ያለ ንብ ማር፣ ያለ ላም ወተት ማምረት ይቻላል?

ማር

የፎቶው ባለመብት, MELIBIO

በቤተ ሙከራ የሚመረቱ የምግብ አይነቶች እየተበራከቱ ነው። በጣም ታዋቂ የሆነው ሥጋ ነው። አሁን ደግሞ ማር እና ወተት ጎራውን ተቀላቅለዋል።

ዳርኮ ማንዲች አትክልት ተመጋቢ ነው። ማንኛውንም አይነት የእንስሳት ተዋጽኦ አይመገብም። ማርን ጨምሮ።

ማርን ያለ ንብ ለማምረት ያሰበው ዳርኮ፣ ሜሊባዩ የተባለ ተቋም መስርቷል።

ሜሊባዩ ንቦች አበባ ቀስመው ማር የሚያመርቱበትን ተፈጥሯዊ መንገድ በመከተል በሰው ሠራሽ ሁኔታ ማር የሚያመርት ተቋም ነው።

ሥጋ፣ ማር ወይም ሌላ የምግብ አይነት በቤተ ሙከራ የሚሠሩ ተቋሞች ተፈጥሯዊውን ቅርጽ፣ ጣዕም እና መዓዛ ለማግኘት ይሞክራሉ።

ሜሊባዮ ከእነዚህ ቤተ ሙከራዎች አንዱ ነው።

በተፈጥሯዊ መንገድ በእርሾ አማካይነት የሚፈጠሩ ምርቶችን በሰው ሠራሽ መንገድ ለማምረት ይሞከራል። ማር፣ እንቁላል እና ወተት በቤተ ሙከራ ከተሠሩት መካከል ይጠቀሳሉ።

ለንደን ውስጥ ያለው ቤተር ዴሪ ወተት እና አይብ በሰው ሠራሽ ሂደት እያመረተ ይገኛል።

የተቋሙ አጋር መስራችና ዋና ኃላፊ ጄቫን ናጋራጃ "ቢራ ለማምረት እርሾ በምንጠቀምበት መንገድ ወተት እና አይብ ማምረት ይቻላል። ግን ቢራ ለማምረት የሚውለው የእርሾ አሠራር ላይ መጠነኛ ለውጥ ማድረግ ያስፈልገናል" ይላል።

እንቁላል ለማምረትም ተመሳሳይ መንገድ ይከተላሉ።

ሳን ፍራንሲስኮ የሚገኘው ክላራ ፉድስ ቤተ ሙከራ ውስጥ እንቁላል ያዘጋጃል። እአአ 2028 እንቁላሉን ለገበያ በማቅረብ የመጀመሪያው ድርጅት ለመሆን ወጥኗል።

ዋና ኃላፊው አርትሮ ኢሊዞድ እንደሚናገረው፤ እርሾ የሚያብላሉበት ሂደት የእንቁላሉን ቅርጽ እና ጣዕም ይወስናል። የቤተ ሙከራው እንቁላልም ዶሮ ከሚፈለፍለው እንቁላል ጋር ተመሳሳይ ነው።

የተለያዩ ምግቦችን በቤተ ሙከራ ማምረት ለአካባቢ ጥበቃ እንደሚረዳ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና ግብርና ተቋም እንደሚለው ሥጋ እና የወተት ተዋጽኦ ለአየር ንብረት ለውጥ መባባስ 14.5% ድርሻውን ይወስዳሉ።

የማር ፍላጎት መጨመር የተለያዩ የንብ ዝርያዎች ላይም ተጽዕኖ እያሳደረ ነው።

ማር አምራች ንቦች ላይ የሚደርሰው ጫና እየተባባሰ መምጣቱን ዳርኮ ይናገራል። ማር በቤተ ሙከራ ሲመረት ንጹህ ማር የሚጠቀሙ ሰዎች አገልግሎት ላይ ያውሉታል። ማርን ከተለያየ ንጥረ ነገር ጋር አዋህደው ምግብ የሚያዘጋጁ ተቋሞችም አማራጭ ያገኛሉ።

ሜሊባዩ የተባለው የቤተ ሙከራ ማር አምራች በዚህ ዓመት መጨረሻ ምርቱን ማከፋፈል ይጀምራል።

የተቋሙ አጋር መስራችና ዋና ኃላፊ ጄቫን እንደሚለው በቤተ ሙከራ የሚሠራ አይብን እንደ ፒዛ ሀት እና ማክዶናልድስ ላሉ ሬስቶራንቶች የመሸጥ እቅድ አላቸው።

አይቡ፣ እንቁላሉ እና ወተቱ ያለ እንስሳት ተሳትፎ ሙሉ በሙሉ በቤተ ሙከራ ስለሚሠራ ለአትክልት ተመጋቢዎች ይቀርባል።

እነዚህ የቤተ ሙከራ ምርቶች ገበያ ላይ ሲቀርቡ የተለያዩ አገራት መንግሥታት እንደ ተፈጥሯዊው ምርት መታየት እንዳለባቸው ያምናል።

ተፈጥሯዊ ማር ወይም ወተት የሚሰጡትን ጥቅም ከቤተ ሙከራው ማር እና ወተት ማግኘት እንደሚቻል ይናገራል። እንዲያውም በተሻለ ደረጃ ጥራታቸውን ጠብቀው እንደሚሠሩም ያክላል።

ለምሳሌ አይብ እና ወተት ውስጥ የሚገኘውን ላክቶስ ንጥረ ነገር አውጥቶ በስኳር ወይም በሌላ ንጥረ ነገር መተካት ይቻላል። ይህም የአይብ እና ወተት ተጠቃሚዎች በቀላሉ ምግቡን እንዲያብላሉ ይረዳቸዋል።

ጄቫን እንደሚለው፤ አሁን ላይ ሙከራ እየተደረገ ያለው በላም ወተት ቢሆንም የእናት ጡት ወተት ላይ ምርምር የማድረግም እቅድ አለ።