የፖሊስን ጭካኔ ተቃውሞ የሚመሩት ናይጄሪያውያን ሴቶች

ሪኑ ኦዱዋላ

የፎቶው ባለመብት, Rinu Oduala

የምስሉ መግለጫ, ሪኑ ኦዱዋላ

ሪኑ ኦዱዋላ ገና የ22 አመት ወጣት፣ ደፋርና፣ ሃሳቧን ያለምንም ፍራቻ የምትገልፅ ናት።

ባህርይዋ ለናይጄሪያ መንግሥት ፍራቻ ፈጥሮበትም የባንክ አካውንቷ እንዲታገድ ትዕዛዝ ተላልፏል።

ሪኑ ናይጄሪያውያን የፖሊስ ጭካኔን በመቃወም መንግሥት ለውጥ እንዲያመጣ አላፈናፍን በማለት ተቃውሟቸውን በመግለፅ ታሪክ ከሰሩ በአስር ሺህ ከሚቆጠሩ ወጣቶች መካከል አንዷ ናት።

ዘረፋን ለማስቆም የተቋቋመውን ልዩ የፖሊስ ክፍል ወይም ሳርስ ተብሎ የሚታወቀው ቡድን አንድን ሰው ሲገድል የሚያሳይ ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎ ተቃውሟዋን ለመግለፅ ሪኑ ጎዳና ላይ ወጣች።

ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን ማሰር፣ ማሰቃየትና ግድያም ይፈፅማል በሚልም ቡድኑ እንዲበተን ጠየቁ።

ሪኑም ከሌጎስ አስተዳዳሪ ቢሮ ውጭም ተቃውሟቸውን ለማሰማትም መጠለያ በመስራትም በርካቶችም ለተቃውሞ ሰፈሩ።

የመገናና ብዙሃን ባለሙያ መሆኗም በማኅበራዊ ሚዲያ ሰልፈኞችን በመጥራት፣ ውጪ ለሚያድሩ ተቃዋሚዎችም ብርድ ልብስ የማሰባሰብ ሥራዎችን ለመስራት ጠቅሟታል።

በርካታዎችም በመንግሥት ቢሮዎች ህንፃ ውጪ ለ72 ሰዓታት ተቃውሟቸውን እየገለፁም ውለው አድረዋል። በኋላም ፖሊስ ጥቃት በማድረሱ ተበትነዋል።

ከ172 ሺህ በላይ የትዊተር ተከታዮች ያሏት ሪኑ በባለፉት ስድስት ሳምንታት የናይጄሪያን መንግሥት መሰረት ካብረከረከው በርካታ የሴት ተቃዋሚዎች መካከል አንዷ ናት።

ሳርስ መቆም አለበት በሚለው የትዊተር እንቅስቃሴዋም ትዊተር በሰማያዊ ይፋ መለዮ እውቅና ሰጥቷታል።

ተቃዋሚዎች በሌጎስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሁኑ ወቅት በሌጎስ የፖሊስን ጥቃትና ትንኮሳን የሚከታተል የፍትህ አጣሪ ኮሚቴ ስብስብ አባል ናት።

የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሳርስ መበተናቸውን ተከትሎም ነው ይህ የፍትህ አጣሪ ኮሚቴ እንዲመሰረት ከፍተኛ ጥያቄ ቀርቦ የነበረው።

ሆኖም እሷም ሆነ 20 የተቃውሞው አስተባባሪዎች ደኅንነት አደጋ ላይ ወድቋል። የሪኑም ሆነ የሌሎቹ አስተባባሪዎች የባንክ አካውንት እንዲታገድ ትዕዛዝ ከማዕከላዊ ባንክ ከተላለፈ ሁለት ሳምንታትን አስቆጥሯል።

"የፖሊስን ጭካኔ ለማስወገድ የተነሳንበት ጥሩ አላማ እንደ ሽብርተኛ እንደሚያሳየን ማወቁ በጣም ልብ የሚሰብር ነው" በማለት ለቢቢሲ ተናግራለች።

ማዕከላዊ ባንክ በበኩሉ የእነዚህን ግለሰቦች የገንዘብ ምንጭን ለማጣራት በሚል ለሦስት ወራት ያህል የባንክ አካውንታቸው እንዲታገድ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተላልፏል ብሏል።

ጠበቃዋም ትዕዛዙን በመቃወምም እየሞገቱ ነው።

"ይሄ የመጀመሪያው ነው"

