ቴክኖሎጂ ፡ ሳተላይት ኢንተርኔት ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በድርጅቶችም ሆነ በግለሰቦች ደረጃ ሳተላይት ኢንተርኔትን የሚጠቀሙ እንዳሉ ሰምተን እናውቅ ይሆናል። ከቴሌኮም ፈቃድ ውጭ ሳተላይት ኢንተርኔትን ሲጠቀሙ ተያዙ የሚልም ዜናም እንዲሁ። ለመሆኑ ሳተላይት ኢንተርኔት ምንድን ነው?
የ "ግርምተ ሳይቴክ" መጽሐፍ ደራሲና በፎርቹን መጽሔት ዝርዝር በዓለም ላይ በ2018 ከፍተኛ ገቢ ካስመዘገቡ 500 ድርጅቶች (Fortune500) መካከል በአንዱ የቴክኖሎጂ ኃላፊ እንዲሁም የቴክቶክ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ ሰለሞን ካሳ ጋር ከወራት በፊት አጭር ቃለ ምልልስ አድርገን ነበር።
ቢቢሲ ፡ ሳተላይት ኢንተርኔት ምንድን ነው?
ሰለሞን፡ ሳተላይት ኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ማለት ልክ በዳያል አፕ፣ በብሮድባንድ፣ በፋይበር ኦፕቲክስ ወይም በሌላ ዓይነት መንገድ የምናገኘውን ዓይነት ኢንተርኔት ሊሰጠን የሚችል ሌላኛው አማራጭ ማለት ነው።
በላንድ ላይን በምናውቀው ዓይነት በገመድ [ኬብል] አማካይነት የሚሰራጨውን ዓይነት ብዙዎቻችን እናውቀዋለን፤ እንጠቀምበታለን። ነገር ግን የሳተላይት ኢንተርኔት አጀማመሩ በፍፁም አሁን የምንጠቀመው ዓይነት የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ የሌለበት ሁኔታ ሲሆን፤ ምንም ዓይነት ሌላ ምርጫ በሚጠፋ ጊዜ በተለይ ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎችን እሳቤ በማድረግ የተሰራ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ነው።
ሳተላይት ኢንተርኔት የሚሰራውም ሕዋ [ስፔስ] ላይ ካሉ ሳተላይቶች ጋር በመሆን ተጠቃሚዎች ደግሞ ዲሽ ቤታችው ላይ ቢሯቸው ላይ በማድረግ፤ በመሬት ላይ ደግሞ የኔትወርክ ኦፕሬቲንግ ሴንተር እና ቴሌፖርት የሚባሉ አሉ።
በእነዚህ በሦስቱ ጥምረቶች ኢንተርኔትን ለተጠቃሚ የሚያደርስ ቴክኖሎጂ ነው። ይህ ቪሳት [Very small aperture terminal (VSAT) ይባላል። ሳተላይት ኢንተርኔት የሚሰራውም በዚህ አማካኝት ነው።
ቢቢሲ፡ ብሮድባንድ እና ሌሎች አማራጮች ባሉበት ሳተላይት ኢንተርኔትን መጠቀም ለምን ያስፈልጋል?
ሰለሞን፡ የብሮድባንድ ኢንተርኔት የለም ወይ? ያን መጠቀም በፍፁም አይቻልም ወይ ? የሚለው በቅድሚያ የሚነሳ ጥያቄ ነው። አንድ ሰው የብሮድባንድ ኢንተርኔት እያለው ለምን ሳተላይት ኢንተርኔት ይጠቀማል? እኔ አሁን ቤቴ ጥሩ የብሮድባንድ ኢንተርኔት አለኝ። ስለዚህ ሳተላይት ኢንተርኔትን መጠቀም አያስፈልገኝም። ምክንያቱም አንደኛ ውድ ነው፣ ፍጥነቱም ከብሮድባንድና ከሌሎቹ ዓይነቶች እጅግ ያነሰ ነው። ስለዚህ ለመገጣጠም [Install] የሚያስፈልጉ ቁሶችም ተጨማምረው ጠቀሜታ የለውም። በመሆኑም ይህ እንደተጠቃሚው ዓላማ ነው የሚወሰነው።
ቢቢሲ፡ ምን አልባት ከመረጃ ደህንነት ጋር በተገናኘ የተለየ ፋይዳ አለው?
ሰለሞን፡ ሳተላይት ኢንተርኔትና ከሳይበር ሴኩሪቲ አብሮ የሚነሳ ነገር ነው። ከመረጃ ጥበቃ አንፃር ምን አልባት ከዋናው የኢንተርኔት መሰረተ ልማት [Infrastructure] የወጣ ራሱን የቻለ ሊሆን ስለሚችል፤ ምን አልባት የቁጥጥር ሁኔታው [ Control feature] አነስ ሊል የሚችልበት ሁኔታ እንደሚኖር አስባለሁ።
ቢቢሲ፡ ማንኛውም ግለሰብ ተነስቶ ቴክኖሎጂው ስላለ ብቻ ሳተላይት ኢንተርኔትን መጠቀም ይችላል?
ሰለሞን፡ ይህ እንደየ አገሩ ሕግና የቴሌኮም አጠቃቀም ይለያያል። ነገር ግን እንዲህ አይነት ነገር ሲጠቀሙ የዚያ አገር መንግሥት አስተዳዳር ይህን ማወቅ አለበት።
ምክንያቱም ይህ ከአገር ደህንነት ጋር እንዲሁም ከብዙ ነገር ጋር ሊያያዝ ስለሚችል፤ ማንኛውም ሳተላይት ኢንተርኔትን ለመጠቀም የሚፈልጉ ድርጅቶች ከዓላማቸው አንፃር ኢንተርኔት ቢቋረጥ በብዙ ዓይነት የኢኮኖሚያዊና ኦፕሬሽን ኪሳራ ውስጥ የሚገቡ ዓለም አቀፍ ተቋማትና በጣም ትላልቅ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ካሉ እና ይህን ቴክኖሎጂ መጠቀም ከፈለጉ ከማንኛውም አገር፤ አገሪቷን ከሚያስተዳድረው አካል ጋር ተነጋግረው ፈቃድ አውጥተው የሚቀጥሉበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ነው የማስበው።
ቴክኖሎጂው ስላለ ብቻ አምጥቶ ቁጭ አድርጎ 'በቃ ኢንተርኔት አለኝ' የሚባል ነበር አይደለም። በሚገባው የፈቃድ ስርዓት ውስጥ መታለፍ አለበት።














