የ15 ዓመት ታዳጊ እያሉ ታስረው በ83 ዓመታቸው የተፈቱት አዛውንት

ጆ ሊጎን

የፎቶው ባለመብት, Pennsylvania Department of Corrections

የምስሉ መግለጫ, ጆ ሊጎን

የ15 ዓመት ታዳጊ እያሉ በፈጸሙት ወንጀል ለ68 ዓመታት ታስረው በመጨረሻ የእድሜ ዘመናቸው የተፈቱት ጀ ሊጎን አሁን 83 ዓመታቸው ነው።

ለሰባት አስርት ዓመታት ያህል የእድሜያቸውን ከሦሰት አራተኛ በላይ በእስር ቤት ያሳለፉት አዛውን ተለቀው ወደማያውቁት ዓለም ተቀላቅለዋል።

በአስር ቤት "ብቻዬን ሆኜ ባላውቅም ብቸኛ ነኝ። ብቻዬን መሆንን እመርጣለሁ።"

"ከታሰርኩበት ጊዜ ጀምሮ እስከምለቀቅ ድረስ አንድ ክፍል ውስጥ ነበር የቆየሁት።"

በአንድ ክፍል መታሰር "እንደ እኔ ብቸኝነትን ለሚፈልጉ" የተሻለው አማራጭ ነው ይላል ጆ ሊጎን።

ታሠረ ታሠረ። በሩ ከተከረቸመበት በኋላ "ውጭ የሚከናወነው ሁሉ አላይም አልሰማም።"

ብቸኝነቱን ያስቀሩለት ሬዲዮና ቴሌቪዥኑ ሲፈቀድላቸው ነበር።

የእስር ቤት ሕይወት ለጆ ሊጎን የተስማማው ይመስላል። የ68 ዓመቱ እስር አንገቱን ደፍቶ፣ አፉን ዘግቶ እና ከችግሮች እንዲላቀቅ አስተምሮታል።

ብቸኛ መሆኑን የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ስለሚያምን ዕድሜ ልክ በአንድ ክፍል ተቆልፎበት መቆየቱ አላሳሰበውም።

ከእስር ቤትም ውጭም ጓደኛ አልነበረውም።

"ያገኘኋቸውን ብዙ ሰዎች… እንደ ጓደኛ እንዳደረኳቸው ነበር የሚቆጥሩት። አሪፍ ነገር ነበረን። ጥሩ ግንንኙነትም ነበረን" ይላል።

"ቃሉ ከፍ ያለ ትርጉም ስላለው ጓደኛ የሚለውን ቃል ግን አልጠቀምም። ብዙ ሰዎች [ጓደኛ ካበዛችሁ] ትልቅ ስህተት ልትሠሩ ትችላላችሁ ይላሉ" ሲል ያስረዳል።

ሊጎን ብቸኛ የሚባል ዓይነት ሰው ነበር።

በአላባማ በበርሚንግሃም ቅድመ አያቶቹ ዘንድ ነው ያደገው። ብዙ ጓደኛ አልነበረውም።

በቤተሰቦቹ ዘንድ አስደሳች ጊዜያትን ማሳለፉን ያስታውሳል። ከእነዚህ አስደሳች ጊዜያት መካከል እሁድ እሁድ ቤተክርስቲያን ውስጥ አያቱ ሲሰብኩ መመልከቱ ነው።

