ኮሮናቫይረስ፡ በብራዚል በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ150 ሺህ በለጠ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ ከተጠቁት አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ብራዚል በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ150 ሺህ በላይ መሆኑን የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በቫይረሱ በሟች ቁጥርም ከአሜሪካ እየተከተለች ሲሆን በቫይረሱ በተያዙ ሰዎችም ቁጥር ብዛት ከአሜሪካና ከህንድ ተከትላ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችም ቁጥር ከአምስት ሚሊዮን የተሻገረው በዚሁ ሳምንት ነው።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጄይር ቦልሶናሮ ወረርሽኙን በማጣጣል እንዲሁም የተለያዩ ባለሙያዎች መመሪያዎችን አገሪቷ እንድትጥል የሰጧቸውን ምክር ችላ በማለት ይወቀሳሉ።
በደቡብ አሜሪካ ካሉት አገራትም ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ሞት የተመዘገባት ሲሆን ትልቋ ከተማ ሳኦ ፖሎም ክፉኛ ከተጎዱት መካከል ናት።
ከጤና ሚኒስቴር በተገኘውም መረጃ መሰረት ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 150 ሺህ 198 ሲሆን 5 ሚሊዮን 82 ሺህ 637 ብራዚላውያንም በቫይረሱ ተይዘዋል።
በቀጠናው ክፉኛ ከተመቱት መካከል ብራዚልን እየተከተለች ባለችው ኮሎምቢያ ደግሞ 27 ሺህ 495 ዜጎቿን በወረርሽኙ ያጣች ሲሆን 894 ሺህ 300 ሰዎችም በቫይረሱ መያዛቸውን አረጋግጣለች።
በአሁኑ ሰዓት በብራዚል የሟቾች ቁጥር በተወሰነ መልኩ የቀነሰ ሲሆን በባለፉት ሁለት ወራትም 1 ሺህ ሟቾች እየተመዘገቡ ነበር።
ፕሬዚዳንቱ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ባለመጣል እንዲሁም በሽታውን "ቀለል ያለ ጉንፋን ነው" በማለታቸውም ውርጅብኝን አስተናግደዋል።
ሆኖም ራሳቸውም በኮሮናቫይረስ ተይዘው የነበሩት ፕሬዚዳንት ትችቱን አይቀበሉትም።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሃሚልተን ሙራዎም የመንግስታቸውን አካሄድ በመደገፍ ህዝቡ አካላዊ ርቀቱን ባለመጠበቁ ነው ወረርሽኙ የተዛመተው በማለት ህዝቡን ወንጅለዋል።













