የሴቶች መብት፡ "ወሲባዊ ጥቃቶችና ግድያ ማስፈራሪያዎች፣ አፀያፊ ስድቦች..."- በኢንተርኔት የሴቶች ጥቃት

ሜይትሬይ ራማክሪሽናን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሜይትሬይ ራማክሪሽናን በኔትፍሊክስ ላይ ለዕይታ በበቃው 'ኔቨር ሃፍ አይ ኤቨር' የኮሜዲ ፊልም ላይ በመሪ ተዋናይነት ከፍተኛ እውቅናን አትርፋለች።

የ18 ዓመቷ ተዋናይት የመሪ ተዋናይነቱን ቦታ ያገኘችው ከአስራ አምስት ሺህ ተወዳዳሪዎች መካከል ነው።

በኔትፍሊክስ ላይ ከፍተኛ ተመልካች ካገኙ ፊልሞች መካከል በሆነው በዚህ ፊልም ላይ ከስደተኛ የሕንድ ቤተሰቦች በአሜሪካ የተወለደችና ስደተኝነትን፣ ባህልና አሜሪካዊ ታዳጊ መሆንን ለማጣጣም የምትጥር ገፀ-ባህርይን ወክላም ተጫውታለች።

በፊልሙም ላይ ባሳየችው የትወና ችሎታም ከፍተኛ አድናቆትን ማትረፍ ችላለች።

ያገኘችው ድንገተኛ ዝናም በተወሰነ መልኩም ቢሆን ተወዳጅ ብቻ የምትሆን መስሏት ነበር።

"ለሥራውም ቢሆን እንደዚህ አይነት ቃለ መጠይቆች ራሴን አዘጋጅቻለሁ። በጭራሽ ያልጠበቅኩትና መቼም ቢሆን ላዘጋጅ የማልችለው በኢንተርኔት ላይ ለገጠመኝ ጥላቻ ነው" ትላለች።

ሜይትሬይ የኢንተርኔት ጥላቻ የምትለው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የገጠማትን ትንኮሳ ነው።

"እንዲህ አይነት ትንኮሳ እንደሚያጋጥም መጠበቅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የምንኖርባት ዓለም ይህቺ ናትና" በማለትም ታስረዳለች።

አክላም "አፀያፊና ዘግናኝ የሚባሉ አስተያየቶች ይፃፉብኛል። የሞት ማስፈራሪያዎችም ይደርሱኛል። እንዲህ አይነት ነገር ያው በእውነታ ሲያጋጥም ሌላ መልክ ይኖረዋል" ትላለች።

ካናዳዊቷ ተዋናይት በማኅበራዊ ሚዲያ የሚገጥማት የሞት ማስፈራሪያም ሆነ ትንኮሳና ስድብ ግራ ስላጋባትም ለተወሰነ ጊዜም አካውንቶቿን ሁሉ ዘግታለች።

"የተወሰነ ወቅት ላይ ሁሉንም የማኅበራዊ ሚዲያ ገፆች እኔ ነበርኩ የምቆጣጠራቸው። የራሴን ድምፅ በትክክለኛ መልኩ ማሰማት ስለምፈልግ ነበር ያንን የማድርገው" የምትለው ተዋናይቷ "በአሁኑ ጊዜ ግን አካውንቶቼን ዘግቼ እረፍት እየወሰድኩኝ ነው" ትላለች።

'በርካታ ታዳጊዎችና ሴቶች ትንኮሳና ጥቃት በኢንተርኔት ይደርስባቸዋል'

ሜይትሬይ ታዋቂ ተዋናይት ስለሆነች ነው እንዲህ አይነት ትንኮሳዎችን፣ ዘግናኝና አፀያፊ ስድቦችን የምታስተናግደው ብላችሁ ካሰባችሁ ተሳስታችኋል።

ከ15 አስከ 22 እድሜ ያሉ 14 ሺህ ታዳጊዎችና ሴቶች ተመሳሳይ ትንኮሳ እንደሚደርስባቸውም በቅርቡ የተሰራ የዳሰሳ ጥናት ይፋ አድርጓል።

