ናይጄሪያዊቷ ፊልሟ ከኦስካር ሽልማት ውጪ መደረጉን ተቃወመች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ናይጄሪያዊቷ ተዋናይትና አዘጋጅ ጄኔቪቭ ናጂ ፊልሟ ከኦስካር ሽልማት ውጪ መደረጉን ተቃወመች።
"ላየንኃርት" የተሰኘው የጄኔቪቭ ፊልም ከኦስካር ምርጥ ዓለም አቀፍ ፊቸር ፊልሞች ዝርዝር ውጪ የተደረገው፤ በተዋንያኑ መካከል የተደረገው ንግግር "እንግሊዘኛ ስለሚበዛው" መሆኑ ተገልጿል።
የኦስካር አወዳዳሪ አካል እንዳለው፤ በዓለም አቀፍ ዘርፍ የሚወዳደሩ ፊልሞች መሠራት ያለባቸው ከእንግሊዘኛ ውጪ ባሉ ቋንቋዎች ነው።
"ላየንኃርት" ለኦስካር ውድድር የቀረበ የመጀመሪያው የናይጄሪያ ፊልም ነው። የፊልሙ ተዋንያን ወደ 11 ደቂቃ ገደማ በኢግቦ የሚያወሩ ሲሆን፤ የተቀረው የፊልሙ ክፍል የተሠራው በእንግሊዘኛ ነው።
በጎ ምላሽ ያገኘው ፊልሙ፤ አሁን ኔትፍሊክስ ላይ እየታየ ይገኛል። በሴት አዘጋጆች ተሠርተው ለኦስካር ከቀረቡ 93 ፊልሞች መካከል አንዱ ነው።
የፊታችን እሮብ በዓለም አቀፍ ፊልሞች ዘርፍ ለዕይታ እንደሚቀርብ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፤ ሰኞ ዕለት ከውድድር ውጪ መደረጉ ለአዘጋጆቹ በኢሜል ተነግሯቸዋል።
በፊልሙ ላይ የምትተውነው አዘጋጇ ጄኔቪቭ እንደምትለው፤ ፊልሙ ናይጄሪያውያን እንዴት እንደሚነጋገሩ ስለሚያሳይ ከውድድር ውጪ መደረግ አልነበረበትም።
"እንግሊዘኛ ናይጄሪያ ውስጥ ለሚነገሩ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ቋንቋዎች እንደ ድልድይ ነው። እንግዲህ ቅኝ ገዢዎቻችንን አልመረጥንም። እናም ፊልሙ የናይጄሪያ ነጸብራቅ ነው" ስትል በትዊተር ገጿ አስፍራለች።
በእንግሊዝ ቅኝ የተገዙ አገሮች እንግሊዘኛን በሥራ ቋንቋነት እንደሚገለገሉበት ይታወቃል።
ታዋቂዋ የሆሊውድ ፊልም አዘጋጅ ኤቫ ዱቭሪ፤ "ላየንኃርት" ከውድድር ውጪ መደረጉን ተቃውማለች። ናይጄሪያ የተሠሩ ፊልሞች ኦስካር ላይ እንዳይወዳደሩ ጫና እንደሚያሳድርም ኤቫ ተናግራለች።












