ናይጄሪያውያን የፖሊስ ጭካኔን ተቃውመው ጎዳና ላይ ወጡ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የፖሊስን የጭካኔ በትር መቋቋም ያልቻሉ ናይጄሪያውያን ተቃውሟቸውን በጎዳናዎች ላይና በማህበራዊ ሚዲያዎች እያሰሙ ነው።
በተለይም ፖሊሶች አንድን ሰው ሲገድል የሚያሳይ ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎም ነው ተቃውሞቹ የተቀጣጠሉት።
እነዚህ ተቃውሞዎች በተለይም ዘረፋን ለማስቆም የተቋቋመውን ልዩ የፌደራል ፖሊስ ክፍል ወይም ሳርስ ተብሎ የሚታወቀው ላይ ያነጣጠሩ ሲሆኑ፤ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን ማሰር፣ ማሰቃየትና ግድያም ይፈፅማል በሚልም ከፍተኛ ውግዘትም እየቀረበበት ነው።
ይህንንም ተከትሎ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ የፖሊስ ጭካኔን አስቆማለሁ፣ በተቋሙም ላይ ማሻሻያ ይደረጋል ከዚህም በተጨማሪ ጥፋት ያጠፉትም ለፍርድ ይቀርባሉ በማለት መልእከታቸውን አስተላልፈዋል።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን ይበሉ እንጂ ተቃዋሚዎች ማሻሻያ ሳይሆን ሳርስ መፍረስና መበታተን አለበትም እያሉ ነው።
ከዚህ ቀደም በፖሊስ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች ምንም አይነት ለውጥ አላመጡም በማለትም ይተቻሉ።
ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው መንግሥታቸው "የፖሊስ ተቋምን ለማሻሻል ያለው ቁርጠኝነት ጥርጣሬ ውስጥ መግባት የለበትም" በማለት በትዊተር ገፃቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አክለውም "የፖሊስን ጭካኔና ያልተገባ ባህርይ ለማስቆም እየተሰሩ ያሉ ማሻሻያዎችንም በአሁኑ ወቅት እያየሁ ነው" ብለዋል።
በርካታ ፖሊሶች ናይጄሪያውያንን ለመጠበቅ የቆሙ ከመሆናቸው አንፃር ነገሩን በእርጋታ ማጤን እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
በዚህ ሳምንት አርብ በመዲናዋ አቡጃ የፖሊስ ጥቃትና ጭካኔን ለማውገዝ በወጡ ተቃዋሚዎች ላይ ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ ረጭቷል።

የፎቶው ባለመብት, TWITTER/@_EL_AMEEN/via REUTERS
የፖሊስ ቃለ አቀባይ በተቃዋሚዎች ላይ የተጠቀመው ኃይል እምብዛም ነው ቢሉም ሰልፈኞቹ በበኩላቸው በፖሊስ ድብደባ እንደደረሰባቸውና ተኩሶችም መስማታቸውን ተናግረዋል።
ከጎዳና ሰልፎች በተጨማሪ ኢንድ ሳርስ (ሳርስ መበተን አለበት) በሚል ሃሽታግ በትዊተር ላይ በርካታዎች የተሳተፉ ሲሆን ታዋቂዎቹ ናይጄሪያውያን ሙዚቀኞች ዊዝ ኪድና ዴቪዶም ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ናይጄሪያዊ- እንግሊዛዊው ተዋናይ ጆን ቦየጋም ከጎናችሁ ነኝ በማለት በማህበራዊ ድረ ገፁን ድጋፉን ገልጿል።
ኢንድ ሳርስ የሚለው ሃሽታግ ከሁለት አመታት በፊት ሲሆን የተጀመረው ከሰሞኑም በሳርስ ቡድን ኣባላት ወጣቱ መገደሉን ተከትሎም እንደገና ወደ ትዊተር መጥቷል።
በርካቶችም በፖሊስ የደረሰባቸውን ግፍና ስቃይም አጋርተዋል። ይህ የፖሊስ ቡድን በአብዛኛውን ጊዜ ወጣቶችን ኢላማ እንደሚያደርግ የተነገረ ሲሆን በርካቶች ገንዘብ በመክፈል ነፃ ቢሆኑም ሌሎች ግን ላልተገባ እስር እንዲሁም ግድያ መዳረጋቸውን የቢቢሲው ኢንዱካ ኦሪጅንሞ ከአቡጃ ዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዛሬው ዕለትም የናይጄሪያ ምርመራ ኃላፊ መሃመድ አዳሜ ሳርስ ሰዎችን አስቁመው እንዳይፈትሹና መንገድም ላይ ድንጋይ አስቀምጠው መንገዶችን ለመዝጋት ከሚያደርጉት እንዲቆጠቡ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ሁልጊዜም የፖሊስ መለዮዋቸውን እንዲለብሱና ምርመራም እንደሚጀመር ኃላፊው ቢያሳውቁም ተቃዋሚዎቹ ማሻሻያ መስማት አንፈልግም። ቡድኑ ሊበተን ይገባል በማለታቸውም ፀንተዋል።
ከዚህ ቀደምም በዚህ ቡድን ላይ አንዳንድ ማሻሻያዎች ቢሞከሩም ውጤት አላፈሩም ተብሏል።