በኋላም አካባቢውን ቀየረ።

ከነርስ እናቱ፣ ከመካኒክ አባቱ፣ ከታናናሽ ወንድም እና እህቱ ጋር ለመኖር ወደ ፊላዴልፊያ አቀና። ያኔ 13 ዓመቱ ነበር።

ከትምህርት ጋር አይንና ናጫ ነበረ። ማንበብም ሆነ መፃፍ አይችልም።

ስፖርትም አያስደስተውም።

ጓደኞቼ የሚላቸውም በባህሪ የሚግባቡት አልነበሩም።

"ብዙ አልዝናናም። አንድ ወይም ሁለት ጓደኞች ያሉኝ ዓይነት ሰው ነበርኩ። ብዙ ሰው ወደተሰበሰበበት አልሄድም" ይላል።

ሊጎን መቼም የጎርጎሮሳዊያኑን 1953 አንድ ዓርብ ምሽትን አይረሳትም። "ችግር ውስጥ የከተተችው" ነበረች።

በዕለቱ አብረውት የነበሩትን በትክክል አያውቃቸውም።

በአጋጣሚ ከሚያውቃቸው ሁለት ሰዎች ጋር ሰፈራቸው ውስጥ ዞር ዞር ሲሉ ነበር ከሚጠጡ ሰዎች ጋር ተገናኙ።

ተቀላቅለው "ተጨማሪ ወይን ለመግዛት ሰዎችን ጥቂት ገንዘብ መጠየቅ ጀመርን . . . እናም አንዱ ነገር ወደ ሌላው አመራ…"

መጨረሻው ያላማረ ምሽት። አለመግባባት ተፈጠረ- ሁለት ሰዎች ሲገደሉ ስድስቱ ቆሰሉ።

እሱም በግጭቱ ተሳታፊ ነበር።

ሊጎን ነበር መጀመሪያ ዘብጥያ የተወረወረው።

ጆ ሊጎን

የፎቶው ባለመብት, Bradley S Bridge

የምስሉ መግለጫ, ጆ ሊጎን 68ቱን እስር ዓመታት በስድስት አስር ቤቶች አሳልፈዋል

ፖሊስ ጣቢያው ማን አብሮት እንደነበረ እውነቱን መናገር እንደማይችል ለፖሊስ ይናገራል።

"ሁለቱ የማውቃቸውን እንኳን ትክክለኛ ስማቸውን አላውቀውም። በቅጽል ስማቸው ነበር የምጠራቸው" ይላል።

ሊጎን በሮድመን ጎዳና ከሚገኘው ቤታቸው ርቆ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ነበር የተወሰደው።

ለአምስት ቀናትም የሕግ ድጋፍ አላገኘም።

ወላጆቹ ሊጠይቁት ሲሞክሩም መከልከላቸው ለረዥም ጊዜ አስቆጥቶት እንደነበር ይናገራል።

በዚያው ሳምንት የ15 ዓመቱ ታዳጊ በግድያ ወንጀል ተከሰሰ። እሱ ክሱን አልፈጸምኩም አለ።

በኋላም ሁለት ሰዎችን በስለት መውጋቱን ከአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ፒቢኤስ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ገለጸ። ሁለቱም በሕይወት መትረፋቸውንና መጸጸቱንም አስረዳ።

"[ፖሊሶቹ] እንድንፈርም ጽሑፎች ሰጡን። ጽሑፉ እኔ በግድያው መሳተፌን ይገልጻል። እኔ ግን ማንንም አልገደልኩም።"

ፔንሲልቬንያ በዕድሜ ልክ እስራት ላይ አመክሮ ከሌላቸው ስድስት የአሜሪካ ግዛቶች አንዷ ናት።

ሊጎንን ጉዳዩን ሲያምን ዳኛውም በአንደኛ ደረጃ ግድያ ሁለት ክሶች ጥፋተኛ ይሉታል።

ታዳጊው ያለአመክሮ ዕድሜ ይገፍታህ ተረደበት። ፍርድ ቤት ሆኖ ግን ውሳኔውን አልሰማም።

ቅጣቱ ከጊዜው አንጻር የተለመደ የሚባል ነው። ቅጣቱን በውል ሳያውቀው ወደ እስር ቤት ወረደ። ማንንም የመጠየቅ ዕድልም አላገኘም።

"ምን መጠየቅ እንዳለብኝ እንኳን አላውቅም ነበር። ለማመን ከባድ ቢሆንም እውነታው ያ ነበር። ህይወቴን በሙሉ እስር ቤት እንደምሆን አላውቅም ነበር። 'አመክሮ ያለው ዕድሜ ልክ' የሚሉ ቃላትን ሰምቼም አላውቅም" ይላል ሊጎን።

