይረስ የባሕል መድኃኒት እንዲወስዱ ለምን ታበረታታለች?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በመላው ዓለም የሚገኙ ሳይንቲስቶች ለኮቪድ-19 ፈውስ የሚሆን መድኃኒት ለመቀመም ሩጫ ላይ ናቸው።
ቤይጂንግ በበኩሏ በዚህ ፈታኝ ሰዓት የባሕል መድኃኒቶቿን ከፍ ከፍ ማድረግ ሥራዬ ብላ ተያይዛዋለች።
ሰሞኑን በቻይና መንግሥት የተሰራጨ አንድ መረጃ እንደሚያትተው "በወረርሽኙ ከተያዙት 92 እጅ የሚሆኑት ቻይናዊያን በአንድም ሆነ በሌላ ሁኔታ ሊፈወሱ የቻሉት የቻይና ባሕላዊ ሕክምና ረድቷቸው ነው" ይላል።
የቻይና የባሕል ሕክምና በዓለም ላይ ረዥም ክፍለ ዘመን ያስቆጠረና ውስብስብ ታሪክ ያለው ነው።
ከሥራ ሥርና ከቅጠላ ቅጠል ቅመማ ጀምሮ እስከ ቻይና ደረቅ መርፌ ሕክምና (አኩፓንቸር) እንዲሁም ታይ ቺ (ከማርሻል አርት ጋር የተያያዘ በባሕላዊ ስፖርት እንቅስቃሴ ፈውስ የማግኘት ሂደት)፤ እነዚህ ሁሉ የቻይና ባሕላዊ ሕክምና ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።
ታይ ቺ አእምሮንና ሰውነትን የማዋሀድና የማናበብ እንቅስቃሴ ነው።
በቻይና ኅብረተሰብ ውስጥ የባሕል ሕክምና ሰፊ ተቀባይነት ያለው ሲሆን፤ ከአባት ወደ ልጅ ከትውልድ ትውልድ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣና በቻይናዊያን ባሕል ውስጥ ሰፊ ቦታ የሚሰጠው ነው።
አሁን አሁን ግን ነገሩ ተቃውሞም እየገጠመው ይመስላል።
በተለይ የባሕል ሕክምናው ሳይንስን ገሸሽ ማድረግ ሲጀምር ነገሩ ደስ ያላሰኛቸው የአዲሱ ትውልድ አባላት "ኧረ ይሄ ነገር መስመር ሳተ" ማለታቸው አልቀረም።
ቻይና የአሁኑን የወረርሽ ዘመን አስታካ ዘመናት ያስቆጠረውን ይህን የባሕል ሕክምና በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ገናና እንዲሆንላት ጥርሷን ነክሳ፣ መቀነቷን ሸብ አድርጋ በመስራት ላይ ያለች ትመስላለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቻይና የብሔራዊ ጤና ኮሚሽን ለምሳሌ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ባሳተመው የጤና መመርያ መጽሐፍ ላይ የባሕል ሕክምና አንድ ራሱን የቻለ ምዕራፍ እንዲይዝ አድርጎታል።
የአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ በበኩሉ የቻይና የባሕል ሕክምና ከዚህ ቀደም የሳርስ ወረርሽኝ በተቀሰቀሰበት በ2003 አካባቢ እንዴት ቻይናዊያንን እንደታደገ አበክሮ ማስገንዘብ ይዟል።
በጤና መመርያው ላይ ለምሳሌ ወረርሽኙን ለመታደግ ስድስት የባሕል ሕክምና ዘዴዎች እንዳሉ ያብራራል። ከእነዚህ መካከል ሁለቱ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ነበር።
የመጀመሪያው ሉዋንሁዋን ኪንጉዌን የተሰኘው የባሕል ሕክምና ነው። ይህ መድኃኒት የሚዘጋጀው ከ13 የሥራ ሥርና የቅጠላ ቅጠል ጭማቂ ነው። በተለይም ፎርቴሲያ የተሰኘው ባለ ቢጫ ቀለም ተክል እና ሮዲዮላ ሮዝ ቅጠል ፍቱንነታቸው ከፍ ያለ እንደሆነ ይነገራል።
ሌላው ደግሞ ጂንሁዋ ኪንጋን ነው። ይህ በ2009 ለተቀሰቀሰው ሌላ ወረርሽኝ ፈውስ ሆኖ ነው የቆየው። የሚዘጋጀው ከቀረፋ፣ ሀኒሳክል ከተሰኘ ቅጠል፣ ከሱፍ እና ከተልባ ነው።