እነዚህም ታዳጊዎችና ሴቶች በሃያ አገራት ነዋሪዎች ናቸው።

ለዚያም ነው ተዋናይቷ በሥርዓተ-ፆታ እኩልነትና፣ ትንኮሳዎችን ለመከላከል በሚሰራው ፕላን ኢንተርናሽናል ለተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አምባሳደር የሆነችው።

በዳሰሳ ጥናቱ ላይ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው 58 በመቶ ያህሉ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ትንኮሳ ወይም ጥቃትን አስተናግደዋል።

ከአስሩ ስምንቱ ደግሞ አፀያፊና፣ ዘግናኝ፣ ዘረኛ ስድቦችን እንዲሁም የወሲባዊ ጥቃት ማስፈራሪያዎቸ እንደገጠማቸው ተናግረዋል።

"ይሄ መቼም ቢሆን ዝም ሊባል የሚገባው ጉዳይ አይደለም። ኢንተርኔት በርካታ ዕውቀቶችን የምንማርበት መድረክ ነው። ሆኖም በዚህ ፋንታ ታዳጊዎችና ሴቶች የየቀኑ ህይወታቸው አልበቃ ብሎ በኢንተርኔትም ላይ ተመሳሳይ ትንኮሳ ማጋጠሙ አሳዛኝ ነው" ትላላች ሜይትሬይ።

በኢንተርኔት ላይ የሚደርስ ጥቃት ሴቶች ከማኅበራዊ ሚዲያ እንዲወጡ እየገፋቸው ነው።

ፕላን ኢንተርናሽናል በሰራው የዳሰሳ ጥናት መሰረት ከአምስት ታዳጊና ሴቶች መካከል አንዷ በኢንተርኔት ላይ በሚፈጸመው ትንኮሳና ጥቃት ምክንያት የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንታቸውን ይዘጋሉ ወይም የሚያሳልፉትን ጊዜ ይቀንሳሉ።

እነዚህ ጥቃቶች በአብዛኛውን የሚያጋጥሙት በፌስቡክና በኢንስታግራም ላይ መሆኑንም ጥናቱ አመልክቷል።

ሴቶች በዚህ መንገድ ከማኅበራዊ ሚዲያ መገለላቸው በተለይም በዚህ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት በርካቶች ኢንተርኔትን ሙጥኝ ባሉበት ጊዜ መሆኑ አሳዛኝ እንደሚያደርገው የፕላን ኢንተርናሽናል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አን ብሪጂት አልብሬክትሰን ተናግረዋል።

"ታዳጊዎችንና ሴቶችን ከኢንተርኔቱ መድረክ በዚህ መንገድ ማባረር በጣም አሳፋሪ ነው። በተለይም በዚህ ዲጂታል ዓለም ላይ ሴቶች የሚሰሙበትና መሪ የሚሆኑበትን አቅም ማሳጣትም ነው" ብለዋል ሥራ አስፈፃሚዋ።

"እነዚህ ጥቃቶች አካላዊ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን ማስፈራሪያ፣ ስድብና ትንኮሳው ራሳቸውን በነፃነት እንዳይገልፁ ይገድባቸዋል፤ ያሳስራቸዋል" ብለዋል።

የሰብዓዊ መብት ታጋይዋ ወሲባዊና የዘረኝነት ጥቃት ማስፈራሪያዎች ደርሰውባታል

የአስራ ዘጠኝ ዓመቷ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና ፌሚኒስት ናዱስካ በአገሯ ኒካራጓ በተወሰነ መልኩ ትንኮሳን ብታስተናግድም በከፍተኛ ሁኔታ ያስደነገጣት ግን ስፔን በሄደችበት ወቅት መሆኑን ትናገራለች።

