ሐሰተኛ በተባለው ምስል ሰበብ ቻይና አውስትራሊያን ይቅርታ አልጠይቅም አለች

ቻይና አውስትራሊያን ይቅርታ አልልም አለች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ቻይና በመንግሥቷ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ አንድ የአውስትራሊያ ወታደርን የሚያሳይ አሰቃቂ ምስል በማውጣቷ ይቅርታ እንደማትጠይቅ አስታውቃለች።

ቻይና ጨምራም አውስትራሊያ የተፈጸመውን ድርጊት እንደጦር ወንጀል እንዳይታይ ለማድረግ እየሞከረች ነው ስትልም ከሳለች።

የአውስትራሊያ ወታደሮች ንጹሀን የአፍጋኒስታን ዜጎችን መግደላቸውን የሚጠቁም ሪፖርት ከወጣ በኋላ ምርመራ እየተደረገ ነው።

የቻይና ከፍተኛ ባለሥልጣን በትዊተር ገጻቸው የአውስትራሊያ ወታደር የአፍጋኒስታን ታዳጊ በስለት ሲገድል የሚያሳይ ፎቶ መለጠፋቸውን ተከትሎ፤ የተቆጣችው አውስትራሊያ ቻይና ይቅርታ ትጠይቀኝ ብላ ነበር።

በማኅበራዊ ገጾች ላይ የተሰራጨው ምሰል ሐሰተኛ ነው ስትልም አውስትራሊያ ከሳለች።

ቻይና በበኩሏ፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ለመሻከሩ ተጠያቂው አውስትራሊያ ናት ስትል ወንጅላለች።

የአውስትራሊያ መከላከያ እአአ ከ2009 እስከ 2013፤ የአውስትራሊያ 25 ወታደሮች 39 የአፍጋን ንጹሀን ዜጎችን ስለመግደላቸው ተአማኒ መረጃ አግኝቻለሁ ብሏል።

ቻይና ሪፖርቱ እንደወጣ አውስትራሊያን ኮንናለች።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባዩ ሊጃን ዛሆ፤ የተቀናበረ የአውስትራሊያዊ ወታደር ምስል በትዊተር ገጻቸው ለጥፈዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ስኮት ሞሪሰን "ቤጂይንግ አስቀያሚ ምስል በመለጠፏ ልታፍር ይገባል" በማለት ቻይና ይቅርታ ትጠይቀን ብለው ነበር።

በአውስትራሊያ የቻይና ኤምባሲ ግን ይቅርታ ሳይጠይቅ እንዲያውም የጠቅላይ ሚንስትሩን ንግግር ተችቷል።

"እኛን የሚወቅሱት የአውስትራሊያ ወታደሮች ከፈጸሙት አሰቃቂ ተግባር የሕዝቡን ትኩረት ለመውሰድ ነው" ሲል ኤምባሲው መግለጫ አውጥቷል።

አውስትራሊያ እና ቻይና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብተዋል።

አውስትራሊያ ስለኮቪድ-19 መነሻ ምርመራ ይደረግ ማለቷን ተከትሎ ደግሞ ነገሮች ተባብሰዋል።

ባለፉት ጥቂት ወራት ሁለት በቻይና ይሠሩ የነበሩ የአውስትራሊያ መገናኛ ብዙሃን ባልደረቦች እንዲወጡ ተደርጓል።

በቅርቡ ሁለት የአውስትራሊያ ምሁራን ቻይና ከመግባት ታግደዋል።

ቻይና የአውስትራሊያ ወይን ላይ 200% ቀረጥ መጣሏ ደግሞ ወደ ምጣኔ ሀብት ሽኩቻ ከቷቸዋል።