ፈጠራ፡ 'አውሮፕላን' ሰርተው ለማብረር የሞከሩት ወንድማማቾች

የፎቶው ባለመብት, Bikila Daniel
በምስራቅ ወለጋ ከነቀምቴ በቅርብ ርቀት በምትገኘው የሲቡ ሲሬ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወንድማማቾች ከሰሞኑ የሰሯትን 'አውሮፕላን' ለማብረር ጥረት ማድረጋቸው የበርካቶች መነጋገሪያ ሆነዋል።
ወንድማማቾቹ ለሊሳ ዳንኤል እና ቢቂላ ዳንኤል ይባላሉ።
ወጣቶቹ "ኦሮሚያ" ሲሉ የሰየሟትን 'አውሮፕላናቸውን' ለማብረር ሙከራ ማድረጋቸው የአከባቢ ሰዎች በታሪክ መዝገብ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለ ሞተር አውሮፕላን ካበረሩት አሜሪካውያን ወንድማማቾች ኦርቪል እና ዊልበር ራይት ጋር አነጻጽረዋቸዋል።
ወንድማማቾቹ የሰሯትን 'አውሮፕላን' ለማብረር ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
'አውሮፕላኗ' እንዴት ተሰራች?

የፎቶው ባለመብት, Bikila Daniel
ወንድማማቾቹ የሰሯት 'አውሮፕላን' 2 ሜትር ርዝመት እና 4.5 ሜትር ከፍታ እንዳላት ይናገራሉ። ሁለት ሰዎችን የማሳፈር አቅም ያላት ይህች 'አውሮፕላን' የክንፎቿ ርዝመት ከአንዱ ጫፋ እስከ ሌላኛው ጫፍ 7 ሜትር ይሆናል።
ቢቂላ እና ለሊሳ እንደሚሉት ከሆነ 'አውሮፕላኗን' ለመስራት ሦስት ዓመታት ፈጅቶባቸዋል።
ከጥቂት ቀናት በፊት የበረራ ሙከራ ለማድረግ ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳካ ይናገራሉ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱን "ሞተሩ ያረጀ ስለሆነ ከመሬት ተነስታ አልበረረችም" ሲሉ አስረድተዋል።
ወጣቶቹ ሙከራቸው ባይሳካም ሰዎች እንዳበረቷቷቸው ይናገራሉ። ሙከራ ባደረጉበት ወቅት አደጋ ሊያጋጥም ይችላል በማለት ስጋት ገብቷቸው የነበሩ ሰዎች እንደነበሩም አልሸሸጉም።
ወንድማማቾቹ አውሮፕላን የመሠረት ፍላጎት ከልጅነታቸው ጀምሮ የነበረ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ሰው ይዞ ሊበር የሚችል 'አውሮፕላን' ከመስራታችን በፊት "መብረር የሚችሉ ትናንሽ አውሮፕላኖችን" ሰርተናል ይላሉ።
"ልጆች እያለን ትንንሽ አውሮፕላኖችን እንሰራ ነበር። እናታችን ታበረታታናለች። የሚያስፈልጉን ነገሮችን ትገዛልን ነበር። ዛሬ ላይ አእምሯቸን እያደገ፤ የትምህርት ደረጃችንም ከፍ እያለ ሲመጣ መስራት እንችላለን [ሰው ይዞ መብረር የሚችል] ብለን ተነሳን" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ፈጣሪ በሰጠን ሙያ አውሮፕላን ሠርተን ተሳክቶልናል"
የሰሯትን 'አውሮፕላን' ኦሮሚያ ሲሉ የሰየሙት ወንድማማቾቹ፤ "ኦሮሚያ ወደፊት የራሷ የሆነ አቪዬሽን እንዲኖራት ምኞት ስላለን ነው" ብለዋል።
ከምን ተሰራች?

የፎቶው ባለመብት, Bikila Daniel
ቢቂላ እና ለሊሳ የሰሩት 'አውሮፕላን' በአካባቢያቸው ከሚገኙ ቁሳቁሶች እንደሆነ ይናገራሉ።
ወጣቶቹ የሞተር ሳይክል ሞተር፣ ከዋንዛ ዛፍ የተገኘ እንጨት፣ በድጋፍ መልክ ከሰዎች ያገኙት አሮጌ የአውሮፕላን ጎማ እንዲሁም ከባጃጅ የተወሰዱ እቃዎችን በግብዓትነት መጠቀማቸውን ይናገራሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ከአልሙኒየም የተሠራ ቆርቆሮ፣ ስፖንጅ፣ በርካሽ ዋጋ የተገዙ ያረጁ የአውሮፕላን መቀመጫዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ያስረዳሉ።
"ቆርቆሮ እና ብርት እርስ በእርስ እየተፋፋቁ ድምጽ እንዳይፈጥሩ ስፖንጅ ተጠቅመናል" በብለዋል ወንድማማቾቹ።
የዋርካ እንጨት ጠንካራ ስለሆነ እና ክብደት ስለሌለው ጥቅም ላይ ማዋላቸውን ይናገራሉ።
ይህን ለመሠረት ክህሎቱን ከየት አገኛችሁት ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ወንድማማቾቹ ኢንተርኔት እና መጽሃፍት ሲያጣቅሱ መቆየታቸውን ገልፀዋል።
ዩቲዩብ ላይ ያሉ ቪዲዮችን በመመልከት እና ከኢንተርኔት ላይ መጽሃፍትን እያወረዱ ሲያነቡ መቆየታቸውን ያስረዳሉ።
ወንድማማቾቹ እንደሚሉት ለሰሩት 'አውሮፕላን' አግባብ የሆነውን ሞተር ባለማግኘታቸው ከመሬት ተነስታ መብረር አልቻለችም።

የፎቶው ባለመብት, Bikila Daniel













