ፖሊሶች በአንድ ጥቁር ላይ የፈጸሙትን ጥቃት ፕሬዝዳንት ማክሮን አወገዙ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሦስት ፖሊሶች ፓሪስ ውስጥ አንድ ጥቁር ሙዚቀኛን ሲደበድቡ የሚያሳይ ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎ ድርጊቱን "ተቀባይነት የሌለውና አሳፋሪ" ሲሉ አወገዙ።
በዚህም ሰበብ በፖሊስና በዜጎች መካከል መተማመንን እንደገና ለማጎልበት ያለሙ ሐሳቦች እንዲቀርቡም ጠይቀዋል።
ፈረንሳይ "ለአመፅ መፈጠር፣ ለጥላቻ ወይም ለዘረኝነት መስፋፋት" መንገድ ልትከፍት አይገባም ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
በቪዲዮው ላይ ማይክል ዘክለርን ሲደበድቡ የሚታዩት ሦስት የፖሊስ መኮንኖች ከሥራ የታገዱ ሲሆን ቁጥጥር ስር ውለዋል ምርመራም እየተደረገባቸው ነው።
የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ዠራልድ ዳርማኒን "የሪፐብሊኩን ዩኒፎርምን ያረከሱ" በመሆናቸው መኮንኖቹ ከሥራ እንዲሰናበቱ ግፊት እንደሚያደርጉ ለፈረንሳይ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
በፈረንሣይ ዋና ከተማ የተቀረፀው ቪዲዮ ለሕዝብ ይፋ ከተደረገ በኋላ ቁጣቸውን ከገለጹት መካከል ለፈረንሳይ የዓለም ዋንጫን ያነሱት የእግር ኳስ ኮከቦች ይገኙበታል።
የፈረንሣይ መገናኛ ብዙሃን አንድ ባለሥልጣን ጠቅሰው ፕሬዝደንት ማክሮን በተፈጠረው ክስተት እንደተበሳጩ መግለጻቸውን ዘግበዋል።
ማክሮን በተከታታይ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ሁሉንም ዓይነት አድሎዎችን በተሻለ ሁኔታ ለመዋጋት ሀሳቦች ያስፈልጋሉ ብለዋል።
"ሕጉን የሚያስከብሩ አካላት ሕጉን ማክበር አለባቸው። በዕለት ተዕለት ህይወታችን እኛን ለመጠበቅ በድፍረት የሚሰሩትን አንዳንዶች የሚያደርጉት የሚያረክሰው በመሆኑ በጭራሽ አንቀበልም" ብለዋል።
ፈረንሳዊው የእግር ኳስ ኮከብ ክሊያን ምባፔ የቅርብ ጊዜውን ክስተት በማውገዝ ከብሔራዊ ቡድኑ እና ከሌሎች ስፖርተኞች ጋር ተቀላቅሏል።
"ሊቋቋሙት የማቻል ቪዲዮ፣ ተቀባይነት የሌለው ብጥብጥ። ዘረኝነትን አልቀበልም ይበሉ" ሲል በደም የተሸፈነውን ፕሮዲውሰር ምስል ተጠቅሞ በትዊተር ገጹ ገልጿል።
የደኅንነት ካሜራ ቪዲዮው ሐሙስ ዕለት ነበር ይፋ የተደረገው። ግለሰቡ ስቱዲዮው ከገባ በኋላ ሦስት ፖሊሶች ሲረግጡት፣ በቡጢ ሲመቱት እና ሲደበድቡት ይታያል። ግለሰቡ መጀመሪያ ላይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ባለመያዙ እንዲቆም ተደርጎ እንደነበር ተገልጿል።
ዘክለር በአምስቱ ደቂቃ ድብደባ ወቅት የዘረኝነት ጥቃት እንደደረሰበት ተናግሯል። በእምቢተኝነት ተከሶ በቁጥጥር ሰር ቢውልም ዐቃቤ ሕግ ክሱን ውድቅ አድርገው በፖሊሶቹ ላይ ምርመራ ከፈተዋል።
አቤቱታውን ለማቅረብ ከጠበቃው ጋር የፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት የሄደው ዘክለር ለጋዜጠኞች "እኔን መጠበቅ የነበረባቸው ሰዎች ጥቃት ሰንዝረውብኛል። ለዚህ የሚያበቃ ምንም ነገር አላደረግኩም። ሦስቱም በሕጉ መሠረት እንዲቀጡ እፈልጋለሁ" ብሏል።
የፓሪስ ከንቲባ አን ሂዳልጎ "በድርጊቱ በጣም ደንግጫለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፈረንሣይ መንግሥት አወዛጋቢውን የፀጥታ ረቂቅ አዋጅ እንዲወጣ እየሠራ ሲሆን ተቃዋሚዎች ግን ሕጉ የመገናኛ ብዙሃን የፖሊስ ባህሪን የመመርመር አቅማቸውን ያዳክማል በሚል እየተቹት ነው።
የረቂቅ ህጉ አንቀጽ 24 እንደ ግለሰብ ለጥቃት ይጋለጣሉ ተብለው የሚገመቱ የፖሊስ ወይም የጦር ሠራዊት አባላት ምስሎችን በማህበራዊ ድር አምባዎች ላይ መለጠፍ እንደ ወንጀል ይቆጠራል።
የሕጉ ተቺዎች እንደሚሉት እንደዚህ ያሉ ምስሎች ይፋ ካልሆኑ ባለፈው ሳምንት እወንደወጡት ካሉት ክስተቶች መካከል አንዳቸውም ይፋ አይወጡም ነበር።
መንግሥት አዲሱ ረቂቅ ሕግ የፖሊስ በደሎችን ሪፖርት የሚያደርጉ መገናኛ ብዙሃን እና ዜጎች መብት ላይ አደጋ አያደርስም ሲል ይከራከራል።
ትችቱን ተከትሎ መንግስት አንቀፅ 24 ላይ ማሻሻያ በማከል "የፖሊስ መኮንን ወይም የወታደርን አካላዊ ወይም ሥነልቦናዊ ታማኝነትን ለመጉዳት በግልጽ ያነጣጠሩ ምስሎችን ማሰራጨት ላይ ብቻ ያተኮረ" መሆኑን አስታውቋል።
ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ሰዎች በአንድ ዓመት እስራት ወይም እስከ 40 ሺህ ፓውንድ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።












