ስዊዲን ፡ ወንድ ልጃቸውን ለ30 ዓመት ቤት ቆልፈው ያስቀመጡት እናት ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የስዊድን ፖሊስ አንዲት በዋና ከተማዋ ስቶክሆልም የሚኖሩ እናት ልጃቸውን ያለ አግባብ አስረዋል በሚል በቁጥጥር ሥር አውሏቸዋል።
ሴትዮዋ የሚኖሩት ከስቶክሆልም ወጣ ብሎ በሚገኝ ሰፈር ነው።
አሁን 40 ዓመት የሞላው ልጃቸው ምናልባት ላለፉት 30 ዓመታት ቤት ውስጥ ታስሮ ነበር የኖረው የሚል ጥርጣሬን አሳድሯል።
በሕክምና ላይ የሚገኘው ይህ ጎልማሳ የሴትዮዋ ልጅ ተቆልፎበት ከነበረው አፓርታማ በተገኘበት ወቅት ቆሳስሎና ቆሽሾ እንዲሁም ከባድ መጎሳቀል ውስጥ እንደኖረ በሚያሳብቅ መልኩ ነበር።
እናት የፖሊስን ክስ አስተባብለዋል።
እንዴት ከ30 ዓመት በኋላ ሊገኝ ቻለ?
ይህ ጎልማሳ ልጃቸው ሊገኝ የቻለው ባለፈው እሑድ ነው።
እናቱ ድንገት በመታመማቸውን ሆስፒታል ይወሰዳሉ።
እሳቸው ሆስፒታል በሄዱበት ጊዜ ሴት ልጃቸው ወደ ቤት በድንገት ትመጣለች።
ለ30 ዓመታት የታሰረውን ልጅ ያገኘችው ሴት የታጋቹ ታናሽ እህት ስትሆን ወደ መኖርያቸው የሄደችውም እሑድ ነበር።
ወደ እናቷ ቤት የሄደችውም መታመማቸውን በመስማቷ እንደሆነ ለስዊድን ዜና ማሰራጫ ተናግራለች።
እሷ ከቤት ወጥታ የራሷን ኑሮ የጀመረችው ገና ወጣት እያለች ሲሆን ከዚያ በኋላ ወንድሟን ለዘመናት አይታው እንደማታውቅ አብራርታለች።
ልጅ እያሉ ግን ወንድሟ ትምህርት ቤት እንዳይሄድ በድንገት በእናቷ ሲወሰን ይህን ለሚመለከታቸው ሰዎች መናገሯን አስታውሳለች።
ወንድሟ ትምህርት ቤት መሄድ የተወው በ11 ዓመቱ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, EPA
እሑድ ዕለት ወደ እናቷ አፓርታማ በሄደች ጊዜ ያደገችበትን ቤት አንድ ክፍል በር ስትከፍት ሽንት ሽንት የሚል ሽታ እንዳጋጠማት ተናግራለች።
ሰው ካለ በሚል “እዚህ ቤት! ሄሎ!” እያለች ጨለማ ክፍሉ ውስጥ ስትጣራ የሆነ እንቅስቃሴ እንዳስተዋለች አብራርታለች።
ድምጹን ወደሰማችበት አቅጣጫ ስትራመድ በአንድ ጥግ ኩርምት ብሎ የተቀመጠ ሰው ተመለከተች።
ያ ሰው አዳፋ ልብስ ለብሶና እግሩ አካባቢ ቆሳስሎ ነበር።
“እሱም ወንድሜ ለ30 ዓመታት ያላየሁት ወንድሜ ነበር” ብላለች።
“እንዳየኝ እንደምንም ቆሞ ለመቆም እየሞከረ ስሜን ደጋግሞ ይጠራኝ ነበር። ጥርሶቹ በሙሉ ወላልቀዋል። ስለዚህ ቃላት በትክክል ማውጣት አይችልም ነበር” ብላለች።
በጣም የገረማትም ከዚህ ዘመን በኋላ እንዴት እንዳልረሳት ብቻ ሳይሆን ሲያያት ምንም ፍርሃት እንዴት እንዳልተሰማው ነው።
የ40 ዓመት ጎልማሳ የሆነው ወንድሟ ሆስፒታል እንደደረሰ የሆስፒታል ሰዎች ጉዳዩን ለፖሊስ በማሳወቃቸው ነው እናት በቁጥጥር ሥር የዋሉት።
የስቶክሆልም አቃቢ ሕግ ኢማ ኦልሰን ግለሰቡ ቀዶ ጥገና ሕክምና እንዳደረገ ከመግለጽ ውጭ ተጨማሪ ያሉት ነገር የለም።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ኦላ ኦስተርሊንግ በበኩላቸው ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ይህ ሰው በእናቱ ለስንት ዘመን ቤት ውስጥ እንደታሰረ ገና የምናጣ ራው ጉዳይ ቢሆንም ነገር ግን ለብዙ ዓመታት በር ተቆልፎበት እንደኖረ ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።
እናቱ ለምን ልጃቸውን አሰሩት?
ኤቪቲ የስዊድን ቴሌቪዥን በጉዳዩ ላይ የሴትየዋን ሴት ልጅ አነጋግሮ ባቀረበው ዘገባ እንዳለው አጋች እናት የመጀመርያ ወንድ ልጃቸው ሞቶባቸዋል።
በዚህም ከፍተኛ ሐዘን ይሰማቸው ነበር።
ከሞት እንዲነሳላቸውም በጽኑ ይለምኑ ነበር።
ከዚያ በኋላ የወለዱትን ይህንን ወንድ ልጃቸውን የሰየሙትም ሞቶ መሪር ሐዘን ውስጥ በከተታቸው የበኩር ልጃቸው ስም ነበር።
ምናልባት ይህንን ልጃቸውን ለ30 ዓመታት ከርሳቸው ጋር አስረው ያቆዩት ከዚሁ ሞት ፍርሃት ጋር ተያይዞ ጤናማ ባልሆነ የቁጥጥር ስሜት በፈጠረው ሥነ ልቡና ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።