የቻይና የባሕል ሕክምና ደጋፊዎች እነዚህን የተቀመሙ መድኃኒቶች ለኮሮናቫይረስ ማስታገሻ መጠቀም ፈውስ ያስገኛል ሲሉ፤ ሌሎች በበኩላቸው መድኃኒቶቹ በእርግጥም ፈውስ ስለማስገኘታቸው ሳይንስ በቤተ ሙከራ ሊያረጋግጣቸው ይገባል ይላሉ።
የአሜሪካ ብሔራዊ የጤና ኢንስቲትዩት በበኩሉ እነዚህ የባሕል መድኃኒቶች የበሽታ ምልክቶችን በማስታገስ ረገድ ምጥን ሚና ቢኖራቸውም ኮሮናቫይረስን ይፈውሳሉ ወይ የሚለው ግን ገና የሚጣራ ነው ብሏል።
በጉዳዩ ላይ በኔቸር የሳይንስ ጆርናል ላይ ኤዲዛርድ ኤርነስት የተባሉ የዩናይትድ ኪንግደም ተመራማሪ እንደጻፉት ደግሞ የቻይና የባሕል ሕክምና ፈውስ ማምጣቱ ይቅርና አደገኛ ነው፤ ሊወሰድም አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።
ተመራማሪዋ ይህን ይበሉ እንጂ የቻይና ሕክምና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቻይና አገር ብቻም ሳይሆን በመላው ዓለም ተፈላጊነቱ በእጥፍ ጨምሯል።
የቻይና ስቴት ካውንስል ባለፈው ዓመት ባወጣው አንድ መረጃ የቻይና ባሕላዊ ሕክምና ኢንዱስትሪ 420 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመት ይፋ አድርጎ ነበር።
የቻይና ፕሬዝዳንት ሺ ደግሞ በቻይና ሕክምና ዙርያ ጠንካራ የደጋፊነት መንፈስ እንዳላቸው ይነገራል። እንዲያውም በአንድ ወቅት "የቻይና ባሕላዊ ሕክምና የቻይና ሥልጣኔ ሕያው ቅርስ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
ቻይና በርካሽ ምርቶቿም ሆነ በብድር ቀፍድዳ ታዳጊ አገራትን በጉያዋ አድርጋ የድጋፍ መሰረቶቿ እንዲሆኑ እንደምትሞክረው ሁሉ፤ ይህን የባሕል ሕክምና በመላው ዓለም በማስተዋወቅ አዲስ ምዕራፍ፣ አዲስ ግንባር፣ አዲስ እቅድ ይዛ ተነስታለች።
ቤይጂንግ ይህን ባሕላዊ ሕክምና በተቀረው ዓለም ለማስተዋወቅ ብዙ ብትጥርም ሰምሮላታል ለማለት ግን ይከብዳል። በቢሊዮን የሚቆጠሩ የዓለም ሕዝቦች አሁንም ቢሆን የቻይና የባሕል ሕክምና ምን እንደሆነ አያውቁም። እንኳንስ ሊሞክሩት በጭራሽ ሰምተውት የማያውቁ ብዙ ናቸው።
ቻይና ይህን ወረርሽኝ ከለላ በማድረግ ባሕላዊ ሕክምናዋን ለማስተዋወቅ መሞከሯን ብዙዎች አልወደዱላትም።
በችግር ውስጥ ፖለቲካዊና ባሕላዊ ትርፍ እንደማጋበስ አድርገው ነው የተመለከቱት። ቻይና ግን ይህን ታስተባብላለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይና በአሁኑ ሰዓት በድጋፍ ስም ከዘመናዊ የሕክምና ቁሳቁሶች ጋር ቀላቅላ የባሕል መድኃኒቶቿን ከባሕል ሐኪሞቿ ጋር አጣምራ ወደ ታዳጊ የእስያ፣ የአፍሪካና የምሥራቅ አውሮፓ አገራት እየላከች ትገኛለች።
"የቻይናን ልምድ ማካፈል እንፈልጋለን፣ ለኮቪድ-19 የቻይናን መፍትሄ ለዓለም ማጋራት እንፈልጋለን፣ በዚህም የተቀረው ዓለም የቻይናን መድኃኒቶች እንዲሞክቸው እንሻለን" ብለዋል የቻይና ብሔራዊ የባሕልም ሕክምና አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ዩ ያንሆንግ።
ሚስተር ዮንግ ቻይና የባሕል መድኃኒቶቿን የእጅ አዙር ኃያልነት ማሳያና ተጽእኖ መፍጠሪያ እያደረገቻቸው እንደሆነ አይክዱም።
"በወረርሽኙ ቁጥጥር የቻይናን አካሄድ ውጤታማነት፣ የምዕራቡን ዓለምን ደግሞ ውጤት አልባነት አስታከን የቻይና የባሕል ሕክምና እንዲታወቅ እየሰራን ነው" ይላሉ ምክትል ፕሬዝዳንቱ።
