ተንቀሳቃሽ ስልክን አነስተኛ ባንክ የሚያደርገው ‘ቴሌ ብር’

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ

የፎቶው ባለመብት, Firehiwot Tamiru

ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ አስቤዛ ሸምተው አልያም ዕቃ ገዝተው ወይም የአገልግሎት ክፍያ ለመፈጸም ፈልገው 'ቱ ቱ' ብለው ገንዘብ መቁጠር ላይጠበቅብዎት ይችላል።

ከግብይትዎ በኋላ "እስኪ ስልክህን/ሽን ንገረኝ/ንገሪኝ" ብለው በተንቀሳቃሽ ስልክዎ አማካኝነት ክፍያ ሊፈጸሙ ይችላሉ።

በአጭሩ ስልከዎ አንድ የባንክ መስኮት የሚሰጠውን አገልገሎት ማቅረብ ይችላል። እንዴት?

ይህ በእጅ ስልክ ገንዘብ የማንቀሳቀስ አስራር በበርካታ አገራት የተለመደ ሆኗል።

ጎረቤት ኬንያ ከ14 ዓመታት በፊት የጀመረችው 'ኤምፔሳ' የተሰኘውን የሞባይል ገንዘብ ስርዓት አሁን ላይ 72 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ነዋሪ እየተጠቀመው ይገኛል ይላል ቮክስ ከተባል ድህረ ገጽ የተገኘ መረጃ።

በሰባት አገራት የሚሰራው ኤምፔሳ 42 ሚሊዮን ንቁ ደንበኞችና 400 ሺህ ወኪሎች አሉት።

50 በመቶ የሚሆነው የኬንያ ዓመታዊ ጥቅል ምርት [GDP] በዚሁ ስርዓት በኩል ይንቀሳቀሳል።

በኡጋንዳ ከጠቅላላ ህዝቡ የባንክ አካውንት ያለው 11 በመቶ ሲሆን ኤምፔሳን የሚጠቀመው ሰው ግን 42 በመቶ ተሸጋግሯል። እናም እነዚህ አገራት ከግብይት በኋላ ቁጥርህ/ሽን ንገረኝ ማለት የተለመደ ነው።

ከትናንት በስትያ [ማክሰኞ ግንቦት 3 - 2013] ይፋ የሆነው ቴሌብር መሰል አገልግሎትን በኢትዮጵያ የማቅረብ አላማ ይዟል።

የቴሌ ብር አርማ

የፎቶው ባለመብት, Firehiwot Tamiru

የኢትዮጵያ ሞባይል ገንዘብ አገልግሎት - ቴሌብር

ከቢቢሲ ጋር ቆይታ የነበራቸው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ኩባንያቸው ያሉትን መሰረተ ልማቶች ለድምጽ፣ ለጽሁፍ መልዕክትና ለኢንተርኔት አገልግሎት ብቻ ሲያውለው መቆየቱን አውስተዋል።

ታድያ ቴሌብር የተሰኘው አዲሱ አገልግሎት መሰረተ ልማቱን ገንዘብ ለመቀበል፣ ለመላክ፣ የግብይትና የአገልግሎት ክፍያን ለመፈጸምም እንዲውልና "ክፍያን ለማሳልጥ" እንዲያግዝም ያስችላል ሲሉ ያስረዳሉ።

በተጨማሪም የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ከውጪ ሀገራት ገንዘብ መቀበል ይችላሉ ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚዋ።

በኢትዮጵያ የፋይናንስ አገልግሎቶች በባንክና መሰል ተቋማት ብቻ እየተሰጠ የቆየ መሆኑን የሚገልጹት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ኢትዮ ቴሌኮም ደግሞ ከቴሌኮም አገልግሎት በተጨማሪ የፋይናንስ ስርዓት ላይ መሳተፍ የሚችልበት የህግ ማዕቀፍ አልነበረም ብለዋል።

"አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ስርአቱን ቢዘረጋም ከባድ ያደረገው ግን ኢትዮቴለኮም ይህንን አገልግሎት መስጠት እንዲችል የሚያደርገው የህግ ማዕቀፍ ለማሻሻል የሄድንበት ርቀት ግን ረጅምም አስቸጋሪም እንዲሁም ፈተናም የነበረበትም ነው ሲሉ" ተናግረዋል።

