ምግብ ፡ ሲንጋፖር በቤተ ሙከራ ለተፈጠረ የዶሮ ሥጋ ፍቃድ ሰጠች

ሰው ሰራሹ የዶሮ ሥጋ

የፎቶው ባለመብት, EAT JUST

የሲንጋፖር የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን በቤተ ሙከራ "ምጥ" ተወልዶ ያደገውንና በዓለም የመጀመሪያ የሆነውን ሰው ሰራሽ ዶሮ ለገበያ እንዲቀርብ ፈቀደ።

ይህ የዶሮ ሥጋ ልዩ የሚያደርገው ከታረደ ዶሮ የተገኘ ሳይሆን በሳይንስ ከቤተሙከራ የተፈጠረ መሆኑ ነው።

ይህ ውሳኔ መቀመጫውን ሳንፍራንሲስኮ ላደረገው "ኢት ጀስት" ለተሰኘው አዲስ ኩባንያ በሲንጋፖር ገበያ ይከፍትለታል ተብሏል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከጤናና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ሥጋና የሥጋ ተዋጽኦ ውጤቶች የገበያ ድርሻቸው እያነሰ መጥቷል።

ከጤና፣ ከአካባቢ ጥበቃና ከአየር ንብረት ለውጥ ሰንሰለቶች ጋር ተያይዞ ሰዎች ማንኛውም ዓይነት ሥጋ መብላታቸው የሚደገፍ አልሆነም። የዓለም ሕዝብ ወደ አትክልት መመገብ ሙሉ ለሙሉ ፊቱን እንዲያዞር ማድረግ ደግሞ ቀላል አልሆነም።

ችግሩን ለመቅረፍ አንድ አማራጭ ተደርጎ ይታሰብ የነበረው ሥጋን ከከብቶች ሳይሆን ከቤተ ሙከራ በመፍጠር የሕዝቦችን አመጋገብ ሥርዓት መቀየር ነበር።

ይህን ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዳዲስ ሐሳቦች ብቅ ብቅ እያሉ ነው።

አንዱ ሳይንሳዊ ምርምር ያተኮረው ከእንሰሳቱ የመቅኔ ህዋስ ወስዶ ያንን ወደ ቤተ ሙከራ በማስገባት ጣፋጭና በቂ ፕሮቲን የሚሰጥ ሥጋን በመፈብረክ የእንሰሳት እርድን ማስቀረት ነው።

በዚህ ዘዴ የከብት ማርባት፣ ማሳደግና ማረድ እንዲሁም የቄራ ሂደቶችን ማስቀረት ይቻላል የሚል ትልም ነው የተሰነቀው።

የቤተሙከራ ሥጋ እውን ሲሆን አንዳችም የከብት እርድ ሳይፈጸም መፈሰክ፣ በርገር መግመጥ፣ ሥጋ ወጥ መሥራት ይቻላል።

ከዶሮ፣ ከበግ፣ ከፍየልና ከበሬ በተወሰደ የመቅኔ ህዋስ ብቻ በቤተ ሙከራ የተፈለገውን ያህል ሥጋ መቅረብ እንዲቻል በዓለም ላይ በብዙ አገሮች ምርምሮች እየተካሄዱ ናቸው። ብዙዎቹም ውጤት አስገኝተዋል።