ሌላኛዋ ሳርስ እንዲበተን ስትሟገት የነበረችው ጠበቃ ሙዱፔ ኦዴሌም ባለፈው ወር ፓስፖርቷን ተነጥቃለች። በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ለእስር የተዳረጉ ግለሰቦችን ወክላም ሙያዊ እርዳታዋን ስትለግስ ነበር።

ባለፈው ሳምንትም በፌሚኒስቶች ጥምረት የተቋቋመ ድረ ገፅ ተዘግቷል። በአስር ሴቶች የተቋቋመው ይህ ድረ ገፅ የተዛባ የሥርዓተ- ፆታን መዋቅር ለማቃናት የተቋቋመ ሲሆን በተቃውሞውም ላይ ከፍተኛ ሚና ነበረው። ድረ-ገፁን የዘጋው አካልም ሆነ ለምን ተዘጋ የሚለው ጉዳይ ግልፅ አይደለም።

የታዋቂው አፍሮ ቢት ሙዚቀኛ ፌላ ኩቲ እናት ፉንሚላዮ ራንሶም ኩቲ

የፎቶው ባለመብት, Alamy

የምስሉ መግለጫ, የታዋቂው አፍሮ ቢት ሙዚቀኛ ፌላ ኩቲ እናት ፉንሚላዮ ራንሶም ኩቲ

በተቃውሞ ሰልፉ ላይ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች 385 ሺህ ዶላር ማሰባሰብ ችለዋል።

የተወሰነውንም ገንዘብ በተቃውሞው ለታሰሩት የሕግ ባለሙያ ምክር እንዲያገኙ ለማስቻል፣ ለቆሰሉት የህክምና ወጪ፣ በተቃውሞውም ላይ የግል ጥበቃን ለመቅጠርና በየዕለቱም ለሻይና አንዳንድ ወጪዎችም ውሏል።

ቀሪው የተሰባሰበውም ገንዘብ በፖሊስ ጭካኔ ጥቃት ለደረሰባቸውና በፖሊስ ለተገደሉ የጥቃት ሰለባ ቤተሰብ አባላትና እንዲሁም ለአዕምሮ ጤና ማማከር አገልግሎት ይውላል ተብሏል።

በፖሊስ ህይወታቸውን ላጡ ሰዎችም ማስታወሻ የሚሆኑ ተግባራትንም ድጋፍ ለማድረግ እቅድ ይዟል።

"ይህ በናይጄሪያ ወጣቶች የመንቃት ሁኔታ ጅማሮ ነው። አገሪቷ ያለችበትን ሁኔታ ለማሻሻል ብዙ እንሰራለን" በማለት የፌሚኒስት ጥምረት መስራች ከሆኑት መካከል ፋክሪያህ ሃሺም ለቢቢሲ ተናግራለች።

"ይህንን ትግላችን እንቀጥላለን በተለይም በሴቶች ህይወት ላይ ለውጥ ለማምጣት" ብላለች።

ናይጄሪያ ስር የሰደደ የሴት ጭቆና ያለበት አባዊ (ፓትርያርካል) ማኅበረሰብ የሰፈነባት አገር ብትሆንም ሴቶች ለውጥን በመሻት ከፍተኛ ድምፅ በማሰማት ይታወቃሉ፤ በተለይም በቅኝ ግዛት ትግል ወቅት።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ሳርስ መበተን አለበት በማለት ተቃውሞውን የሚመሩት ሴቶች መሆናቸውን ባለስልጣናቱን ማስደነቅም ሆነ ማስደንገጥ አልነበረበትም።

በጎሮጎሳውያኑ 1929 የአባ ሴቶች አመፅ ወይም (የሴቶች ጦር) መነሻው በደቡባዊ ናይጄሪያ የሚገኙ የገበያ ሴቶች ላይ ግብር መጣሉን ተከትሎ ነው።

ለሁለት ወራትም ያህል በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ተቃውሟቸውን በቅኝ ገዥዎች ባለቤትነት ስር ያሉ ሱቆች፣ ባንኮችና ፍርድ ቤቶች በማቃጠል ገለፁ።

በመጨረሻም የቅኝ ገዢዎቹ አስተዳዳሪዎች እቅዳቸውን መከለስ ነበረባቸው።

ከአባ ሴቶች አመፅ 18 ዓመታት በኋላ የታዋቂው አፍሮ ቢት ሙዚቀኛ ፌላ ኩቲ እናት ፉንሚላዮ ራንሶም ኩቲ በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ የተሰማሩ ግለሰቦች ላይ የተጣለውን ግብር በመቃወም በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን አደራጅታለች።