ሁለት ዓመት ከፈጀ "ውጣ ውረድ" በኋላ ግን ይህንን አገልግሎት መስጠት እንዲችል ኩባንያው የተቋቋመበት ደንብ ማሻሻያ ከተደረገበትና ከብሄራዊ ባንክ ፍቃድ ካገኘ በኋላ አገልግሎቱ በ10 ቀናት ውስጥ ይፋ መሆኑን ገልጸዋል።

መሰል ስርዓቶችን ለመዘርጋት ከ ሁለት እስከ ሶስት ዓመታት ሊፈጅ እንደሚችል ያነሱት ፍሬህይወት 'ሆኖም ፍቃድ እንደምናገኝ ተስፍ በማደረግ በአምስት ወራት ዝግጁ አድርገናል' ብለዋል።

ከባንኮች ወደ ቴሌብር የገንዘብ ዝውውር ለመፍጠር ለሁሉም ባንኮች ግብዣ ልከናል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ባንኮቹን ለማስተናገድ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል። ንግድ ባንክ በሁለት ሳምንት ውስጥ 'ሲስተሙን ከኛ ጋር እንደሚያቀናጅ አሳውቆናል'ም ብለዋል።

ይህ ማለት ቀድሞ ያሉ የሞባይል ባንክ ስርዓቶች የአንድ ባንክ ደንበኛ መሆንን ይጠይቃሉ። በአንፃሩ ቴሌብር የየትኛውም ባንክ ደንበኛ መሆን ሳይሆን ሲምካርድን ብቻ ይጠይቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Firehiwot Tamiru

አገልግሎቱን እንዴት ማግኘት ይቻላል?

ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ላይ 53 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት ሲሆን ከዚህ ውስጥ ደግሞ 25 ሚሊዮኑ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ናቸው።

23 ሚሊዮን ደንበኞች ደግሞ ስማርት ስልክ አላቸው።

እናም እንደዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገለጻ 23 ሚሊዮኑ ደንበኞች ለዚህ አገልግሎት የተዘጋጀውን መተግበሪያ በማውረድ መጠቀም ይችላሉ።

ሌላኛው አማራጭ ደግሞ ኮከብና [*]መሰላልን [#] በመጫን በሚቀርቡ አገልግሎቶች ወይም USSD እና በአጭር የጽሁፍ መልዕክት መሆኑን አስረድተዋል።

የስልክ ቁጥርዎ ልክ እንደ ባንክ አካውንት ቁጥር ያገለግላል። በእጅዎ ያለውን ጥሬ ገንዘብ ለኢትዮ ቴሌኮም ወኪል ይሰጣሉ ወኪሉ ደግሞ በእጅዎ ያለውን የገንዘብ መጠን ወደ እጅ ስልክዎ ይልከዋል። ወይም በተቃራኒው ከእጅ ስልክዎ ገንዘብ ወደ ወኪሉ ልከው ወኪሉ ደግሞ የላኩትን መጠን በጥሬ ገንዘብ ይሰጥዎታል።

ሞባይል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በስፍት መገኘቱ ከፋይናንስ ተቋም በበለጠ የገንዘብ ዝውውርን ለማስፋፋት ያግዛል የሚሉት ስራ አስፈጻሚዋ "በርካታ አገራት በቀላሉ ዜጎች ለግንኙነትና መረጃ ለመለዋወጥ የሚጠቀሙበትን ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በመጠቀም ገንዘብ መላክና መቀበል እንዲሁም ክፍያ እንዲፈጽሙ በማድረግ የፋይናንስ ተደራሽነትን ከፍ ማድረግ ችለዋል" ብለዋል።