የቻይና የባሕል ሕክምና በዓለም ጤና ድርጅት ዘንድ ባለፈው ዓመት አድናቆት ማግኘቱ ለሌላ እውቅና አብቅቶታል።
ብዙዎች የዓለም ጤና ድርጅት ለቻይና የባሕል ሕክምና የሰጠውን አድናቆት አሳሳች ሲሉ ተችተውት ነበር።
የዓለም ጤና ድርጀት በዓለም ዙርያ በነበሩ የባሕል ሕክምናዎች ላይ የ"ተጠንቀቁ" መልዕክት ሲያሰራጭ በቻይና የባሕል ሕክምና ዙርያ ግን ይህንኑ ተመሳሳይ መልዕክቱን ከእንግሊዝኛና ከቻይንኛ ቋንቋዎች ላይ ማንሳቱ ትዝብት ውስጥ ጥሎት እንደነበር ይታወሳል።
አንዳንዶች ድርጅቱ በቻይና ተጽዕኖ ሥር ወድቋል ሲሉ ይህንኑ እንደማስረጃ ያቀርባሉ፤ ይተቹታልም።
የቻይና ባሕል ሕክምና ጥብቅ ሳይንሳዊ የቤተ ሙከራ ሂደቶችን ያላለፈ በመሆኑ በዓለም ዙርያ ተቀባይነቱ እንደልብ እንዳይሆን አድርጎታል።
ባሳለፍነው ግንቦት የስዊድን ቤተ ሙከራ ሊንሁዋ ኪንግዌን የተሰኘውን የቻይና የባሕል መድኃኒት በቤተ ሙከራ በማስገባት ምርምር ያደረገበት ሲሆን፤ ከዚህ ውህድ ውስጥ ማግኘት የቻለው ሜንቶል የተባለን የቀረፋ ሽታ ያለው ንጥረ ነገር ብቻ ነው። ለመድኃኒትነት የሚያበቃ ምንም ነገር ሳያገኝበት ቀርቷል።
የቻይና የባሕል ሕክምና በብዝኃ ሕይወት ለይ አደጋ እንደቀነ የሚናገሩም አልጠፉም።
ከቻይና ሕዝብ ብዛት አንጻር አንዳንድ የባሕል መድኃኒቶችን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ለማግኘት በብርቅዬ እንሰሳት ላይ የሚፈጸም አደን እንዲበራከት አድርጓል።
ለምሳሌ የቻይና ብሔራዊ ጤና ኮሚሽን የድብ ሐሞት ፈሳሽን የያዘ ውህድ መወጋት የኮሮናቫይረስን መከላከል ጥሩ ነው በማለቱ፤ እንዲሁም ከፓንጎሊን ተራማጅ እንሰሳ ቅርፊት መድኃኒት ይሰራል የሚል እምነት በመንሰራፋቱ በእነዚህ ላይ አደን በርክቶ ነበር።
መድኃኒትን በፕሮፓጋንዳ?
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቻይና መንግሥትና የቻይና መገናኛ ብዙሃን ባሕላዊ ሕክምናቸውን በማስተዋወቅ ረገድ ከመጠን ያለፈ ዘመቻ መክፈታቸው ሌላ ያልታሰበ ጣጣ ይዞባቸው መጥቷል።
ለምሳሌ በዩናን አውራጃ በወረርሽኙ ምክንያት ወደ ትምህርት ቤት ዝር እንዳይሉ የተነገራቸው ተማሪዎች ወረርሽኙ ጋብ ሲል ወደ ትምህርት ገበታ ሊመለሱ ሲሉ የባሕላዊ መድኃኒት ካልተጋታችሁ ትምህርት ቤት መግባት አትችሉም ተብለው ነበር።
በቤይጂንግ የከተማ አስተዳደር ደግሞ አንድ ሕግ ረቂቅ ላይ ደርሶ ነበር። ረቂቅ ሕጉ የቻይና የባሕል ሕክምናን የሚያጥላላ ማንኛውም ቻይናዊ ለፍርድ እንዲቀርብ የሚጠይቅ ነው።
እነዚህ የቅርብ ጊዜ ክስተቶች የቻይና የባሕል ሕክምና ጉዳይ በዚያች አገር አዲስ የውይይትና የክርክር ምዕራፍ እንዲከፈት ምክንያት ሆኗል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም 'የቻይና ባሕል ሕክምና ሳይንስ ነው ወይስ አይደለም?' የሚለው ሙግት ማኅበራዊ የመገናኛ መድረኮችን አጥለቅልቆታል።
"ሳይንስ ለተጠየቅ ክፍት ነው፤ የቻይና ባሕል ሕክምና ለተጠየቅ ዝግ ነው። ስለዚህ የቻይና የባሕል ሕክምና ሳይንስ አይደለም" ይላል አንድ የዌቦ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ።
ዶ/ር ሊዮ በበኩላቸው በዚህ መንገድ ሙግቱን ይዘጉታል።
"አንድ መድኃኒት በሳይንስ እንጂ በፕሮፓጋንዳ ኃይል ፈዋሽነቱ አይረጋገጥም።"