በባለፈው ዓመት የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ በተደረገው ዘመቻ ወደ ስፔን ያቀናችው ናዱስካ፤ ማስፈራሪያዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማስተናገዷን ታስታውሳለች።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና ፌሚኒስት ናዱስካ

የፎቶው ባለመብት, Plan International

የምስሉ መግለጫ, የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና ፌሚኒስት ናዱስካ

በርካታ የጥላቻ መልዕክቶች እንደደረሷት የምትናገረው ናዱስካ አንዳንዶቹም "መጤ ነሽ ከአገር እናባርርሻለን፤ እንደበድብሻለን" የሚሉም ነበሩ።

"በጣም ነው ያስፈራኝ። በእውነቱ በኢንተርኔት ላይ ደኅንነት አይሰማኝም" ትላለች።

በተደጋጋሚ ትንኮሳና ጥቃቶችን ያስተናገደችው ናዱስካ ሁኔታው በጣምም ስለረበሻት የአዕምሮ ጤንቷንም በተወሰነ መልኩ ነክቶት ነበር። የሥነ ልቦና አማካሪዎችን ማየት እንዲሁም መድኃኒትም መውሰድ ጀምራለች።

በተለያዩ አገራት መሬት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በተመሳሳይ በኢንተርኔት ላይ የሚያጋጥሙ ሲሆን በተለይም አናሳ ማኅበረሰብ ተብለው በሚታሰቡና የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ላይ ጥቃቱ እንደሚበረታም የዳሰሳ ጥናቱ ይፋ አድርጓል።

"እንደ ሚቱ (እኔም) እና የጥቁር ህይወት ዋጋ አለው (ብላክ ላይቭስ ማተር) የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎች ማኅበራዊ ሚዲያው ምን ያህል ለትግሉ ጠቃሚ መድረክ እንደሆኑ አሳይተዋል" ይላሉ አን ብሪጀት።

ጥናቱ ይፋ ያደረገው እውነታ የሚረብሽ እንደሆነ የሚናገሩት ሥራ አስፈፃሚዋ፤ ከፍተኛ ትንኮሳ ያለበት አህጉር አውሮፓ ሲሆን ይህም 63 በመቶ የሚሆኑ ታዳጊዎች በኢንተርኔት ላይ የሚደርስባቸውን ትንኮሳ ሪፖርት አድርገዋል።

ዝቅተኛው ደግሞ ሰሜን አሜሪካ ሲሆን ቁጥሩም 52 በመቶ ነው።

የሚቱ እንቅስቃሴ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"በአካል ከሚደርስባቸው ትንኮሳ በላይ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በታዳጊዎች ላይ የሚደርስው ትንኮሳ ከፍተኛ ነው" ይላሉ ሥራ አስፈፃሚዋ።

በሥርዓተ ፆታ እኩልነት ላይ የሚሰሩ ግለሰቦችም እንዲህ አይነት ትንኮሳዎች ሙሉ በሙሉ ሴቶችን ከኢንተርኔቱ መድረክ እንዳያርቃቸውም ይፈራሉ።

"ወንዶች የብልታቸውን ፎቶ በተደጋጋሚ መላካቸው አስድንጋጭ ነው"

ለማኅበራዊ ሚዲያ አዲስ የሆኑ ሴቶች በኢንተርኔት ላይ የሚከናወኑ ትንኮሳዎችም ሆነ አንዳንድ ያልተገቡ ድርጊቶች ተስፋ አስቆራጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ኡጋንዳዊቷ፣ የ20 ዓመቷ ካቲ ትናገራለች።

ከሦስት ዓመት በፊት የማኅበራዊ ሚዲያ ገጿን ስትከፍት የተሰማትም ስሜት ይሄው ነው። በልብስ ሰፊነት እናቷን፣ እህቷንና ወንድሟን የምታስተዳድረው ካቲ ማኅበራዊ ሚዲያን የተቀላቀለችው ካለባት የሥራ ጫና እፎይታና እረፍት አገኝበታለሁ በሚል እሳቤ ነበር።