"ልጅነቴ ምን ያህል የተበላሸ እንደነበር መናገር እፈልጋለሁ። ማንበብም ሆነ መጻፍ አልችልም። ስሜን እንኳን መፃፍ አልችልም ነበር። ስሜ ጆ መሆኑን አውቅ ነበር። እኔ እስከ ማስታወሰው ድረስ በጆ ነበር የምጠራው።"

ከመፍራት ይልቅ ግራ ተጋብቶ ወደ ማረሚያ ቤቱ እንደገባ ሊጎን ይናገራል። በአዕምሮው የሚመላለሰው ነገር ቤተሰቡ ነበር። "ከእነሱ ርቆ በአንድ ክፍል ታጥሮ መቀመጥ። ይህ ነበር የማስበው ጉዳይ" ይላል።

ጆ ሊጎን ከአባቱ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Bradley S Bridge/Joe Ligon

የምስሉ መግለጫ, ጆ ሊጎን አባቱ ሜካኒክ እናቱ ደግሞ ነርስ ነበሩ

ከ68 ዓመታት በላይ በስድስት እስር ቤቶች አሳልፏል። ሁሌም ከማረሚያ ቤቱ ህይወት ጋር ራሱን ያለማምዳል።

"ጠዋት 12 ሰዓት በጥሩምባ እንቀሰቀሳለን። አሊያም በድምጽ 'ሁሉም ሰው ለመቆጠር ይነሳ፣ የመቁጠሪያ ሰዓት ነው' እንባላለን። አንድ ሰዓት የምግብ ሰዓት ነው፣ 2 ሰዓት ደግሞ የሥራ ሰዓት።"

ሊጎን አልፎ አልፎ በምግብ አብሳይነትና ልብስ ማጠቢያ ክፍል ውስጥ ቢሠራም በአብዛኛው የሠራው በጽዳት ሠራተኝነት ነበር።

ከምሳ በኋላ በድጋሚ ወደ ሥራው ይመልሳል።

እንደገና ምሽት ላይ በእራት ሰዓት በድጋሚ ጥሪ የተደርጎ የአንድ ቀን ከክፍሉ ውጭ ያለው ውሎው ማብቂያ ይሆናል።

የእስር ቤት ሕይወቱ በአብዛኛው ተመሳሳይ ቢሆንም የውጭው ዓለም በአስርተ ዓመታት ውስጥ የማይቀየር ለውጥ እያስመዘገበ ነው።

"አደንዛዥ ዕፅ አልተጠቀምኩም፣ አልጠጣም፣ ሰዎች እንዲገደሉ ምክንያት አልሆንኩም፣ ለማምለጥ አልሞከርኩም እንዲሁም ለማንም መጥፎ አልሆንኩም" በማለት ቆይታውን ያስታውሳል።

"በተቻለኝ መጠን በትህትና አሳለፍኩኝ። ማረሚያ ቤቱ ያስተማረኝ ስለራስ ማሰብን፣ ሁል ጊዜም ትክክለኛውን ለማድረግ መሞከርን እና ከመጥፎ ድርጊት መራቅን ነው" ብሏል።

በዚህ ሁኔታ 53 ዓመታት አለፉ።

በኋላ አንድ ጠበቃ ሊያየው እንደሚፈልግ ተነገረው። ግለሰቡ ብራድሌይ ኤስ ብሪጅ ይባላል።

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአውሮፓውያኑ 2005 ታዳጊዎች በግድያ ሊቀጡ አይገባም በሚል ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ፤ ብራድሌይ ኤስ ብሪጅ ያለ አመክሮ ዕድሜ ይፍታህ ስለተፈረደባቸው ታዳጊዎች መመርመር የጀመረ ባለሙያ ነው።

ጆ ሊጎን እና ጠበቃው ብሪጅ

የፎቶው ባለመብት, Bradley S Bridge

የምስሉ መግለጫ, ጆ ሊጎን እና ጠበቃው ብሪጅ

በወቅቱ ፔንሲልቬንያ በተመሳሳይ ሁኔታዎች ውስጥ የነበሩ 525 እስረኞች ነበሯት። እንደ ብሪጅ ከሆነ ቁጥሩ በአሜሪካ ከፍተኛው ነው። ፊላዴልፊያ 325 ሲኖራት ሊጎን ደግሞ ረዥም ዓመት የታሰረው ፍርደኛ ነው። ለዚህም ነው ረዳት ጠበቃው ሊያገኘው ቀጠሮ የያዘው።