ኢት ጀስትና መምፊስ ሚትስ ኩባንያዎች በዚህ ረገድ ከፊት ይሰለፋሉ።

ከመቅኔ ህዋሲ ወስዶ ሥጋ ለመሥራት ከአራት እስከ ስድስት ሳምንት ይወስዳል ተብሏል።

በቤተ ሙከራ የሚፈበረክ ሥጋ ጣዕሙን በተፈለገው መልኩ መቀያየር ይቻላል ይላሉ ሳይንቲስቶች።

ከሰሞኑ ማክዶናልድን ጨምሮ በአትክልት ውጤቶች ፈጣን ምግብ ቤቶች ዘንድ እንደ አማራጭ መቅረብ ጀምረዋል።

ከተለያዩ አትክልትና ከአተር የሚቀመሙት ምግቦች ሥጋ ባይሆኑም የሥጋ ጣዕም እንዲኖራቸው ተደርገው የተሰነጉ ናቸው።

ቢዮንድ ሚስ እና ኢምፖሲብል ፉድ ደግሞ በሱፐርማርኬቶች የአትክልት አማራጮችን ይዘው መቅረብ ችለዋል።

የአሜሪካው ኢት ጀስት ይዞት የቀረበው ሐሳብ ግን ከዚህ ሁሉ የተለየ ነው።

የአትክል አማራጭን ሳይሆን ከእንሰሳት መቅኔ ህዋስ የተወሰደና በቤተ ሙከራ የበለጸገ የዶሮ ሥጋን መሰረት በማድረግ ነው ወደ ገበያ እየመጣ ያለው። በመቅኔ ህዋስ ውስጥ በቤተሙከራ አሚኖአሲድና ካርቦሀይድሬት በመጨመር ሥጋው እንዲደረጅ ይደረጋል።

ኢት ጀስት ኩባንያ ሲንጋፖር የሰው ሰራሽ ዶሮ ሥጋ መፍቀዷ የዓለምን የአመጋገብ ሥርዓት ከነአካቴው የሚቀይር ትልቅ ተስፋን የጫረ ነው ሲል አሞካሽቶታል።

በርካታ አገራትም ይህንኑ ይከተላሉ ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግም ገልጧል።

ባለፉት ሁለት አሥርታት በርካታ አዳዲስ ኩባንያዎች ከእርድ ያልተገኙ የሥጋ ውጤቶችን በምርምር ለማምጣትና ወደ ገበያ ለማቅረብ ሞክረው አልተሳካላቸውም።

ሁለት የእስራኤል የምግብ ቴክኖሎጂ ምርምር ተቋማት የሆኑት ፊውቸር ሚት ቴክኖሎጂስ እና በቢል ጌትስ የሚደገፈው ሜምፊስ ሚትስ በቤተ ሙከራ የተገኙ ሥጋዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ወደ ገበያ ለማቅረብ ሞክረዋል።

በርካቶች ይህንን የሳይንስ ግኝት የምግብ ዋጋን በማውረድ፣ የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ትልቅ አስተዋጽ ይኖረዋል ቢሉም ሌሎች ሳይንቲስቶች ደግሞ እንዲያውም ቤተ ሙከራ ውስጥ የተመረተ ሥጋ የዓለም ገበያን ሲቆጣጠር ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ብለው ይሰጋሉ።

የከብት ርቢ ለአካባቢ ጥበቃ አደጋ ነው የሚባለው ከብቶችን ለማርባት በሚደረገው ሂደት ተረፈ ምርትና ከከብት ርቢ የሚወጣው ዝቃጭ ወንዞችንና ምንጮችን ስለሚበክል ነው።

የሲንጋፖር ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን የቤተ ሙከራ ግኝቱ ሥጋ ከጤና አንጻር ምንም አይነት ጉዳት ስላላገኘሁበት ለጊዜው በዶሮ ቅልጥም ጥብስ መልኩ ለገበያ መቅረብ ይችላል ሲል ፈቃድ ሰጥቷል።

ሥጋ ጠል- ቅጠል በል ሰዎች በዚህ የሳይንስት ግኝት ላይ ልዩነት አሳይተዋል። ግማሾቹ ጭካኔ የተሞላበትን የእርድ ሂደት ስለሚያስቀር ከዚህ በኋላ ሥጋ መብላት ችግር የለውም ሲሉ፤ ሌሎች በተቃራኒው ዞሮ ዞሮ ሰው ሰራሽ ሥጋው የተሰራበት ህዋስ የእንሰሳት ስለሆነ ይህን ሥጋ መመገብ ትክክል አይደለም ይላሉ።