ነገር ግን በፌስቡክ የተዋወቀችው ሰው ራቁቱን እንዲሁም የብልቱን ፎቶ እየላከ ያስጨንቃት ጀመር።

የ 20 አመቷ ካቲ

የፎቶው ባለመብት, Plan International

የምስሉ መግለጫ, የ 20 አመቷ ካቲ

"አንድ ግለሰብ በፌስቡክ ላይ 'ሃይ' የሚል መልዕክት ላከልኝ፤ እኔም በምላሹ 'ሃይ' አልኩት"፤ ቀጥሎም "እንዴት ነሽ ሲለኝ ምላሽ ሰጠሁኝ" ትላለች።

"በነገታው ስነቃ ሌሊቱን ሙሉ ራቁቱንና ብልቱን የሚያሳዩ በርካታ ፎቶዎች ልኮልኛል። በጣም ነው የደነገጥኩት" ትላለች።

ካቲ ብቻ ሳትሆን በርካታ ታዳጊዎችና ሴቶች ይህ ሁኔታ በተደጋጋሚ እንደሚያጋጥማቸው ይናገራሉ። በጥናቱም ላይ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸውም መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ታዳጊዎች እንዲህ አይነት ጥቃቶች የየቀኑ ገጠመኛቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችንም ለመከላከል በርካታ ጥሪዎች እየቀረቡ ሲሆን አንዳንድ ኩባንያዎችም ፕሮግራሞችን ዘርግተዋል።

የኢንስታግራምና የዋትስአፕ ባለቤት የሆነው ፌስቡክ፤ ትንኮሳ ይደርስብናል የሚሉ ሪፖርቶችን በጥንቃቄ እንደሚከታተልና የመድፈር ማስፈራሪያዎች ደግሞ ሲሆኑ ወዲያው እንደሚያስወግድ አስታውቋል።

የታዳጊዎችንና የሴቶችን ደኅንነት በኢንተርኔት ላይ ለመጠበቅም ቁርጠኝነት እንዳለው የሚናገሩት የፌስቡክ የሴቶች ደኅንነት የበላይ ኃላፊ ሲንዲ ሳውዝወርዝ በዓለም ላይ ካሉ 200 የደኅንነት ተቋማትም ጋር በመተባበር በኢንተርኔት ላይ የሚደረገውን ጥቃት ለመከላከል እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ትዊተርም እንዲሁ በሴቶች ላይ በኢንተርኔት የሚደርሱ ጥቃቶችን ሴቶቹ ሪፖርት የሚያደርጉትን ከመከታተል በተጨማሪ የሚቆጣጠር ቴክኖሎጂም እየተጠቀመ እንደሆነም ገልጿል።

ሌላኛው ማኅበራዊ ሚዲያ ስናፕቻት ቃለ አቀባይም ለትንኮሳዎች፣ ማስፈራሪያዎችና ጥቃቶች ምንም አይነት ቦታ እንደሌለውና የማያውቋቸውን ግለሰቦች መልዕክት መላክ በማይቻልበት መንገድም ለመቆጣጠርም እንደሚሞከር አስታውቋል።

ቲክቶክ ይህ ዘገባ በሚዘጋጅበት ወቅት ምላሽ እንዲሰጠው ቢጠይቅም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።

በሥርዓት ፆታና ዲጂታል መብቶች ላይ የሚሰሩት ቼናይ ቼይር በአሁኑ ወቅት በኢንተርኔት ላይ ጥቃት የደረሰባቸውን በማገዝ አብረው እንደሚገኙ ገልፀው ማኅበራዊ ሚዲያዎች በእነዚህ ጥቃቶች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።

ተዋናይቷ ሜይትሬይ በበኩሏ ታዳጊዎችና ሴቶች ሪፖርት የሚያደርጉበትን መንገድ ከማጠናከር በተጨማሪ እነዚህ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ከመጀመሪያው ጥቃት እንዲፈጸም መፍቀድ የለባቸውም ትላለች።