ከፊላዴልፊያ ተከላካይ ጠበቆች ማኅበር የመጣው ብሪጅ "ስለ ፍርዱ በትክክል አያውቅም ነበር" ሲል ስለ ሊጎን ይገልጻል።

"እስካገኘው ድረስ ምንም አያውቅም ነበር። ተስፋ አለመቁረጡ አስደሳች ነገር ነው። ሙሉ በሙሉ ተስፋ ነበረው። ከመጀመሪያው ጀምሮ አንድ ነገር እንደሚፈጠር ይጠብቅ ነበር" ብሏል።

"እንዴት እንደማስረዳው ግን ግልፅ አልነበረም። ተስፋ ነበረው። ሊስተካከል ስለሚችል ቁጭ ብሎ ለመጠበቅ ፍጹም ታጋሽ ነበር" ይላል።

ውይይቱ ለሊጎን ዓይን ከፋች ነበር።

ብሪጅ ሁኔታውን የሚቃወምበትን የይግባኝ ቅጅ ሲያሳየው ነበር ሊጎን የእስሩን ዝርዝር መረጃ ለመጀመሪያ ያወቀው።

"ከተያዝኩበት ጊዜ አንስቶ በደል እየተፈፀመብኝ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ። ለወጣት ጥፋተኞች ያለአመክሮ መታሰር ሕገመንግሥታዊነትን የተፃረረ መሆኑን ተረዳሁ" ይላል።

ምንም እንኳን ሊጎን አንድ ቀን ከእስር ቤት መውጣት ስለመቻሉ የተስፋ ጭላንጭል ቢያይም ለ15 ዓመታት ለመረዳት የሚከብዱ ውሳኔዎችን ሲያደርግ ነበር።

ጆ ሊጎን

የፎቶው ባለመብት, Bradley S Bridge

የምስሉ መግለጫ, ጆ ሊጎን ከአስር እንደወጡ የውጪውን ዓለም ፈፍሞ እንደማያውቁት ይናገራሉ

"የዕድሜ ልክ መዘዝ" ያለው ነው ባለው ምክንያት የመፈታት ዕድል ገጥሞት ውድቅ አድርጎታል።

"የአመክሮ ቦርዱ ሁለት ጊዜ ጎብኝቶኝ ነበር። ከዓመታት በፊት የአመክሮ ምህረትን መቀበል አቋራጭ መንገድ ነበር።

"[ነገር ግን] ምህረቱ በቀሪው ህይወቴ በምሠራው ሥራ ላይ የተመረኮዘ ሲሆን የእኔ ጉዳይ ግን የዕድሜ ልክ አመክሮን አይጠይቅም ነበር። የእኔ ጉዳይ ያንን ቢጠይቅ ምንም ችግር አልነበረውም። ለዚያም ነው ያልተቀበልኩት" ሲል ያስረዳል።

እአአ በ2016 የአሜሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁሉም ወጣት ጥፋተኞች በድጋሚ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ይወስናል። ሊጎን በቀጣዩ ዓመት 35 ዓመታት ተፈረደበት።

በእስር ባሳለፈው ጊዜ ምክንያት የአመክሮ ጥያቄ የማቅረብ ዕድል ከፈተለት።

ብሪጅ ጥያቄውን እንዲያቀርብ ቢገፋፋውም እምቢታ ሆነ መልሱ።

"ከባልደረባዎቼ፣ ከአስተዳደር ሠራተኞች እና ከእስረኞች በጣም መጥፎ ምላሽ ነበር ያገኘሁት… 'ለምን አመክሮ አይጠይቅም? [ሁሉም ይሉ ነበር]" በማለት ሊጎን ያስታውሳል።

