ኮሮናቫይረስ፡ ቻይና ቤይጂንግ አቅራብያ የቫይረሱ ስርጭት በመጨመሩ 400 ሺህ ሰዎች እንዳይንቀሳቀሱ አገደች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይና በቤይጂንግ አቅራቢያ በተከሰተ አነስተኛ የቫይረስ ስርጭት ምክንያት ዳግመኛ የእንቅሰቃሴ ገደብ በመጣሏ 400 ሺህ ሰዎች መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ተገለፀ።
ይህ የእንቅስቃሴ ገደብ የተጣለው በቤይጂንግ አቅራቢያ በምትገኘው አንዢን ግዛት፣ ሂቤይ ከተማ መሆኑ ተነግሯል።
ባለፈው የህዳር ወር መጨረሻ ላይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ እና በቁጥጥር ስር ከዋለ ወዲህ በቻይና የቫይረሱ ስርጭት በጣም ቀንሶ ይገኛል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዳግም እንዳይከሰት በሚል ፍራቻ ምንም እንኳ አነስተኛ ቢሆንም በቫይረሱ የተያዘ ሰው በሚገኝበት የትኛውም ስፍራ ላይ ጥብቅ የጤና ባለሙያዎች እርምጃዎች ይወሰዳሉ።
የሂቤይ ከተማ ባለስልጣናት እሁድ እለት ከተማዋ "ሙሉ በሙሉ ዝግ እና በቁጥጥር ስር" እንደምትቆይ አስታውቀዋል።
ይህ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ የቫይረሱ ወረርሽኝ በዉሃን ተከስቶ በነበረበት ወቅት ታውጆ እንደነበረው ያለ ነው ተብሏል።
ይህም ማለት በሥራ ባህሪያቸው የተነሳ አስፈላጊ የሆኑ ሰዎች ብቻ ከቤታቸው እንዲወጡ የሚፈቀድላቸው ሲሆን፣ ከአንድ ቤተሰብ አንድ ሰው ብቻ አስፈላጊ እቃዎችን ለመግዛት ብቻ እንዲወጣ ይፈቀድለታል።
አንዢን ከቤይጂንግ በደቡብ አቅጣጫ 150 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ ናት። የቻይና መገናኛ ብዙሃን በአንዢን በቤይጂንግ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከተከሰተው የቫይረሱ ስርጭት ወዲህ 18 ሰዎች ተይዘው መገኘታቸውን ዘግበዋል።
ባለፉት 24 ሰዓታት በቤይጂንግ 14 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ ሲረጋገጥ ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ በምግብ መሸጫ አካባቢ ከተከሰተው ጋር ስርጭት ጋር ሲደመር 311 ያደርሰዋል።
ምንም እንኳ ይህ ቁጥር በአሜሪካ እና ደቡብ አሜሪካ አገራት ከተከሰተው አንጻር አነስተኛ ቢሆንም ቻይና ግን በፍጥነት እርምጃ ወስዳለች።
የሂቤይ ከተማ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን በቤይጂንግ አቅራቢያ ያሉ ከተሞች የእንቅስቃሴ ገደብ የጣሉ ሲሆን የኮሮናቫይረስ ምርመራም ማድረግ ጀምረዋል።
በቅርብ ጊዜ ከተከሰተው የቫይረሱ ወረርሽኝ በፊት ቻይና አንድም በቫይረሱ የተያዘ ሰው ሳታስመዘግብ 57 ቀናት ቆይታ ነበር።
በአጠቃላይ ቻይና ቫይረሱን በመቆጣጠር ሂደት የተሳካ የተባለ እርምጃ ወስዳለች።
በመጋቢት ወር 80 ሺህ ሰው መያዙ ከተመዘገበ ወዲህ እስካሁን ድረስ 4700 ሰዎች ብቻ ናቸው ተይዘው መገኘታቸው በምርመራ የተረጋገጠው።
እስከ ሰኔ መጨረሻም ቢሆን አዳዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች የተገኙት በቤይጂንግ ሲሆን አንዳንድ ሰዎች በሂቤይ ከተማ ተገኝተው ነበር።
ቀሪው የቻይና ግዛቶችና ከተሞች ግን በጣም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ከሌላ ስፍራ የመጡ ግለሰቦች ተይዘው ከመገኘታቸው ውጪ ቻይና ቫይረሱን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ችላለች።













