የውጪ ሀገር ጥሪዎች ለምን በኢትዮጵያ ቁጥር ይወጣሉ?

የውጪ ሀገር ጥሪዎች ለምን በኢትዮጵያ ቁጥር ይወጣሉ

ለዓመታት ከተለያዩ ሀገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚደወሉ የስልክ ጥሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ ቁጥር እንዲቀየሩ ያደረጉ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የመታሰራቸው ዜና ይሰማል።

ኢትዮ-ቴሌኮም ማግኘት የሚገባውን ጥቅም ከሚያሳጡ ወንጀሎች መካከል የውጪ ጥሪዎችን በሀገር ውስጥ የስልክ ቁጥር ማስተላለፍ ይገኝበታል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው የሚያዩት የኢትዮጵያ ስልክ ቁጥር ከሆነ ጥሪው የሀገር ውስጥ እንደሆነ ያስባሉ።

ሆኖም ጥሪው ከጣልያን ወይም ከከሳዑዲ ሊሆን ይችላል። ቢሆንም ግን በጣልያን ወይም በሳዑዲ ሀገር የኮድ ቁጥር (ኤርያ ኮድ) ሳይሆን በኢትዮጵያ ቁጥር ይታያል።

ለመሆኑ የውጪ ሀገር ጥሪዎችን የሀገር ውስጥ ማስመሰል ለምንና በማን ይሰራል?

ቢቢሲ ያናገረው አቶ ተክሊት ኃይላይ ከሶስት ዓመታት በፊት በኢትዮ-ቴሌኮም የክራውድ ማኔጅመንት የአይቲ ባለሙያ ነበረ።

አሁን በግሉ የማማከር ስራ የሚሰራው አቶ ተክሊት፤ ቴሌ ሳለ ትራንጉላይዜሽን በሚባል መንገድ የውጪ ሀገር ጥሪን ወደ ሀገር ውስጥ ቁጥር የሚቀይሩ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ያሉበትን ቦታ ይለይ ነበር።

እንዴት የውጪ ሀገር የስልክ ጥሪዎች በኢትዮጵያ ቁጥር እንዲወጡ ይደረጋል?

ሲም ቦክስ ክራውድ ይባላል። ከተለያዩ ሀገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚደወሉ የስልክ ጥሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ ቁጥር እንዲቀየሩ ለማድረግ የሚፈልጉ ግለሰቦች ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው የኢትዮጵያ ሲም ካርድና የኢንተርኔት መስመር ይገዛሉ።

በሌላ ወገን "ኢንተርኮኔክት" የተባለ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋሞች ከኢትዮጵያ ውጪ ይገኛሉ። ከያሉበት ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ ጥሪዎች በኢትዮጵያ ቁጥር እንዲታዩ ማድረግ ይችላሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ከተቋሞቹ ጋር ስምምነት ላይ ይደርሳሉ። ከዛም ተቋሞቹ የውጪ ሀገር የስልክ ጥሪዎች (ራውቲንግ) ወደ ቴሌ ሳይሆን ግለሰቦቹ ወዳዘጋጁት ሲም ካርድ (አይፒ አድራሻ) አንዲላክ ያደርጋሉ።

"እነዚህ ጥሪዎች በቴሌ በኩል መተላላፍ ሲኖርባቸው ግለሰቦቹ ወደገዟቸው ሲም ካርዶች (የስልክ ቁጥሮች) ይሄዳሉ" ሲል ተክሊት ይገልጸዋል።

ስልክ የሚደወልላቸው የኢትዮጵያ ነዋሪዎች ምን እየተከናወነ እንደሆነ አያውቁም። በእርግጥ ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ ደዋዮችም ሆነ ሀገር ውስጥ የሚገኙ የጥሪው ተቀባዮች ስለ ሂደቱ አያውቁም። የሚያገኙት ጥቅምም የለም።

የስልክ ቁጥሩን መቀየር ለምን አስፈለገ?

አንድ ጥሪ ከውጪ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ሲደረግ በደቂቃ ወደ 11 ብር ገደማ ያስከፍላል። በአንጻሩ የሀገር ውስጥ ለሀገር ውስጥ የስልከ ጥሪ በደቂቃ ወደ 75 ሳንቲም ገደማ ያስከፍላል። ግለሰቦቹ በሚጠቀሙበት መንገድ ለውጪ ሀገር ጥሪ 75 ሳንቲም ብቻ በማስከፈል፤ ከ 11 ብር ላይ የቀረውን ገንዘብ ኢንተርኮኔክት ከሚሰሩ ተቋሞች ጋር ይቀራመቱታል።

ግለሰቦቹ ጥሪውን ለማስተላለፍ የሚያወጡት የኢንተርኔት ወጪ ብቻ ነው።

በኢትዮጵያ ህግ መሰረት የግለሰቦቹ ተግባር ህገ ወጥ ቢሆንም፤ ሂደቱን ህጋዊ አድርገው የሚገለገሉበት ሀገሮች ብዙ ናቸው።

አቶ ተክሊት እንደምሳሌ የሚጠቅሰው የሳዑዲ ቴሌኮምን ነው። የሳዑዲ ቴሌኮም የአለም አቀፍ ጥሪ ወጪ ለመቀነስ ሲም ቦክስ ክራውድን በይፋ ይጠቀማል ይላል።

በብዙ ሀገሮች ሲም ቦክስ ክራውድ መጠቀም ህጋዊ ስለሆነ ጥሪው የሚደረግባቸው ሀገሮች መንግሥታትን በህግ መጠየቅ አይቻልም።

ግለሰቦቹ ከውጪ ተቋማት ጋር የሚቀራመቱትን ገንዘብ ማግኘት የነበረበትን ቴሌ እንደሆነ የሚያስረግጠው ባለሙያው "ሂደቱ ህጋዊ ቢሆን ኖሮ ቴሌ ይጠቀም ነበር" ይላል።

መፍትሔው ምንድን ነው?

አቶ ተክሊት እንደሚለው ከተለያዩ ሀገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚደወሉ የስልክ ጥሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ ቁጥር እንዲቀየሩ የሚያደጉት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች በብዛት የሚሰሩት አዲስ አበባ፣ መተማና ሞያሌ ነው።

የስልክ ጥሪዎቹ በዋነኛነት የሚነሱባቸው ሀገሮች ደግሞ ቻይና፣ ጣልያንና ሳዑዲ ናቸው።

ከተለያዩ ሀገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚደወሉ የስልክ ጥሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ ቁጥር እንዲቀየሩ የማድረጉ ሰዎች በተደጋጋሚ ቢታሰሩም ብዙም ሳይቆይ ሌላ ቡድን ስራውን ይጀምራል።

"ቴሌ በምሰራበት ወቅት ተቋሙ በየወሩ ወደ ሶስት ሚሊየን ዶላር ያጣ ነበር" ይላል።

ባለሙያው እንደሚለው አሰራሩ ሀጋዊ ቢሆን የውጪ ተቋማት ከግለሰቦች ጋር ሳይሆን በቀጥታ ከቴሌ ጋር መደራደር ይችላሉ። ግለሰቦቹ በህገ ወጥ መንገድ የሚያገኙት ጥቅምም የተቋሙ ይሆናል።