በኢትዮጵያ 35 በመቶ የሚሆነው ዜጋ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆኑን የጠቀሱት ስራ አስፈጻሚዋ "የቀረው ሰፊው በሚሊዮን የሚቆጠር ማህበረሰብ ሊሳተፍ ያልቻለ ነው ማለት ነው። .....ስለዚህ በሞባይል ቴክኖሎጂ ታግዘን ሰፊውን ማህበረሰብ በፋይናንስ አግልግሎት ተደራሽ ብናደርገው ጤነኛ የሆነ የፋይናንስ ፍሰትና ዘለቄታዊነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ያግዛል" ሲሉ ይገልጻሉ።

እናም የቴሌ ብር ዋነኛው ዓለማ ባንክን የመሰሉ የፋይናንስ ተቋም ያላገኘውን ሰፊውን የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ማድረግ ነው።

አገልግሎቱን ለማግኘት ተጠቃሚዎች በራሳቸው መተግበሪያውን በማውረድ ወይም #127* በመደወል አልያም 127 የጽሁፍ መልዕክት በመላክ መመዝገብ እንደሚችሉም ተናግረዋል።

እናም ኢትዮ ቴሌኮም በአምስት ዓመታት ውስጥ ከ40 እስከ 50 የሚሆነውን የኢትዮጵያ የገንዘብ ዝውውር በቴሌብር በኩል እንዲሆን አቅዷል።

አሁን ላይ ገንዘብ ወደቴሌ ብር ገቢ ወይም ወጪ ለማድረግ በመጀመሪያ ዙር 1ሺህ 500 ወኪሎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው ይህንንም ቁጥር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ 15 ሺህ ለማሳደግ መታቀዱን ገልጸዋል።

ቴሌ ብርና የባንኮች የሞባይል አገልግሎት

በኢትዮጵያ የተለያዩ ባንኮች የእጅ ስልኮችን በመጠቀም ገንዘብ ማንቀሳቀስ እንደሚቻል ሲያስተዋውቁ ይደመጣል።

ታዲያ ቴሌ ብር ከእነዚህ በምን ይለያል የሚል ጥያቄ ለዋና ስራ አስፈጻሚዋ አቅርበንላቸው ሲመልሱ "አንደኛ ደበኞቻችን 53 ሚሊዮን ደርሰዋል፤ የባንክ ተጠቃሚዎችችን ግን እዚያ ላይ አልደረሱም። ስለዚህ ሰፊ ያልደረስናቸውን ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ የተሻለ ያገለግለናል" ሲሉ ያብራራሉ።

በሁለኛ ደረጃ ደግሞ "ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ የሞባይል ቴክኖሎጂ ባንኮች ከደረሱት በላይ ለመድረስ ያስችላል" ብለዋል።

አገራት ይህንን ስርዓት በመዘርጋታቸው ጥሬ ገንዘብ ለማሳተምና ደህንነቱን ለመጠበቅ የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ አግዟልም ብለዋል። ከዚህም ባሻገር ኢትዮቴሌኮሞ ልክ የአየር ሰአትን በብድር እንደሚሸጠው ሁሉ ገንዘብን በቴሌ ብር በኩል የማበደር እቅድም አለው።

መሰል አገልግሎቶች የኢትዮጵያን የቴሌኮም ዘርፍ ለሚቀላቀሉ የውጪ ኩባንያዎች አለመፈቀዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቴሌ ብር ይፋ በሆነበት ስርዓት ላይ ተናግረዋል።

ይህም በመሆኑ ምክንያት የዲፕሎማሲ ጫና እየተደረገብን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የውሳኔውን አስፈላጊነት ሲያስረዱ "በቀጥታ ከብሄራዊ ጥቅም ጋር ስለሚያያዝ ነው። ለውድድር የሚያመች ልምድ ስላልነበረን ተጠቃሚ ስለማያደርገን ነው" ብለዋል።

ሆኖም ይህንን አገልግሎት ኢትዮ ቴሌኮም ብቻውን የሚሰጠው ቢበዛ ለአንድ ዓመት ነው ሲሉም ገልጸዋል። በዚህ አንድ ዓመት ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮም ከ20 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን እንደሚመዘግብና ከዚህ ውስጥ ከ12 ሚሊዩን በላይ የሚሆኑት ንቁ ደንበኛ ሆነው 710 ሚሊዮን ብር ይዘዋወራል ተብሎ እቅድ ተይዟል።