የስፔኗ ካናሪ ደሴት በርካታ የምዕራብ አፍሪካ ስደተኞች እየጎረፉባት ነው ተባለ

በካናሪ ከደረሱት ስደተኞች መካከል

የፎቶው ባለመብት, EPA

በርካታ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ስደተኞች ወደ ስፔኗ ካናሪ ደሴቶች እየጎረፉ እንደሆነ ቀይ መስቀል አስታውቋል።

በባለፉት አርባ ስምንት ሰዓትም 1 ሺህ ስደቶች መድረሳቸውን ያስታወቀው የቀይ መስቀል መረጃ በአስር አመታት ውስጥ ያልታየ ቁጥርም ነው ተብሏል።

በደሴቲቷ ጉብኝት ያደረጉት የስፔን የስደተኞች ሚኒስትር ጆሴ ሉይስ ኤስክሪቫ "የተቀናጀ ምላሽ እንሰጣለን" በማለትም ቃል ገብተዋል።

ከምዕራብ አፍሪካ አገሮች አንስቶ ደሴቲቱ የሚያደርሰው መስመርም ከ2018 ጀምሮ እውቅናን አትርፏል።

ከዚህ ቀደምም ከፍተኛ የስደተኞች ቁጥር የታየው በጎሮጎሳውያኑ 2006 ሲሆን 35 ሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞች በስፔን የባህር ዳርቻ ደሴቶች ላይ መድረሳቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።

ከምዕራብ አፍሪካዋ ሴኔጋል የተነሱት በርካታ ስደተኞችም ከ1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር በላይ በውሃ መጓዝ የሚጠበቅባቸው ሲሆን በዚህ ሳምንትም 186 ሰዎች የተሳፈሩባቸው ሁለት ጀልባዎች በሴኔጋል የባህር ኃይል መያዛቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

የስፔን ቀይ መስቀል እርዳታ ለስደተኞቹ ሲያደርግላቸው

የፎቶው ባለመብት, EPA

በነዚህ ሁለት ቀናት የደረሱት ስደተኞችም ከሴኔጋልና ከጋምቢያ መሆናቸውም ተገልጿል።

ስደተኞቹ በ37 ጀልባዎችም ወደ ደሴቲቷ መድረሳቸውንም የስፔን የዜና ወኪል ኢፌኢ ዘግቧል።

የስፔን የቀይ መስቀልም ጊዜያዊ መጠለያ በማዘጋጀት እንክብካቤም እያደረገላቸው ይገኛል።

የቀይ መስቀል ቃለ አቀባይ ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት አንዳንድ ቀለል ካለ በሽታ በስተቀር ሁሉም በሙሉ ጤንነት ላይ የሚገኙ እንደሆኑና የኮሮናቫይረስ ምርመራም ተደርጎላቸዋል ብለዋል።

የስደተኞቹ ሚኒስትር ሁኔታውን ለመረዳት ሶስቱን ዋነኛ የስፔን ደሴቶችን ጎብኝተዋል።

ሆኖም ስደተኞቹ በቋሚነት የሚኖሩበትን ቤት አላመቻቹም በሚልም የምክር ቤት አባሉ ብላስ አኮስታ መተቸታቸውን ኤልሙንዶ ጋዜጣ ዘግቧል።

ከጥር እስከ ሃምሌ ባሉት ወራት 3 ሺህ 269 ስደተኞች ከምዕራብ አፍሪካ ተነስተው ካናሪ ደሴቶች የደረሱ ሲሆን ይህም ቁጥር በዚሁ ወቅት ከነበረው ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር 600 በመቶ መጨመሩን አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) አስታውቋል።

በዚህ አመትም ደሴቶቹ ለመድረስ ሲሉ የ250 ሰዎች ህይወት መቀጠፉንም እንዲሁ አይ ኦ ኤም አክሎ ገልጿል።