"እኔም 'የማድረግ የምችለውን ነገር አልቀበልም' እላለሁ። መጥፎ ለመሆን ወይም ክፉ ለመሆን [አላደረግሁትም] አሁንም ቢሆን አመክሮ የምቀበል ከሆነ እየተበደልኩ ነበር።"

"ሁሌም እነዚህን ቃላት ብቻ ነበር የምጠቀመው 'ነፃ ወጥተሃል መባልን እፈልጋለሁ'" ይላል።

ብሪጅ የ2017ቱን ውሳኔ መቃወም ነበረበት።

ጉዳዩን ወደ ፌዴራል ፍርድ ቤት ወስደው።

በ2020 እአአ ዳኛው ብሪጅን ደግፎ ውሳኔውን አስተላለፈ።

የካቲት 11 ቀን ሊጎንን ለመውሰድ ብሪጅ ወደ ሞንትጎመሪ ካውንቲ በሄደ ጊዜ የቀድሞው እስረኛ በአስደናቂ ሁኔታ የተረጋግቶ አገኘው።

"'ኦህ አምላኬ ጠንከር ያለ ምላሽ ጠብቄ ነበር። ግን ምንም ስሜት አልነበረውም። አንዳች ድራማ የለም - ምንም" ብሏል።

ሊጎን ምናልባትም ለአስርተ ዓመታት ያከናወነውን እያደረገ ነበር - ሃሳቦቹን በራሱ አምቆ መያዝ።

ከእስር ከተለቀቀ ከአንድ ወር በኋላ ግን ከፊኒክስ ማረሚያ ቤት የወጣበትን ቀን በሚያስደንቅ ሁኔታ ይገልጻል።

"እንደገና እንደመወለድ ነበር። ምክንያቱም ሁሉም ነገር ለእኔ አዲስ ነበር። ሁሉም ነገር [ተለውጧል]። ሁሉም ነገሮች አሁንም ለእኔ አዲስ እንደሆኑ ናቸው።"

"ከእነዚህ አዳዲስ መኪኖች መካከል የተወሰኑትን እመለከታለሁ። እነዚህ መኪኖች በፊት ከማውቃቸው መኪኖች ጋር ተመሳሳይ ንድፍ የላቸውም። እነዚህን ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች እመለከታለሁ ... አሁን እንደማያቸው ዓይነት ሕንፃዎች በፊት አልነበሩም።"

በክፍሉ ውስጥ እጆቹን እያወዛወዘ "ይህ ሁሉ አዲስ ነው" ይላል። "እለምደዋለሁ። እወደዋለሁ። ይህ ለእኔ አስደሳች ነው። ይህ በእውነት የሚያስደስት ነው" ይላል።

ሊጎን ያለፉትን 68 ዓመታት ዋጋ ከፍሎባቸዋል።

ያለ አመክሮ ለመለቀቅ ሲል ዓመታትን በእስር ማሳለፉን ያውቀዋል። ይህም ከቤተሰቦቹ ጋር ሊያሳልፍ የሚችለውን ጊዜ ከማሳጣት ባለፈ በዚህ ጊዜ ውስጥ ብዙ የቤተሰቦቹ አባላት ህይወት አልፏል።

"የእህቴ ልጅ ቫለሪ እስር ቤት በነበርኩበት ጊዜ ተወለደች። ታላቅ እህቷ እና ታናሿ እዚያው እያለሁ ተወለዱ። ሁሉም የቅርብ ቤተሰቦቼ አልፈዋል። አሁንም በሕይወት ያሉነው እኔ፣ [ቫለሪ] እና የቫለሪ እናት ብቻ ነን" ሲል ይገልጻል።

የ83 ዓመት አዛውንት ለረጅም ጊዜ ከጠበቀው ህይወት ጋር ራሱን እያዋሃደ ጥቂት ዕቅዶችንም እያወጣ ነው።

ለዚህም በደንብ የሚያውቀው ሥራ መሥራት ይፈልጋል።

"በሕይወቴ ዘመኔ በሙሉ የሠራሁትን ለመሥራት ዝግጁ ነኝ። የጽዳት ሠራተኛ በመሆኔ የጽዳት ሥራ ስጡኝ" ሲል ያጠናቅቃል።