በኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ ላይ ጭማሪ ሊደረግ ነው

መብራት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች ላይ የታሪፍ ጭማሪ ለማድረግ አስፈላጊው ሂደት መጀመሩን የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለስልጣን ሲያስታውቅ፤ ማሻሻያው ዝቅተኛ የኃይል ተጠቃሚዎችን እንደማይነካ ባለስልጣኑ ገልጿል።

ይህንን ለቢቢሲ የተናገሩት የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለስልጣን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጌታሁን ሞገስ ሲሆኑ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ጭማሪው በተለያዩ ደረጃዎች አልፎ ተቀባይነት ሲያገኝ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።

አቶ ጌታሁን የታሪፍ ጭማሪ ማድረግ ያስፈለገበትን ምክንያት ሲያብራሩ፤ ለመጨረሻ ጊዜ የታሪፍ ጭማሪ ተደርጎ የነበረው ከ12 ዓመታት በፊት እንደነበረ አስታውሰው ''በየዓመቱ ከ10-15 በመቶ ድረስ የዋጋ ግሽበት ነበር፤ የውጪ ምንዛሬ ዋጋ ላይም ከፍተኛ ለውጥ አለ" ብለዋል።

እንደዳይሬክተሩ "ከዚህ በተጨማሪ መስሪያ ቤቱ እስከ 60 በመቶ የሚሆኑ የካፒታል ዕቃዎችን ገዝቶ ነው የሚያስገባው በውጪ ምንዛሬ ነው። ከዚህ በተጨማሪ መስሪያ ቤቱ በስፋት የሚጠቀምባቸው ብረት እና የምህንድስና ዕቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ስላለ የዋጋ ማሻሻያ እንደናደርግ ግድ ብሎናል።'' ይላሉ።

ይህ ጭማሪ ሳይሆን ማስተካከያ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ ''መስሪያ ቤታችን በቂ ገንዘብ ከተጠቃሚዎች መሰብሰብ ባለመቻሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ላይ ተደጋጋሚ ቅሬታን ሲያስነሳብን ነበር'' ብለዋል።

ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ጋር ሲነጻጸር ኢትዮጵያዊያን ለኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚጠይቁት ገንዘብ አነስተኛ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ጌታሁን፤ ''በሌሎች ሃገራት በየሦስት እና አራት ዓመቱ የዋጋ ማሻሻያ ማድረግ የተለመደ ነው እኛ ሃገር ግን ላለፉት 12 ዓመታት አልተደረገም'' ይላሉ።

ብሔራዊ የኤሌትሪክ ታሪፍ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ የሚሰጡ ግብረ መልሶችን ካካተተ በኋላ የተጠቃለለ የውሳኔ ሃሳብ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ቀርቦ ይጸድቃል እንደሚፀድቅ አቶ ጌታሁን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አዲሱ ታሪፍ መቼ ወደ ሥራ ሊገባ እንደሚችል ለቀረበላቸው ጥያቄም ትክክለኛ ቀኑን መናገር እንደማይችሉ ነገር ግን አዲሱ ታሪፍ በአስቸኳይ ወደ ሥራ እንዲገባ የኢነርጂ ባለስልጣን ፍላጎት መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል።

ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉት የመስሪያ ቤቱ ደንበኞች ከፍጆታ መጠናቸው አንጻር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በመሆናቸው፤ በእነዚህ ደንበኞች ላይ የሚጣል ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ እንደማይኖር ያስረዱት አቶ ጌታሁን፤ ከፍተኛ የኤሌትሪክ ፍጆታ የሚጠቀሙ አነስተኛ ኃይል የሚጠቀሙትን እንዲደግፉ የሚያደርግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውን አሰራር እንደሚዘረጋ ተናግረዋል።