'የሊሳቢ አንበሲት' የሚል ቅጥያ ስም የተሰጣት ፉንሚላዮ ለነፃነት በተደረገው ትግል እንዲሁም የሴቶችን ጥያቄም በማጉላት ከፍተኛ አስተዋፅኦን በማበርከት ታሪክ ያስታውሳታል።

አቤኩታ ተብሎ የሚጠራውም የሴቶች ማኅበራቸውም 20 ሺህ ሴቶች አባላትን የያዘ ሲሆን በፅናታቸውም ይታወቃሉ።

"በናይጄሪያ ታሪክ ውስጥ ለመብታቸው የታገሉ በርካታ ሴቶች አሉ፤ ጠመንጃም ያነሱ በርካቶች ናቸው። ሴቶች የታገሉባቸው የጦር አውድማዎች ወይ ተዘንግተዋል ወይም ከታሪክ ተፍቀዋል" ትላለች የሴቶች መብት ተሟጋችና ሳርስ ይበተን ስትል የተቃወመችው ንዲ ካቶ።

ሳርስ ይበተን የጀርባ አጥንት

በቺቦክ ግዛት በፅንፈኛው ታጣቂ ቡድን ቦኮ ሃራም ታግተው የተወሰዱ ታዳጊ ሴት ተማሪዎችን ለማስመለስ ባለፉት ስድስት ዓመታት ስትሰራ የነበረችውና የ'ብሪንግ ባክ አወር ገርልስ' እንቅስቃሴ አንደኛዋ መስራች አይሻ የሱፉ በዚህም ተቃውሞ ውስጥ አንደኛዋ ተሳታፊ ነበረች።

በመዲናዋ አቡጃ ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ በመርጨት ተቃዋሚዎችን ለመበተን ሲሞክር አይሻ ፍንክች አለማለቷ ብዙዎችን አስደንቋል። በፅናት ፖሊሶችን መጋተሯም የሚያሳየው ፎቶ የሳርስን መበተን ለሚቃወሙ ሰልፈኞችም ምልክትና አርአያ ሆናለች።

ሴቶች የፖሊስ ጭካኔን የሚቃወመው ሰልፍ የጀርባ አጥንት መሆናቸው ለአይሻ አስገራሚ አይደለም።

"ሴቶች ሁሉን ነገር በማከናወን ቀዳሚውን ቦታ ይይዛሉ። በአገሪቱ ላይ ለውጥ ያመጡ የተቃውሞ ሰልፎችንም ብናይ የተመራው በሴቶች ነው" ትላለች።

"የሳርስ መበተን ተቃውሞም እንዲህ የተሳካው ሴቶች በተጫወቱት ከፍተኛ ሚና ነው። በተለይም የፌሚኒስቶች ጥምረት ተግባርና ትብብር በጣም አስደናቂ ነው። እነዚህ ሴቶች አስገራሚ ናቸው" ብላለች።

አይበገሬዎቹ

ንዲ ካቶ ትግሉ ገና እንደተጀመረ ትናገራለች "ወጣቶች ተመልሰው ድምፃችን የሚሰማበትን የተለያዩ መንገዶች ለመንደፍ እየሞከርን ነው። ተቃውሞውን አላቆምንም።"

ሳርስን ለመበተን በተደረገው ትግል ሴቶች በማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ መሬት ላይ ድምፃቸው እንዲሰማ የሄዱበትን መንገድም ለሴቶች እኩልነት በሚያደርጉት ትግልም መጠቀም እንዳለባቸው አይሻ ትናገራለች።

"ከፌሚኒዝም ባሻገር ሴቶች በኃይል አሰላለፉ ላይ መምጣት አለባቸው። ቦታ እንዲሰጠን መጠየቅ የለብንም እኛ ነን መፍጠር ያለብን" ትላለች።

"በፖለቲካው መሳተፍ ለምትፈልግ ማንኛዋም ሴት ጊዜው አሁን ነው። ራሳችንን መጠራጠር የለብንም። የሚገባንን ድርሻ እንጠይቅ ለዚያ ደግሞ ምንም አይነት ምክንያት አያስፈልገውም" በማለትም ታስረዳለች።

ሙዱፔ ኦዴሌም ትግሉ ይቀጥላል ትላለች።

"መጪው ጊዜ ለሴቶች ብሩህ ነው። ምን ማከናወን እንደምንችል ተረድተናል። ሴቶች ለማኅበረሳባቸውም ሆነ ለራሳቸው የሚፈልጉትን ማከናወን ከወሰኑ ማንም የሚያስቆማቸው የለም" በማለትም አፅንኦት ሰጥታለች።