በፈረንሳይ ፖሊሶችን ቪዲዮ መቅረፅ የሚከለክለው ረቂቅ ህግ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፈረንሳይ ፖሊስ በመዲናዋ ፓሪስ አዲሱን የፖሊስ ደህንነት ረቂቅ ህግ ለመቃወም የወጡ ተቃዋሚዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ በመጠቀም ላይ ነው። በረቂቁ ህግ መሰረት "ለመጥፎ ተግባር" ለማዋል ፖሊሶችን ፎቶ ማንሳትም ሆነ ቪዲዮ መቅረፅ ወንጀል ነው ይላል።
በዚህ የተቆጡ ፈረንሳያውያን ወደ ጎዳና ላይ የወጡ ሲሆን የተወሰኑትም ድንጋይና ተቀጣጣይ ነገር በፖሊስ መወርወራቸውን ተከትሎ ግጭት ተፈጥሯል ተብሏል። የጋዜጣ መሸጫ ኪዮስክና መኪኖች የተቃጠሉ ሲሆን በርካቶችም በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በፓሪስ 46 ሺህ የሚሆኑ ተቃዋሚዎች መውጣታቸውን የአገር ውስጥ ሚኒስትር የገለፀ ሲሆን በርካቶቹ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን ቢገልፁም የተወሰኑት ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል።
እስካሁን ድረስ 46 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፤ 20 ፖሊሶችም ተጎድተዋል።
ህጉ የፕሬስ ነፃነትን ይቃረናል፤ የፖሊስ ጭካኔንም ለመዘገብ እክል ይፈጥራል ይላሉ ተቃዋሚዎች።
"ረቂቅ ህጉ የፕሬስ ነፃነት ላይ እክል የሚፈጥር ነው። የማወቅና የማሳወቅ መብትን እንዲሁም ራስን በነፃነት የመግለፅ መብት ጋር የሚጣረስ ነው" በማለት ከተቃውሞ ሰልፈኞቹ መካከል መናገሩን አጃንስ ፍራንስ ፐሬስ ዘግቧል።
መንግሥት በበኩሉ ፖሊሶች በበይነ መረብ ከሚደርስባቸው ትንኮሳና ጥቃት ለመጠበቅ ነው ይላል።
ቅዳሜ እለት ከፓሪስ በተጨማሪ በፈረንሳዮቹ ቦርዶክስ፣ ሊሌ፣ ሞንትፔሊየር፣ ናንቴስና ሌሎች ከተሞችም የተቃውሞ ሰልፎች ነበሩ።
በዚህ ሳምንት ሶስት ነጭ ፖሊሶች አንድ ጥቁር የሙዚቃ ፕሮዲውሰር በዘረኝነት ተነሳስተው ሲደበድቡት የሚያሳይ ቪዲዮ ወጥቶ ነበር.
ሚሸል ዜክለር በፖሊስ ሲደበደብና በቡጡ ሲነረት የሚያሳይ ቪዲዮ በርካቶችን አስደንግጧል።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሁኔታውን "አሳፋሪ" ና "ተቀባይነት" የሌለው ያሉ ሲሆን በፖሊስና በዜጎች መካከል ያለው እምነትም እንደገና እንዲገነባ እቅድ እንዲቀርብ ጠይቀዋል።
በቪዲዮው ላይ የሚታዩት ፖሊሶችም ከስራ ታግደው ምርመራ እየተከናወነባቸው ነው።
በተለየ ዜና ፖሊስ በመዲናዋ ጊዜያዊ የስደተኞች መጠለያን ማፍረሱን ተከትሎ ከስደተኞችና ተሟጋቾች ጋር ግጭት ተፈጥሯል። በዚህም ላይ ፖሊስ ሙሉ ሪፖርት እንዲያቀርብ ትእዛዝ ተላልፏል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ረቂቅ ህጉ ለምን አወዛጋቢ ሆነ?
በአገሪቱ ታችኛው ምክር ቤት ድጋፍ የወጣው ረቂቅ ህጉ ምክር ቤቱ እንዲያፀድቀው እየተጠበቀ ነቅ። ከረቂቅ ህጉ ውስጥ አንቀፅ 24 እንደሚያትተው በስራ ላይ ያሉ ፖሊሶች "አካላዊም ሆነ ስነ ልቦናዊ ጉዳት" ለማስከተል በሚል ፎቶ ማንሳትም ሆነ ቪዲዮ መቅረፅ በወንጀል ያስቀጣል ይላል።
ህጉን ተላልፈው የተገኙም አንድ አመት እስርና 53 ሺህ 840 ዶላር ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
መንግሥት እንደሚለው ረቂቅ ህጉ ሚዲያም ሆነ ግለሰቦች የፖሊስን ጥቃት ሪፖርት የማድረግ መብታቸውን አይከለክልም፤ የረቂቅ ህጉ ዋና አላማ ለፖሊስ ጥበቃ ለመስጠት ነው በማለት ይከራከራል።
ተቃዋሚዎች ግን እንደሚሉት ባለፈው ሳምንት እንደተፈፀመው ጥቁር ግለሰብ በፖሊስ ሲደበደብ የሚያሳይ ቪዲዮ አይጋለጥም ነበር ይላሉ።
ረቂቅ ህጉ ከፍተኛ ትችን ማስተናገዱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂን ካስቴክስ አንቀፅ 24ን ለማሻሻል ኮሚሽን አቋቁማለሁ ብለዋል።












